Get Mystery Box with random crypto!

ከሥራ አጥነት ወደ ቀጣሪነት የተሸጋገሩ የቸሃ ወጣት አርሶአደሮች ከተንጣለለው የቃሪያ ማሳ ደርሰና | ATC NEWS

ከሥራ አጥነት ወደ ቀጣሪነት የተሸጋገሩ የቸሃ ወጣት አርሶአደሮች

ከተንጣለለው የቃሪያ ማሳ ደርሰናል። በስተቀኝ ደግሞ ሽንኩርት፣ ኪያር፣ ጥቅል ጎመን፣ ዝኩኒና ሌሎችም የጓሮ አትክልቶች በስፋት ተተክለው ይታያሉ። በቅርብ ርቀት ደግሞ በርከት ያሉ ሴቶችና ወጣቶች የቀሩ ምርቶችን በመሰብሰብ ሥራ ተጠምደዋል። ይህ ከ30 ሄክታር በላይ የሚልቀው ማሳ ታዲያ ከዓመታት በፊት ከባህር ዛፍ ውጪ ምንም አገልግሎት የማይሰጥ ሜዳ እንደነበር ከአካባቢው አርሶ አደሮች ነግረውናል።

ወጣት ዳንኤል ሽፈታ እዚሁ ቸሃ ወረዳ ወድሮ ቀበሌ ላይ ነው ተወልዶ ያደገው። ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ በሆርቲካቸር ትምህርት ዘርፍ ተመርቆ በእርሻ ሥራ ለመሰማራት ከአራት ጓደኞቹ ጋር ይመክራል፤ የራሳቸውን ሥራ ለመጀመር የሚያግዛቸውን 70 ሺ ብር ከቆጠቡ በኋላ ከቸሃ ወረዳ 28 ሺ ብር ብድር፣ ምርጥ ዘርና እንደ የውሃ ፓምፕ የመሳሰሉ ግብዓቶችን በማግኘት በአንደኛው ጓደኛቸው አባት ጓሮም ሽንኩርትና ሌሎች አትክልቶችን ማልማት ይጀምራሉ።

ከአንድ ሄክታር በማይልቀው መሬት ላይ አልምተው 70 ሺ ብር ሲያገኙ ልባቸው የበለጠ ለማልማት ተነሳሳ፤ እናም ከአንድ ሄክታር ወደ ሁለት፤ ከሁለት ወደ ሦስት ሄክታር መሬት አሰፉ። የምርት አይነታቸውንም ከዚህ ቀደም በአካባቢው ኅብረተሰብ ብዙም ያልተለመዱ ግን ደግሞ በከተሞችና በውጭ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ እንደ አበባ ጎመን፣ ብሮኮሊና ኪያር ያሉ የጓሮ አትክልቶችን እንዲያለሙ ወረዳው ሰባት ሄክታር መሬት አመቻቸላቸው። እነዚህ ብርቱ ወጣቶች ታዲያ ሳይታክቱ ማልማታቸውን ቀጠሉና እድገታቸውን ጨመሩ። ይህን ያየው የወረዳው አስተዳደርም የብድር አቅርቦቱን ወደ 300 ሺ ብር ከፍ አደረገላቸውና አቅማቸውን አጎለበቱ።

‹‹በአሁኑ ጊዜ የእርሻ መሬታችን 30 ሄክታር ሲሆን በዚህም ጎመን፣ ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ብሮኮሊ፣ አበባ ጎመን፣ ሃብሃብና ሌሎችም ተፈላጊ ምርቶችን በስፋት በማልማት ለገበያ እናቀርባለን›› የሚለው ወጣት ዳንኤል፤ በተለይም በወረዳው አማካኝነት በተፈጠረላቸው የገበያ ትስስር በመጠቀም ያለ ብዙ ድካምና እንግልት ምርታቸውን ወደ ተጠቃሚው እንደሚያደርሱ ይገልጻል። በአሁኑ ወቅት ካፒታላቸውን ወደ አስር ሚሊዮን ብር ማድረሳቸውን አመልክቶ፤ ከ100 በላይ ለሚልቁ የአካባቢው ወጣቶች በቋሚነት የሥራ እድል መፍጠራቸውን ያመለክታል።

በተጨማሪም በየቀኑ ከ100 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በእርሻው ላይ በጊዜያዊነት ተቀጥረው የሚሰሩበት ሁኔታ የተመቻቸላቸው መሆኑንም ይጠቅሳል።
ወጣት ዳንኤል እንደሚገልጸው፤ ምርቶቻቸውን አጎራባች ወረዳዎችና የክልሉ ዞኖች በስፋት ከማቅረብ በዘለለ፤ በኢትዮጵያም ሆነ በውጭ ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው ለመቅረብ ተግተው እየሠሩ ነው። በአሁኑ ወቅትም ጥሩና ምርታማ ዘሮችን በማባዛት ለአዳዲስ ማህበራትና አርሶአደሮች ያሰራጫሉ፤ ይህንንም ዘር የማባዛት ሥራቸውን በማጠናከር ክልሉ የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲጎለብት የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ ነው ያሉት።

በተጓዳኝም የእርሻ ተረፈ ምርታቸውን በማቀነባበርና መኖ በማዘጋጀት ከብቶችን የማደለብና የወተት ልማት ሥራ ለመሥራት ማቀዳቸውን ወጣቱ አርሶአደር ይናገራል። ውጥናቸው መሳካት ግን አሁን ያለው የብድር መጠን ሊሻሻል እንደሚገባ ሳይጠቁም አላለፈም። በሌላ በኩል ደግሞ ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው ቁጭ ያሉ ወጣቶች ከተስፋ መቁረጥ ውስጥ ወጥተው እንደእነሱ መንግሥት ያመቻቸውን ምቹ እድል እንዲጠቀሙ ነው የመከረው።
የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አክሊሉ ካሳ እንደሚናገሩት፤ ዞኑ በዋናነትም በበጋ መስኖ ልማት ከ30 ሺ ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ሰብሎችን እያመረተ ይገኛል።

ከዚህም ውስጥ ወደ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታን ምርት መሰብሰብ ችሏል። ዞኑ በስሩ ባሉ የወረዳና ቀበሌ መዋቅሮች የሚገኙ አርሶአደሮችን የመደገፍ ሥራ እያከናወነ ነው። በተጨማሪም እንደእነ ዳንኤል ድህነትን ታሪክ የሚያደርጉ በርካታ ወጣቶችን በመፍጠር የአካባቢውን ብሎም እንደሀገርም በምግብ እህል ራስን የመቻል እንቅስቃሴ ከግብ እንዲደርስ እየተሠራ ነው።

አዲስ ዘመን

ለጥቆማ @atc_newsbot
https://t.me/atc_news