Get Mystery Box with random crypto!

ሁለቱ ሕጎች “የውሸተኛ ቅጣቱ በሰዎች ያለመታመን ብቻ አይደለም፣ ከዚያ የከፋው ቅጣቱ እርሱ ራሱ | አስቂኝ ቀልዶችና ሌሎችም

ሁለቱ ሕጎች

“የውሸተኛ ቅጣቱ በሰዎች ያለመታመን ብቻ አይደለም፣ ከዚያ የከፋው ቅጣቱ እርሱ ራሱ ማንንም ለማመን አለመቻሉ ነው” - George Bernard Shaw

አንዳንድ ሰዎች መልካምና ጨዋ የሚሆኑት ካላቸው ጨዋ ማንነት ወይም የመልካም ስነ-ምግባር ዲሲፕሊን ተነስተው ሳይሆን ቅጣት ስሚፈሩ ብቻ ነው፡፡ ይህ ጠባብ አመለካከት ወደተበላሸ ማንነት እንድንወርድ የሚዳርግ አመለካከት ነው፡፡ ከአንድ ትክክል ካልሆነ ነገር መቆጠብ የሚገባን ዋና ምክንያት፣ ነገሩ ትክክል ስላልሆነና ጎጂ ስለሆነ ሊሆን ሲገባው፣ ለጊዜው ከቅጣት ለማምለጥ ወይም ጊዜያዊ ጥቅምን ለማግኘት ከሆነ ሁኔታው የማንነትን ብልሹነት አመልካች ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ማንኛውም ክፉ ተግባራችን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ከቅጣት አያመልጥም፡፡

በአለም ላይ ሁለት አይነት ሕጎች አንዳሉ በማሰብ መጀመር እችላለን፡፡ አንዱን ሕግ “የተፈጥሮ ሕግ” በማለት መሰየም ስንችል፣ ሁለተኛውን ሕግ ደግሞ “ሰው-ሰራሽ” ሕግ በማለት ልንሰይመው እንችላለን፡፡ ማንኛውም ተግባራችን ከእነዚህ ከሁለቱ ሕጎች በአንዱ ከመዳኘት በፍጹም አያመልጥም፡፡

“ሰው-ሰራሽ” ብለን የሰየምነው ሕግ አንድ የተከለከለ ነገር አድርገን ስንያዝ በተደነገገው ሰው-ሰራሽ ሕግ መሰረት ስንዳኝና ስንቀጣ ማለት ነው፡፡ “የተፈጥሮ ሕግ” ብለን የሰየምነው ደግሞ ምንም እንኳ ለጊዜው ከሰው-ሰራሽ ሕግ የምናመልጥበትን መንገድ ብናመቻች የሰራነው ስራ ቀስ በቀስ ዘሩ በቅሎ ሊቀጣን የመቻሉ ሁኔታ ነው፡፡
የምናደርጋቸውንም ሆነ ከማድረግ የምንገታባቸውን ነገሮች በሙሉ ከእነዚህ ሁለት ሕጎች አንጻር ብንመለከታቸው አመለካከታችንን የማስፋት ጠቀሜታ አለው፡፡

የምናደርጋቸውና ከማድረግ የምንገታቸው ክፉም ሆኑ ደግ ተግባሮቻችን የሚዳኙት በሁለት ሕጎች መሆኑን መገንዘብ የአመለካከት ዘይቤአችንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የመቀየር ጉልበት አለው፡፡ ዛሬ የማደርገውም ሆነ የምናገረው ጤና-ቢስ ነገር እጅ በእጅ ባይቀጣኝም ፈጠነም ዘገየም ፍሬው በቅሎ ጭማቂውን እንደምጎነጨው ማሰብ አስፈላጊ ነው፡፡

እያንዳንዱ ተግባሬ እንደዘር ስለሆነ ማለት ነው፡፡ ዛሬ አንድ መልካም ነገር ማድረግ እንደሚገባኝ እያወኩኝ ምንም እንኳን ማድረግ ባልፈልግና እጅ-በእጅ የሚከፈለኝ ዋጋ እንደሌለ ባስብም፣ በውስጤ ካለው መርህ የተነሳ በማድረጌ ምክንያት ነገ የሚበቅለውን ጣፋጭ ፍሬ መመገቤ አይቀርም፡፡ ይህ በፍጹም ሊሻር የማይችል ዘላቂ ሕግ ነው፡፡ ወይ እንተባበረዋለን፣ ወይም ደግሞ በተቃራኒው ሄደን የማንፈልገውን ውጤት ስንቀበል እንኖራለን፡፡ ምርጫው የእኛው ነው፡፡

ለህሊና እንኑር … ለሕዝብ እንኑር … ለመልካምነት እንኑር !

@askignkeldoch