Get Mystery Box with random crypto!

በትግራይ ተቋርጦ የነበረው የሰብዓዊ ድጋፍ ዳግም መጀመሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ፡ | Asham TV

በትግራይ ተቋርጦ የነበረው የሰብዓዊ ድጋፍ ዳግም መጀመሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ፡፡

አሻም ዜና |ነሀሴ 25፣ 2014 ዓ.ም

የድርጅቱ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ(ኦቻ) ነሐሴ 29 ቀን 2022 እ.አ.አ. ባወጣው መግለጫ፣ ያገረሸውን ጦርነት ተከትሎ ከነሐሴ 24 2022 ጀምሮ የሰብዓዊ እርዳታ መቋረጡን ገልፆ ነበር፡፡

ነሐሴ 30 ቀን 2022 የድርጅቱ ዋና ፀሃፊ ቃል አቀባይ ስቴፋኒ ዱያሪች በሰጡት ዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ እና ኦቻ እንዳረጋገጠው የሰብዓዊ እርዳታዎች ዳግም መዳረስ ጀምረዋል፡፡

ኦቻ ባወጣው መግለጫ ”እኛ እና ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የፀጥታው ሁኔታ በፈቀደው መጠን ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፡፡” ብሏል፡፡

ይህንኑ የኦቻ መግለጫ በንባብ ያቀረቡት ስቴፋኒ ዱያሪችም በአፋርና አማራ ክልሎች ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በአፋር ክልል ከያሎና ጉሊና ወረዳዎች በሺዎች የሚቆጡሩ ሰዎች በአካባቢው በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት ተፈናቅለዋል፤ ከአማራ ክልል አዋሳኝ በሆነው የጭፍራ አካባቢም በተመሳሳይ መልኩ ሰዎች መፈናቀላቸውን ገልፀዋል፡፡

በአማራ ክልል፣ በሰሜን ወሎ ዞን፣ በጃራ የመጠሊያ ጣቢያ ተጠልለው የነበሩ 30ሺህ ያህል ተፈናቃዮችም ለሁለተኛ ጊዜ መፈናቀላቸውን ተናግረዋል፡፡ በደቡብ ወሎ ዞን፣ ደሴ ከተማም መፈናቅሎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ቃል አቀባዩ ሁሉም ተፋለሚ ሀይሎች ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ ህግጋትን መሠረት በማድረግ ንፁሃንና የንፁሃን መገልገያ የሆኑትን እንዲጠብቁ፣ ንፁሃን ደህንነታቸው ወደሚጠበቅበት ስፍራ እንዲሄዱ እንዲፈቀዱላቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዮሐንስ አሰፋ