Get Mystery Box with random crypto!

ⒶⓇⓉⒾⓄⓈ ⒶⓇⓉⒾⓄⓈ | Artios Media

ⒶⓇⓉⒾⓄⓈ
ⒶⓇⓉⒾⓄⓈ

ARTIOS DEVOTION
ⓟⓗⓘⓛⓔⓜⓞⓝ
ቀን #4

በፍቅር እለምንሃለሁ

ፊል 8 - 11
---------------------------------
⁸ ስለዚህ ማድረግ የሚገባህን እንድታደርግ አዝህ ዘንድ በክርስቶስ ድፍረት ቢኖረኝም
⁹ በፍቅር እለምንሃለሁ፤ እንግዲህ ሽማግሌና አሁን ደግሞ የክርስቶስ ኢየሱስ እስረኛ የሆንሁት እኔ ጳውሎስ፣
¹⁰ በእስር እያለሁ ስለ ወለድሁት ልጄ ስለ አናሲሞስ እለምንሃለሁ።
¹¹ አስቀድሞ የሚጠቅምህ አልነበረም፤ አሁን ግን ለአንተም ሆነ ለእኔ የሚጠቅም ሰው ሆኖአል።
---------------------------------

ከመጀመሪያው ቀን አንስተን በተመለከትናቸው ክፍሎች ውስጥ የጳውሎስና የፊልሞና ወዳጅነት ጠንካራ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ጳውሎስ በክርስቶስ እንደ ተሾመ አገልጋይ፣ በመንፈሳዊ ልጆቹ ላይ ስልጣኑን ተጠቅሞ ማዘዝ ሲችል ያንን ማድረግ ግን አልመረጠም። የተሻለ ጉልበትና ተጽዕኖ ማሳረፍ ይችላሉ ብሎ ያሰበውን በፍቅርና በትህትና መለመንን ፈለገ።

በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ ጳውሎስ የደብዳቤው አንኳር መልዕክት ወደ ሆነው የአናሲሞስ ጉዳይ እየተንደረደረ ነው። ለፊልሞናም ልመናውን ሲያቀርብ ሁለት ዋና ነጥቦችን ያስቀምጣል፦

የራሱን ሁኔታ፦ ጳውሎስ በዚህ ቦታ ላይ እራሱን ሽማግሌና የክርስቶስ እስረኛ ብሎ ይጠራል። ሽማግሌ ሲል በእድሜ የገፋ ትልቅ ሰው፤ እንዲሁም የአስታራቂነትን ሚና እየተወጣ ያለ አባት መሆኑን ለማመልከት የተናገረ ይመስል።

በመቀጠልም ይህንን ልመና የሚያቀርበው በተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ በድሎት ተቀምጦ ሳይሆን በእስር ቤት ሆኖ መከራን እየተቀበለ መሆኑን ይነግረዋል።

በእርቅ ስነ ሥርዓት ውስጥ የአስታራቂዎች ማንነትና ተዓማኒነት ከፍተኛ ሚና ስላለው ጳውሎስ ስለ ሽምግልናውና ስላለበት እስራት መናገሩ ሁለቱን ለማቀራረብ መንገድ እየጠረገ ስለ መሆኑ ጥሩ ማሳያ ናቸው።

የአናሲሞስ ማንነት፦ አናሲሞስ የፊልሞናን ልብ አሳዝኖት ንብረቱን ዘርፎ የኮበለለ ወንጀለኛ ነው። ከዚህ የተነሣ የማይጠቅም ሰው እንደሆነ አሳይቷል። ይህ አይረቤነት ግን አስቀድሞ በሚባል ያለፈ የታሪክ ማህደር ውስጥ ያለ ጉዳይ እንጂ አሁን ግን የሚጠቅም ሰው መሆኑን ጳውሎስ በልበ ሙሉነት ይናገራል።

ፊልሞና እንዲቀበለው የሚለምነው ሰው አሁንም የሚጎዳውን ወንበዴ ሳይሆን በወንጌል እውነት ተለውጦ የሚጠቅመውን አናሲሞስን ነው።

በዛሬው ጥናታችን የጳውሎስን የትህትና፣ የፍቅር ጎዳና ምርጫ ደግሞም ጥልቅ በሆነ የማስታረቅ ጥበብ ሁለት የተጣሉና የተጎዳዱ ሰዎችን እንዴት እያቀረበ እንዳለ አይተናል።

ወንድሞቼ! ያለንበት ቤተክርስቲያን በተለያዩ ሁኔታ የተኮራረፉ፣ የተራራቁ፣ የተጎዳዱ አማኞች ያሉበት ሕብረት እንደሆነች መገመት አያዳግትም። የምንኖርበት ሀገርና ማህበረሰብም ቀላል በማይባል ደረጃ በጠላትነት፣ በጥላቻ እየኖረ እንዳለ ግልጽ ነው።

ስለዚህ ከላይ ያየናቸውን የእግዚአብሔርን ቃል መርህ በመከተል በቤተክርስቲያንና በማህበረሰቡ ውስጥ የእርቅና የሰላም ሰዎች ሆነን እንድንኖር ጌታ ይርዳን።

የእግዚአብሔር ጸጋና ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!!!

ዛሬ የማሰላስለው የቃሉ እውነት፦ የፍቅርና የትህትና ልመና ጉልበት!

የዛሬው ፀሎት፦ እግዚአብሔር ሆይ የእርቅ ሰው ሆኜ የሰላምና የፍቅርን ድልድይ እየገነባሁ እንድኖር እርዳኝ።

ጌታ ቢፈቅድ ከነገ ወዲያ እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ!!

ባይሣ ገመቹ
ሐምሌ 21 , 2014

ⒶⓇⓉⒾⓄⓈ
ⒶⓇⓉⒾⓄⓈ

ይ ላ ሉን
@artios_media
@artios_media
@artios_media
ይ ላ ሉን