2022-07-13 23:07:55
ሐምሌ 7 -- በዓለ አጋእዝተ ዓለም ቅድስት ሥላሴሥላሴ የሚለው ሠለሰ - ሦስት አደረገ ከሚለው የግዕዝ ሥርወ ቃል የተገኘ ሲሆን ሦስት (ሦስትነት ) ማለት ሲሆን በያዘው ምሥጢር ግን አንድም ሦስትም / አንድነት ሦስትነት ተብሎ ይተረጎማል ።
ሦስትነታቸው በስም ፣በአካል፣ በግብር አንድነታቸው በባሕርይ ፣ በህልውና በመለኮት ፣ በሥልጣን በፈቃድ ነው ።
ሀ,የስም ሦስትነት - አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ብሎ ነው ማቴ 28 ፣ 19
ለ, የአካል ሦስትነት - ለአብ ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፣ ለወልድም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፣ ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ አለው።
አካል ከራስ ፀጉር እስከ እግር ጥፍር ያለው ነው ። ገጽ ፊት ነው መልክም ከራስ ፀጉር እስከ እግር ጥፍር ያለ ነው
አካልም እንዳላቸው ሲያጠይቅ መዝ 33 ፥ 15, መዝ 118+73
ኢሳይያስም '' ሰማይኒ መንበርየ ወምድርኒ መከየደ እገርየ '' ብሏል (ኢሳ 66 + 1 ) ለአብርሃም በመምሬ አድባር ዛፍ ሥር ለዮሐንስ በዮርዳኖስ ተገልጸዋል ። ዘፍ 18+ 1-4, ማቴ 3+16
ሐ, የግብር ሦስትነት፦ የአብ ግብሩ መውለድ ማሥረጽ ፣ የወልድ ግብሩ መወለድ ፣ የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ መሥረጽ ነው ። አብን ወላዲ ፣ ወልድን ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስንም ሠራጺ ስላልን የሚበላለጡ አይደለም አንድ ናቸው ። እንዲህም ማለት ሦስት አማልክት ማለት አይደለም ። አንድ አምላክ ይባላሉ እንጂ
የአንድነታቸውስ ነገር እንደምን ነው ? ቢሉ በባሕርይ በህልውና በመለኮት በሥልጣን በፈቃድ አንድ ናቸው የህልውና አንድነታቸው በአብ ልቡናነት ወልድ መንፈስ ቅዱስም ያስቡበታል፤ በወልድ ቃልነት አብ መንፈስ ቅዱስም ይናገሩበታል ። በመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስነት አብ ወልድም ህልዋን ናቸው ይተነፍሱበታል ።
ቅድስት ሥላሴ የሚል የሴት ቅጽል የተቀጸለላቸው ባሕርያቸውን አይቶ ነው ። ልጅ ከእናቱ ባሕርይ እንዲገኝ ይህም ዓለም ከሥላሴ ባሕርይ ተገኝቷልና ፤ እናት ለልጅዋ የሚያሻውን አስባ እንድታቀርብለት ሥላሴም ለፍጥረት ሁሉ የሚያስፈለገውን ሁሉ አስቀድመው ያዘጋጁለታል። ማቴ 6 +32 አንድም እናት ልጅዋ ቢያስቀይማት ፈጽማ እንዳትጥለው ሥላሴም ሰርቀው አመንዝረው ቢበድሏቸው ንስሐ ገብተው ቀኖና ይዘው ቢለምኗቸው ይቅር ይላሉና ። ማቴ 6 +32
ይህን የሥላሴ አንድነት ሦስትነት ካልተማሩ ሥርየተ ኃጢአት ተስፋ መንግሥተ ሰማያት አይገኝምና ፤ ይህንንም ምሥጢር ያፋለሰ ለየራሳቸው ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ አላቸው ዘጠኝ አማልከት ናቸው ። እንዳለው እንደ ዮሐንስ ተዐቃቢ ፍዳን ይቀበላልና ፈጽሞ ጠንቅቆ መረዳት ይገባል ።
ሥላሴ የሚታየውንና የማይታየውን ሁሉ ካለ መኖር ወደ መኖር አምጥተው የፈጠሩ ድካም የማይሰማቸው በሞት የማይለወጡ ገዥ ፈጣሪ ናቸው ። ሥላሴ እንደዛሬ ሁሉ ዓለም ሳይፈጠር አስቀድሞ ባሕርያቸው ባሕርያቸውን ሲያመሰግን ይኖር ነበር ኋላ ግን ሰውና መላእክትን ስማቸውን ለመቀደስ ክብራቸውን ለመውረስ ፈጠሩ። ሌላውን ገን ለአንክሮ ለተዘክሮ ለምግበ ሥጋ ለምግበ ነፍስ ፈጥረውታል።
የበዓሉ ታሪክ አብርሃም ቤቱን ከተመሳቀለ ጎዳና ሠርቶ የወጣ የወረደውን ያለፈ ያገደመውን እንግድነት ሲቀበል ይኖር ነበር ። ሰይጣን ለምቀኝነት አያርፍምና ራሱን ገምሶ አጥንቱን ከስክሶ ከመንገድ ቆይቶ እንግዶቹን ወዴት ትሄዳለችሁ ? ይላቸዋል ። ርቦን ሊያበላን ጠምቶን ሊያጠጣን ከአብርሃም ዘንድ ይሉታል ፤ የወትሮው አብርሃም መሰላችሁን እኔም እንደ እናንተ ርቦኝ ያበላኛል ጠምቶኝ ያጠጣኛል ብዬ ብሄድ ራሴን ገምሶ አጥንቴን ከስክሶ ሰደደኝ ይላቸዋል ፤ እያዘኑ በመጡበት ይመለሳሉ ። እንዲህ አድርጎ 3 ቀን ሙሉ እንግዳ ከለከለበት እሱም ያለምስክር ግብር አላገባም ብሎ ሳይመገብ ቆይቷል ።
በሦስተኛው ቀን በቀትር ከድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ ሥላሴ በመምሬ አድባር ዛፍ ሥር ተቀምጠው ታዪት። ( ዘፍ 13 + 18 ) '' ገሀሡ አጋዕዝትየ ቤተ ገብርክሙ አብርሃም '' ጌቶቼ ከቤት ገብታችሁ እረፉ አላቸው ። ደክሞናልና እዘለን አሉት ። አንዱን አዝሎ ቢገባ ሁለቱ በግብር አምላካዊ ገብተው ተገኝተዋል ። እሱም ሦስት እንደሆኑ አውቆ ሣራን 3 መስፈሪያ ዱቄት ወስደሽ አንድ እንጎቻ አድርገሽ ጋግሪው አላት ፤ ጋግራ አቀረበች ፤ እርሱም ወይፈን አርዶላቸው ወተት እርጎ ጨምሮ አቅርቦላቸው ተመግበዋል / አቅረበ ሎሙ ሐሊበ ዕቋነ ወዕጉለ ላሕም / እንዲል ። መብላቸው ግን አሳት ቅቤ በላ እንደ ማለት ነው ። ይህንንም ሲያጠይቅ አርዶ አወራርዶ ያቀረበው ወይፈን ተነሥቶ '' ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ '' ብሎ አመስግኗል ። '' ድኅረ በላዕክሙ ላሕመ እንበይነ ፍቅረ ሰብእ ፍጹም ፤ ዘበኃይልክሙ ሐይወ ላሕም ፤ ሥላሴ ክቡራነ ስም '' እንዳለ ደራሲ።
በሚሄዱም ጊዜ ከሦስቱ አንዱ እግዚአብሔር ቃል አመ ከመ ዮም እገብእ ኀቤከ ፤ የዛሬ ዓመት እንደዛሬ ወዳንተ እመለሳለሁ ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልዳለች ብሎ ለጊዜው ልደተ ይስሐቅን ፍጻሜው ግን ሰው ሆኖ የሚያድነው መሆኑን ነግሮታል ። ዘፍ 18 + 1- 14
ምንጭ ፦ መዝገበ ታሪክ 1 & 2
128 views20:07