#ባሕራን
ባሕራን ማለት ከባሕር የተገኘ ማለት ነው፡፡ የባሕራን ሕይወት፣ መኖር፣ ክብር፣ ታሪክ ከመጀመሪያው ጀምሮ እስከ ዕለተ ዕረፍቱ ድረስ ያለው በመላእክት አለቃ በቅዱስ ሚካኤል ተአምር ላይ የቆመ ነው፡፡
ይህም በመጽሐፈ ስንክሳር እንደተጻፈው በሰኔ 12 ቀን ይዘከራል፡፡ በአንዲት አገር እግዚአብሔርን የሚፈራ ደግ ክርስቲያን ሰው ነበረ፡፡ በየወሩም የቅዱስ ሚካኤልን ዝክር አያቁዋርጥም ነበር፡፡ በተለይም ኅዳር 12 ቀን እሥራኤልን ከምድረ ግብጽ መርቶ መና እያወረደ ውኃ እያፈለቀ በምደረ በዳ የመገባቸውን፣ ቀን በዓምደ ደመና ሌሊት በዓምደ ብርሃን እየመራ የለበሱት ልብስና የእግራቸው ጫማ ሳያልቅ፣ ከጠላቶቻቸው እየሰወራቸው እና ድልን እንዲቀዳጁ አደረገ አርባ ዓመት ሙሉ በመንገዳቸው የጠበቃቸውን፣ የመራቸውን፣ የረዳቸውን፣ የመገባቸውን እያሰበ በቃል ኪዳኑ ታምኖ፣ ድኆችን በቤቱ ሰብስቦ ይዘክር ነበር፡፡
እንዲሁም በሰኔ 12 ቀን ስለ ሰው ልጆች በአምላክ ዙፋን ፊት ቀርቦ ከእሳት መጋረጃው ውስጥ ገብቶ ምህረትን የሚለምንበትን ቀን አስቦ ዝክሩን በደማቅ ሥነ ሥርዓት ያደርግ ነበር፡፡
የሚሞትበትም ቀን በደረሰ ጊዜ ለሚስቱ ይህንን መልካም ሥራ እንዳታቁዋርጥ ወር በገባ በ12 ዝክሩን እንድታደርግ በተሌም ዓመታዊ በዓሉን ባላት ነገር መታሰቢውን እንድታደርግ እና እርሱ በአካለ ሥጋ ቢለያትም ቅዱስ ሚካኤል በነገር ሁሉ እንደሚረዳት ጎረቢታቸው ባለጸጋው ሰው በሀብቱ እየተመካ ይተናኮላቸው ስለነበር የእርሱን ክፋት የእነሱን መልካምነት የሚውቅ እግዚአብሔር እንደሚጠብቃት፣ ቅዱስ ሚካኤልም እንደማይለያት እና እንደሚረዳት አስተምሮዋት በክብር አረፈ፡፡ እሱ ካረፈ በኋላ ጠቂት እንደቆየች ማርገዙዋን አወቀች፤ ከመሞቱ በፊት ፀንሳ ነበርና፡፡ የመውለጃዋ ጊዜም ደርሶ በምጥ ተጨንቃ ሳለች ረዳቴ ቅዱስ ሚካኤል ሆይ ተጨንቄአለሁና ድረስልኝ ካንተ በቀር ሌላ የሚያጽናናኝ ወገን ዘመድ የለኝምና ባሌ ሲሞት የሰጠኝ ዋስ ጠበቃዬ እንተ ብቻ ነህ ብላ ለመነች፡፡
ቅዱስ ሚካኤልም ልመናዋን እንዳቀረበች እንደ ዓይን ጥቅሻ ፈጥኖ ደረሰና ያለችበትን ቤቱን በብርሃን መላው፡፡ ወዲያውኑ በሰላም ወንድ ልጅ ወለደች፡፡ እጅግ ደስም አላት መልአኩም ደስ የሚያሰኝ የሚያጽናና ድምጹንም አሰማት፡፡ እንዲህም አላት አይዞሽ ይህ ያማረ ልጅሽ ባጠገብሽ ያለውን የባለጸጋውን ሀብት ሁሉ ይወርሳል፡፡ አንቺም ከድህነት ኑሮ ትላቀቂያለሽ ሙሉ ሀብቱን ንብረቱን ባሪያዎቹን ሳይቀር ትወርሳላችሁ ደስ ብሏችሁም በሰላም ትኖራላችሁ አላት፡፡
ይህንን ሲል የመልአኩን ድምጽ ያ ክፉና ጨካኝ ባለጸጋ ሰምቶ ስለ ነበረ ተጨነቀ፡፡ ህጻኑም ጡት በተወ ጊዜ ያ ባለጸጋ ልጅሽን ስጪኝና እኔ ሀብት ስላለኝ ነገር ግን ወንድ ልጅ ስለሌለኝ ላሳድገው ላንቺም ሃያ ወቄት ወርቅ እሰጥሻለሁ ይላታል እሷም ስለ ሃያ ወቄት ወርቁ ደስ ብሏት ልጁዋን ሰጠችው እሱ ግን በቁመቱ ልክ ሳጥን አሰርቶ በሌሊት ባሪያዎቹ ወስደው ከባህር እንዲጥሉት አደረገ፡፡
ያ ሳጥን ለሃያ ቀናት ጉዞ ያክል እያንሳፈፈ ወስዶ ካንዲት አገር ወደብ ዳርቻ ተፋው፡፡
በዚም በጎች የሚጠብቅ አንድ ሰው ባሕር የተፋውን ሳጥን አየና ወደ ቤት ወሰደው፡፡
ሳትኑ ተቆልፎ ነበርና በምን ልክፈተው እያለ ሲያስብ ልቡናውን አሳሰበውና ሳጥኑን ከቤት አስቀምጦ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሄደ በዚያም ዓሣ የሚያጠምደውን በኔ ስም መረብህን ጣለውና የምትይዘውን ዓሣ ትሰጠኛለህ እኔም ዋጋውን እሰጥሃለሁ ይለውና ትልቅ ዓሣ በመረቡ ይያዛል፡፡
ዓሳውን ይዞም ወደ ቤቱ ገባ ማታም ለእራት ሊያዘጋጀው ዓሳውን ሲጠብስ በዓሳው ሆድ ቁልፍ አገኘ፡፡ ያንን ቁልፍ የሣጥኑን ቁልፍ ቢሞክርበት ከፈተለት በሣጥኑ ውስጥም ያን የሚያምር ልጅ በማግኘቱ እጅግ ደስ አለው፡፡ ቀድሞውንም ልጅ አልነበረውምና ያን የመሰለ ልጅ እግዚአብሔር እንደሰጠው እያሰበ ደስ ብሎት አሳደገው፡፡ ስሙንም ከባህር አግኝቼዋለሁ ሲል ባሕራን አለው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ያ በሳጥን አድርጎ በባሕር የጣለው ባለጸጋ ለንግድ ወደ ሩቅ አገር ሲጉዋዝ መሸበትና ወደ አንዲት መንደር ቀርቦ አሳድሩኝ መንገደኛ ነኝ ለማደሬም ጠቀም ያለ ገንዘብ እሰጣችኋለሁ ይልና ባሕራን እንደ ልጅ ሆኖ ካደገበት ቤት ለማደር ይፈቀድለትና ይገባል፡፡የቤቱ ባለቤትም ልጁን ባሕራን እያለ ሲጠራው ይሰማና እንዴት ልጅህን ስሙን ባህራን ብለህ አወጣህለት ይለዋል እሱም ከባህር ስላገኘሁት ነው ይልና ታሪኩን ያጫውተዋል፡፡
ያ በለጸጋም ይደነግጥና መቼ ነው ይህ የሆነው ይለዋል ከሃያ ዓመት በፊት እንደሆነ ሲነግረው የራሱ ጉድ እንደሆነ በማወቁ ሌሊቱን ሙሉ ሲጨነቅ ሲያስብ ያድራል፡፡ ሲነጋም ወደ አደረበት ቤት ባለቤት ቀረብ ይልና እባክህን ለሥራ የሚያስፈልገኝን ዕቃ ከቤቴ ረስቼ መጥቻለሁና ልጅህን ልላከው ለአንተም ሃያ ወቄት ወርቅ እሰጥሃለሁ፡፡ ለልጅህም የሚያስፈልገውን ሁሉ አደርግለታለሁ ይለዋል፡፡ እሱም ይፈቅድለትና ባሕራን ይጠየቃል፡፡ ባህራንም እጅግ ቅን እና ታዛዥ ልጅ ነውና እሺ ብሎ አባቱ እንዳለው ለዚያ ባለጸጋ ይታዘዛል፡፡
ባለጸጋውም “ይህ ባህራን የተባለ ልጅ ይህችን ደብዳቤ ይዞ እንደመጣ ወዲያው ሰው ሳያይ ግደሉትና ጉድጉዋድ ውስጥ ጣሉት የሚል ጽሑፍ ጽፎ እሱና የሀብቱ አሳዳሪ ብቻ የሚተዋወቁበትን የምሥጢር ምልክት ወይም ፊርማ አኑሮ ሰጠውና በመንገድ ላይ ማንም ቢያገኝህ ይህቺን ደብዳቤ እንዳታሳይ ይለዋል፡፡
ባህራንም ሲጉዋዝ ሰንብቶ ከተላከበት አገር ሊደርስ የአንድ ቀን ጉዞ ሲቀረው በንጉሥ ጭፍራ አምሳል በነጭ ፈረስ ላይ የተቀመጠ ጎልማሳ አገኘውና ሰላምታ አቀረበለት ባህራንም ሰላምታውን ተቀበለ ያ ጎልማሳም በእጅህ የያዝከው ምንድን ነው እስኪ አሳየኝ ይለዋል፡፡ባሕራን ግን መንገድ ላይ ለማንም አታሳይ ተብሎ ስለ ነበር ለጊዜው ለማሳየት ፈቃደኛ አልሆነም ነበር ነገር ግን ያ ጎልማሳ ደጋግሞ ስለጠየቀው እሺ በእጅህ ላ እንዳለ አሳየኝ አለውና ሲያሳየው እፍ ቢልበት ጽሑፉ ተለውጦ “ይህ ደብዳቤውን የያዘ ባሕራን የተባለ ልጅ እናንተ ጋር እንደደረሰ እና ደብዳቤውን እንዳነበባችሁት ወዲያውኑ አንድ ልጄን አጋቡት ሀብት ንብረቴን ሁሉ አውርሱት በባሪያዎቼ ላይ ሁሉ አዛዥ ይሁን እኔ ቶሎ አልመለስምና አትጠብቁኝ” የሚል ሆነ፡፡
ያ ጎልማሳም ባሕራንን ሞትህ በሕይወት ቀይሬልሃለሁና አሁን በሰላም ሂድ መልክትህን አድርስ ብሎት ተሰወረው፡፡ ባህራንም እንደ ታዘዘው ለማድረግ ወደ ተላከበት ቤት በተሰጠው ምልክትና አድራሻ መሠረት ገባ እንደገባም ደብዳቤውን አንብበው ደስ አላቸውና ድል ያለ ሠርግ ሠርገው የባለጸጋውን አንዲት ልጃገረድ ልጁን በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በሥርዓተ ተክሊል አጋቡት ሀብቱን ሁሉ አወረሱት በንብረቱ ሁሉ አዛዥ ናዛዥ ሆነ፡፡
አርባ ቀን ሙሉ ሲጨፈር ሲበላ ሲጠጣ ያ ባለ ጸጋ ከሄደበት ተመልሶ ወደ መንደሩ ሲቀርብ የከበሮ፣የእልልታ፣ የዝማሬ እንዲሁም ባህላዊ ሽለላ ይሰማና ምንድን ነው የምሰማው ብሎ ይጠይቃል፡፡ ደብዳቤ ጽፈህ ልጄን ዳሩለት ሀባቴንም አውርሱት ብለህ የላከው ልጅ እንዳዘዝከው ተድሮ ሀብትህን ሁሉ ወርሶ ይኸው ሲበላ ሲጠጣ ሲጨፈር ዛሬ አርባ ቀን ሞላው ብለው ነገሩት፡፡ እርሱም ደንግጦ ከፈረሱ ወድቆ በድንጋጤ ሞተ፡፡
@Amon0721
@Amon0721
@Amon0721
#ለተጨማሪ፦ https://t.me/Amon_0721