Get Mystery Box with random crypto!

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማሪታይም አካዳሚ ለ21ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 119 መርከበኞች አስመረቀ፡፡ | Amhara Media Corporation

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማሪታይም አካዳሚ ለ21ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 119 መርከበኞች አስመረቀ፡፡

ባሕር ዳር ፡ ግንቦት 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማሪታይም አካዳሚ ለ21ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 119 መርከበኞች አስመርቋል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው የምርምር እና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ተስፋየ ሽፈራው (ዶ.ር) አካዳሚው ከዚህ በፊት ሜካኒካል ኢንጅነሮችን ብቻ ያሰለጥን እንደነበር ጠቅሰዋል። በዚህ ዙር ስልጠና ግን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሰልጣኞችን አካቶ አስመርቋል ብለዋል።

በጣና ሐይቅ ላይ ልምምድ አድርገው ወደ ዓለም አቀፉ የመርከብ ቢዝነስ የሚቀላቀሉ ተመራቂዎች በሄዱበት ሁሉ በሥነ ምግባር እና በተግባቦት በመሥራት ሀገራቸውን እንዲያስመሰግኑ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ማሪታይም አካዳሚ ማኔጅንግ ዳይሬክተር ፍራንስ ጆበርት በበኩላቸው የዛሬ ተመራቂዎች በየትኛውም ዓለም ተጉዘው ለመሥራት የሚያስችላቸውን ዕውቀት እና ክህሎት ይዘው ስለመውጣታቸው ተናግረዋል።

ተመራቂዎች ወደ አዲስ ሀገር እና ሕዝብ ሲቀላቀሉ ቤተሰብ፣ ሀገር እና የኢትዮጵያ ጣፋጭ ምግቦች ሳይቀሩ እንደሚናፍቋቸው የገለጹት ፍራንስ ጆበርት ይህንን በትዕግስት በማለፍ ኢትዮጽያዊ ጀግንነት እንዲፈጽሙ መልዕክት አስተላልፈዋል። ሀገራቸውን ሳይረሱ ጠንክረው በመሥራት የራሳቸውን እና የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ ማሻሻል እንዳለባቸውም መክረዋል።

ተመራቂዎች ወደ ተለያዩ የውጭ ሀገራት በሚኖራቸው የሥራ ስምሪት ሀገር እና ሰንደቅ ዓላማቸውን የሚያስከብር ተግባር የሚፈጽሙ እንደሚኾኑም አመላክተዋል።

ከተመራቂዎች መካከል መርከበኛ ሄኖክ ገበያ ለትምህርቱ ከፍተኛ ፍላጎት ይዞ በመግባቱ የላቀ ውጤት አስመዝግቦ ነው የተመረቀው። በኤሌክትሮ ቴክኒካል ኦፊሰርነት እንደተመረቀ ነግሮናል። ስልጠናው ከዕውቀት በተጨማሪ በሥነ ምግባር እና በሌሎች ክህሎቶችም ታንጾ ለመውጣት አስችሎኛል ብሏል። በተመደበበት ቦታ ሁሉ የሀገሩን ስም እና ክብር በጠበቀ መልኩ እንደሚሠራም ገልጿል።

ሌላው ተመራቂ መርከበኛ ይዲዲያ አዲስ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ከፍተኛ ልምድ ባካበቱ መምህራን ጥራት ያለው ትምህርት ማግኘቱን ተናግሯል። ከዕውቀት በተጨማሪ የተሻለ አካላዊ ቁመና እና ስብዕና ይዞ ለመውጣት እንደቻለም ገልጿል። ያገኘውን ዕውቀት እና ክህሎት ወደ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይዞ በመግባት ራሱን፣ ቤተሰቦቹን እና ሀገሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥራ እንደሚያከናውን ተናግሯል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
ዲስከቨር አማራ አሚኮ https://www.facebook.com/DiscoverAmharaAMECO
አሚኮ ስፖርት https://www.facebook.com/AMECOSport
አሚኮ እውነታ ማጣሪያ https://www.facebook.com/AMECOFactCheck