Get Mystery Box with random crypto!

የስራ ማቆም አድማዋን ገዥዎቹ ይፈልጓታል! ብዙ ጊዜ የስራ ማቆም አድማ ወዘተ ጥሪ ወረቀት ፌስቡክ | አማራ ሚዲያ ማዕከል Amhara media center

የስራ ማቆም አድማዋን ገዥዎቹ ይፈልጓታል!

ብዙ ጊዜ የስራ ማቆም አድማ ወዘተ ጥሪ ወረቀት ፌስቡክ ላይ አያለሁ። ገዥዎቹ ለይምሰል ይቃወሙት ይሆናል እንጅ የሚፈልጉት ነው። በተለይ ያልተደራጀና ያልተጠና ከሆነ።

1) ገዥዎቹ ራሳቸው ህዝብ ስራ እያስፈቱ ነው። ጉዳያቸው አይደለም ባይሰራ። መንገድ ዘግተው ወደስራ እንዳይሄድ ሲከለክሉ ከርመዋል። ማዳበሪያ አያቀርቡ፣ ሲሚንቶ ከነጋዴ ጋር ተመሳጥረው በህገወጥ እየሸጡ ሌላውን ስራ አጥ አድርገውታል። በሶስት አመት ያልቃል የተባለ ግድብ 12 አመት የሞላው አለ። ፋብሪካዎቹ ስራ አቁመዋል። በሚቀጥለው አመት ደግሞ ተመራቂ አንቀጥርም ብለዋል። መስርያ ቤት ስራ የለም። ሄደህ ማየት ነው።ገዥዎቹ በኢትዮጵያ ላይ የስራ ማቆም አድማ ካወጁ ቆይተዋል። ብትሰራ ባትሰራ ጉዳያቸው አይደለም።

2) ወደ አገር ቤት የምትላከውን ትንሽ ዶላር ለራሳቸው አድርገዋል። ገንዘብ ጠፍቷል። አቅርቦት የለም። ነዳጅ በለው ስኳር ማቅረብ እየቻሉ አይደለም። ዘይት በለው ዱቄት ከቀን ቀን እየተወደደ ነው። ሱቅ ብትዘጋላቸው፣ ሳምንትና ወር ፀጥ ረጭ ብትል እረፍት የሰጠሃቸው ነው የሚመስላቸው። ችግሩ አንተ ባወጅከው የመጣ አድርገው፣ የአቅርቦት ጉዳይ ሳያስጨንቃቸው እረፍት ነው የሚወስዱበት።

3) የስራ ማቆም አድማ ስታደርግ ከአደባባይ ትጠፋለህ። ገዥዎቹ የሚፈሩት አደባባይ መውጣትን እንጅ ቤት ከተቀመጥክማ ደስታቸው ነው። ህዝብ የቤት ቁልፍ ቢሰጣቸው ዘግተውበት ቢጠፉ በወደዱ።

4) የስራ ማቆም አድማ የሚጎዳው ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ውስጥ ያለውን ነው። አብዛኛውን ህዝብ ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ ህዝብ የስራ ማቆም አድማ የጠራውን ያማርራል ማለት ነው። አሊያም ገዥዎቹ አድማ የጠሩት እንዲጠሉ ያደርጋሉ። ለኢኮኖሚ ምስቅልቅል የዳረገው ገዥው ሆኖ ህዝብን ያስራበው የሶስት ቀን አድማ አድርገው ያቀርቡልሃል። በጅራፍህ ትገረፋለህ ማለት ነው። ነፃ አወጣዋለሁ ባልከው ህዝብ ዘንድ ፖለታካ ይሰሩብሃል።

5) በተለይ ባልተቀናጀ መልኩ ሲደረግ ሌላ ቀን አዋጭና አስፈላጊ ሲሆን ቢጠራ ህዝብ ከቁም ነገር እንዳያየው፣ ስልቱን እንዲሰለቸው፣ ትግሉን እንዲርቀው ያደርጋል።

6) ዋናዎቹ ገዥዎቹ አማራ ክልል በኢኮኖሚ ድቅቅ እንዲል ይፈልጋሉ። ስራ አቁሞ ቢከርም አድማ የጠራውን አካል ያመሰግኑታል። ህዝብ ትግሉን ሊያግዝ የሚችለው ደግሞ ገንዘብ ሲኖረው ነው። ሌላው በህገወጥ መንገድ ስራ እየሰጠ፤ አማራው ባለችውም ዘግቶ ከዋለ ለጠላቶቹ አዋጭ ነው።

7) ትግል ጊዜን ይጠይቃል። ተማሪዎች ለአመታት የደከሙበት ፈተና የሚፈተኑበት ወቅት ላይ "የትምህርት ማቆም" ተብሎ ስልት ከታጋይ ይሁን ከገዥዎች የመጣው ግራ የሚያጋባ ነው።

ከዚህ ይልቅ የተቃውሞ ምንጩ ግራ እስኪገባቸው ድረስ ሊደረጉ የሚችሉ ስልቶች አሉ። በርካቶች ናቸው። ትግል የሚመራ አካል ስልቶቹን በደንብ አይቶ መርጦ፣ ጉዳትና ጥቅማቸውን አይቶ መሆን አለበት።

ህዝብ በቀላሉ የሚቀባበለው፣ ለሚዲያ ግቡ የሆነ፣ ሰው አይቶት ምልክት የሚያደርገው፣ ፋሽን የሚያደርገው፣ የፀጥታ ኃይሉ ህገወጥ ነው አይደለም ብሎ የሚወዛገብበት፣ ቢከለክል ከህዝብ ጋር የሚጣላበት ስልት ሞልቷል። ከዚህ ላይ ልፃፈው? አልፅፈውም! እንደዛ አይደረግም!