Get Mystery Box with random crypto!

በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የማክሰኞ ገበያ ወረዳ ነዋሪዎች የወሰንና ማንነት ጥያቄዎች በአ | አማራ ሚዲያ ማዕከል Amhara media center

በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የማክሰኞ ገበያ ወረዳ ነዋሪዎች የወሰንና ማንነት ጥያቄዎች በአስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጣቸው ለዓለም ማኅበረሰብ ድምፃቸውን አሰሙ።

የአማራ ሚዲያ ማዕከል
ግንቦት 27 2016 ዓ/ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

በሰልፉ ላይ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የወረዳው ሰላም አስከባሪዎች፣ ወጣቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ኹነዋል።

ባለፉት ዓመታት የወልቃይት ጠገዴ ነዋሪዎች በአማራ ማንነታቸው ምክንያት እስራት፣ ግርፋትና ሞት እንዲሁም ለሰው ልጅ የማይገባ እንግልት ሲደርስባቸው መቆየቱን በሰልፉ ላይ መልእክት አስተላልፈዋል።

የወልቃይት ጠገዴ የወሰንና የማንነት ጥያቄውን የፌደራል መንግስት በህግ ሊያረጋግጥልን ይገባል ሲሉ ለዓለም ማኅበረሰብ ድምፃቸውን አሰምተዋል።

የማክሰኞ ገብያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ጌታሁን ብርሀኔ በሕዝባዊ ሰልፉ ላይ ባስተላለፉት መልእክት፤ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ከደረሰበት ግፍና በደል አንፃር ሲታይ በሰው ልጅ ታሪክ ተፈፅሞ የማያውቅ ወንጀል የተፈፀመበት ሕዝብ መሆኑን ገልፀዋል። ለዚህ ሕዝብ ካሳና ይቅርታ በቂ እንኳን ባይሆንም ቅሉ ጉዳዩን ወደ ጎን በመተው በቁስል ላይ እንጨት እንደመስደድ ያክል የሚቆጠር ድርጊት አሁንም እየተፈፀመ ይገኛል ብለዋል።

የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ጥያቄ ማንነቴ አማራ ነው እንጂ አማራ ልሁን የሚል ጥያቄ አይደለም ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ የፌደራል መንግስ እስካሁን ድረስ በጀት ሳይመድብ ቢቆይም ሃብታችንና በጀታችን ማንነታችን ነው ብሎ በርካታ ችግሮችን ተቋቁሞ መቆየቱን ገልፀዋል።

ትላንት በጦርነት ወደነበረበት የበጌምድር አማራ የተመለሰውን የወልቃይት ጠገዴ የወሰንና የማንነት ጥያቄ የፌደራል መንግስት በህግ ሊያረጋግጥልን ይገባል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ንፁህ የትግራይ ተወላጆች አሁንም ድረስ በወልቃይት ጠገዴ ምድር በሰላም እየኖሩ መሆኑ እየታወቀ ግን የትግራይ ተወላጆች ከወልቃይት ጠገዴ ተፈናቅለዋል የሚባለው ከእውነት የራቀ ሀሳብ ነው፤ ይልቁንስ ገዳዮችና ጨፍጫፊዎች እኩይ ሥራቸውን ፈፅመው መሄዳቸውን የማይካድራው የንፁሀን ጅምላ ጭፍጨፋ ዋና ማሳያ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳች መምሪያ ኃላፊ አቶ ገብረዮሐንስ የሺነህ በበኩላቸው ሰልፉ በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች በዛሬው እለት መካሄዱን ገልፀው ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በህወሀት የጭቆና አገዛዝ ስርዓት የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የደረሰበትን ግፍና በደል ለዓለም ማኅበረሰብ ማሳየት የሰልፉ ዓላማ እንደሆነ ተናግረዋል።

የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በማንነቱ ምክንያት ተዘርዝረው የማያልቁ በደሎች ደርሰውበታል ያሉት ኃላፊው ንፁህ የወልቃይት አማራዎች በማንነታቸውና በያዙት እውነተኛ አቋም ምክንያት ተጨፍጭፈው ሳለ በእኛ ሞት ገዳዮች እንደሞቱና እንደተጎዱ ተደርጎ የሚወራው ሀሰተኛ መረጃ መሆኑን ሊታወቅ እንደሚገባ ገልጸዋል። በታሪክ ሂደት "ወልቃይት ጠገዴን የትግራይ አንድ አካል መሆን ቀርቶ የወልቃይት ጠገዴን ሕዝብ አንድም የትግራይ ገዥ አስተዳድሮት አያውቅም ወደፊትም ቢሆን የማይታሰብ የቁም ቅዥት መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል" ሲሉ አሳስበዋል።

የወልቃይት ጠገዴ የወሰንና ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ደምለው ጀጃው እንደተናገሩት የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ ከ1985 ጀምሮ የነበረ የበርካቶች ንፁሀን ሕይዎት የተገበረበት እንደሆነ ተናግረዋል። የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በትግል አማራዊ ማንነቱን አረጋግጧል ያሉት አቶ ደምለው፤ አሁንም ቢሆን መንግስት የሕዝቡን የማንነትና የወሰን እንዲሁም የበጀት ጥያቄዎች በአፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል።

የሰልፉ ተሳታፊ የሆኑት መላከ ሰላም አዳነ ከፍያለው እንደተናገሩት የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ አማራዊ ማንነት እንዳለው እየታወቀ እስካሁን ድረስ በግዴታ ማንነቱን ተቀምቶ ቆይቷል፤ አባትና እናቴን የማውቀው እኔ ባለቤቱ እያለሁ ሌላ ማንነት በኃይል ተቀበል የሚለኝ አካል ሊኖር አይችልም ሲሉ ተናግረዋል።

እኛ ወልቃይት ጠገዴዎች እንግዳ ተቀባይ እንጅ በቤታችን ሌላ አዛዥና ፈትፋች እንዲኖር አንፈቅድም ያሉት መላከሰላም አዳነ ከፍያለው እስካሁን ልብሳችንን አጥፈን ለብሰን መቆየታችን መንግስት የማንነትና የበጀት ጥያቄያችንን ሳይመልስን የመቆየቱ ምሳሌ ነውና አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠን ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን የጠገዴ ወረዳ መረጃ ያመላክታል።

አሚኮ ይህን ዘገባ ከገፁ አጥፍቶታል።