Get Mystery Box with random crypto!

«የኢትዮጵያ መንግስት የመገናኛ ዘዴ ባለሙያዎችን ይልቀቅ» አምንስቲ የአማራ ሚዲያ ማእከል ሚያዚያ | አማራ ሚዲያ ማዕከል Amhara media center

«የኢትዮጵያ መንግስት የመገናኛ ዘዴ ባለሙያዎችን ይልቀቅ» አምንስቲ

የአማራ ሚዲያ ማእከል
ሚያዚያ 10 2015 አ/ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዉሞን በሰላማዊ ሰልፍ የመግለፅ መብትን እንዲያከብርና የታሰሩ የመገናኛ ዘዴ ባለሙያዎችን እንዲፈታ አምንስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ።

ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ትናንት ማምሻ ባወጣዉ መገለጫ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ባለፈዉ ሳምንት አማራ ክልል በተፈጠረዉ “ሁከት “ምክንያት ያሰሯቸዉን 7 የመገናኛ ዘዴ ባልደረቦች ባስቸኳይ እንዲፈቱ፣ ከእስረኞቹ ባንዷ ላይ ተፈፀመ የተባለዉን አካላዊ ጥቃት እንዲያጣሩ ጠይቋል።መግለጫዉ እንዳለዉ ባለስልጣናቱ «ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትንና ሁሉም ወገን በሰላማዊ መንገድ የመቃወም መብቱን ማስከበር አለባቸዉ።»

ባለፈዉ ሳምንት በአማራ ክልል የመብት ጥሰትና ሁከት መቀስቀሱ እንዳሳሰበዉ የመብት ተሟጋቹ ድርጅት አስታዉቋል።በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተኩስ ልዉዉጥ መደረጉ፣ የሰብአዊ ርዳታ አቀባይ ድርጅት ሰራተኞችን ጨምሮ ሰዎች መገደላቸዉ፣ አዲስ አበባ ዉስጥ ሰዎች በጅምላ መታሰራቸዉንም ድርጅቱ «አሳሳቢ» ብሎታል።

የመንግስት ኃይላትም ሆኑ ሌሎች ታጣቂዎች «የሰብአዊ ርዳታ ሰራተኞችን ያለማጥቃት ኃላፊነት አለባቸዉ።» ይላል መግለጫዉ።የኢትዮጵያ መንግስት «አስቸኳይ፣ጥልቅ፣ገለልተኛና ዉጤታማ ምርመራ አድርጎ ተጠያቂዎችን ለፍርድ ማቅረብ አለበት» እንደ መግለጫዉ።

በምስራቅ አፍሪቃ፣በአፍሪቃ ቀንድና በታላላቅ ሐይቆች አካባቢ የአምንስቲ ኢንተርናሽናል ምክትል ተጠሪ ፍላቪያ ምዋንጎቭያ «ዘግናኝ» ያሉት የገነት አስማማዉ፣ ጌትነት አረጋዊ፣አራጋዉ ሲሳይ፣መስከረም አበራ፣አባይ ዘዉዱ፣ ዳዊት በጋሻዉና ቴዎድሮስ አስፋዉ መታሰር ሐሳብን በነፃነት በመግለጥ መብትና በመገናኛ ዘዴ ነፃነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ነዉ።የኢትዮጵያ ባለስልጣናት 7 የመገናኛ ዘዴ ሰራተኞች ባስቸኳይ እንዲለቁና የተመሰረተባቸዉን ክስ እንዲነሱም ምዋንጎቭይ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በተመረጡ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የጣለዉን ማዕቀብ እንዲያነሳም ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ጠይቋል።አምንስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚለዉ የኢትዮጵያ መንግስት እገዳዉን ከጣለ 3ኛ ወሩን ይዟል።እገዳዉ ሰዎች መረጃ እንዳያገኙ መገደብን ጨምሮ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን የመጠቀምና ያለመጠቀም የሰብአዊ መብትን የሚጥስ ነዉ ሲል DW ዘግቧል::