Get Mystery Box with random crypto!

መንግሥት እና ሕወሓት በአስቸኳይ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን እንዲያቆሙ አሜሪካ ጥሪ አቀረበች አ | Amba Digital - አምባ ዲጂታል

መንግሥት እና ሕወሓት በአስቸኳይ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን እንዲያቆሙ አሜሪካ ጥሪ አቀረበች

አምባ ዲጂታል፤ ሐሙስ ነሐሴ 26፣ 2014 ― መንግሥት እና ሕወሓት በአስቸኳይ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን እንዲያቆሙ አሜሪካ ጥሪ ያቀረበችው በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊዋ አንቶንዮ ብሊንከን በኩል ነው፡፡

ብሊንከን በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ማስታወሻ፤ ተፋላሚ ወገኖች ወታደራዊ እንቅስቃሴውን አቁመው ግጭቱን በዘላቂነት ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

ያለፉትን ወራት በተደረገው የተኩስ አቁም ስምምነት ጋብ ብሎ የቆየው የፌዴራል መንግሥት እና ሕወሓት ጦርነት ካገረሸ ዘጠኝ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ በትዊተር የጻፉት አንቶንዮ ብሊንከን፤ ‹‹ጦርነቱ እንደገና መቀስቀሱ እና አደጋ ላይ የሚጥለው የሰው ሕይወት በእጅጉ ያሳስበናል›› ብለዋል።

ተባብሶ በቀጠለው ጦርነት መንግሥት ትላንት ነሐሴ 25፣ 2014 ባወጣው መግለጫ፤ ሕወሓት በወልቃይት አቅጣጫና በሱዳን ድንበር እንዲሁም በዋግ ጥቃት መክፈቱን ገልጧል፡፡ በአንጻሩ የሕወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ መንግሥት ከኤርትራ ጦር ጋር በመሆን በሰሜን ምዕራብ ትግራይ በኩል አድያቦ አካባቢ ዛሬ ነሐሴ 26፣ 2014 ማለዳ በአራት አቅጣጫ ጥቃት እንደከፈቱባቸው ገልጸዋል፡፡
የአቶ ጌታቸውን ክስ በተመለከተ ከመንግሥት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡ ሆኖም የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ 26 ‹‹ሕወሓት ወረራውን እያስፋፋ መጮሁን ቀጥሎበታል›› በሚል ርእስ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በዚሁ መግለጫ ላይ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን ገፍቶ በለኮሰው እና ዛሬም እያስፋፋው ባለው እሳት ንጹሐን እየተገደሉ ነው፤ ሕዝብ እየተፈናቀለ እና ንብረትም እየወደመ ነው ያለው መንግሥት፤ ‹‹ሕወሓትን ከአገር አጥፊነት ተግባሩ የማስቆም ግዴታ በኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ላይ ወድቋል›› ሲል አስፍሯል፡፡

በሌላ በኩል መንግሥት በዚሁ መግለጫ ላይ ለሰላማዊ አማራጮች ያደረግኳቸው ጥረቶች ‹‹እየመከኑ ባሉበት ሁኔታ›› ሕወሓትን መጫን ሲገባቸው ‹‹ሁለቱ ወገኖች›› በሚል የሚወጡ መግለጫዎችን ‹‹ከእውነታው ያፈነገጡ በመሆናቸው›› ተቀባይነት የላቸውም ብሏል፡፡

ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ የሚገኘውን የመከላከያ የሰሜን እዝ መመታት ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት የአስር ሺሕዎችን ሕይወት በመቅጠፍ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን አፈናቅሏል፡፡