Get Mystery Box with random crypto!

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር በፀጥታ ስጋት ምክንያት አዳዲስ ውሳኔዎችን አሳለፈ አምባ ዲጂ | Amba Digital - አምባ ዲጂታል

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር በፀጥታ ስጋት ምክንያት አዳዲስ ውሳኔዎችን አሳለፈ

አምባ ዲጂታል፤ ማክሰኞ ነሐሴ 24፣ 2014 ― በአማራ ክልል የሚገኘው የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር በፀጥታ ስጋት ምክንያት አዳዲስ ውሳኔዎችን ያሳለፈው በፀጥታ ምክር ቤቱ አማካኝነት ነው፡፡

በዚህም በከተማ አስተዳደሩ በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚኖር ተፈናቃይ ከምሽቱ 12 በኋላ ወደ መጠለያ ጣቢያውም ሆነ ወደ ከተማው መግባት ክልክል የተደረገ ሲሆን፣ በከተማው የሚገኙ የባጃጅ ተሽከርካሪዎች ደግሞ ከምሽቱ በኋላ መንቀሳቀስ እንደማይችሉና ይህን ሲያደርግ የተገኘ ባለባጃጅ ህጋዊ እርምጃ ይወሰድበታል ተብሏል፡፡

በተጨማሪም በከተማው የሚገኙ መጠጥ ቤቶች ምግብ ቤቶች ምሽት ጭፈራ ቤት እስከ ምሸት 2 ሰአት ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ የወሰነው ምክር ቤቱ፤ በከተማው የሚገኙ የንግድ ቤቶች የምርት የዋጋ ጭማሪ ማድረግን በጥብቅ ከልክሏል፡፡

የጦር መሣሪያን በተመለከተም ከተፈቀደላቸው የፀጥታ ኃይሎች ውጭ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ ፈፅሞ ተከልክሏል፡፡ በከተማው ከመንግስት ዕውቅና ውጭ የሚደረጉ ማናቸውም አይነት ውይይቶችና ስብሰባ ማድረግ በጥብቅ ተከልክሏል፡፡

በሌላ በኩል የከተማው ባለሆቴሎች እና አልጋ አከራዮች ማንነቱ ያልታወቀ የታጠቀ ግለሰብ በድርጅታችሁ ሲያጋጥማችው ለህግ አካላት ጥቆማ እንድትሰጡ ያለው የፀጥታ ምክር ቤት፤ የቤት አከራይዎች የሚያከራዩትን ግለሰብ ማንነትት መታወቂያ በመጠየቅ ለይተው እንዲያከራዩ እንዲሁም የተከራዩንም መረጃ በፎርም በመሙላት ለከተማው ሰላምና ፀጥታ መምሪያ እንዲያሳውቁ አሳስቧል፡፡

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ነሐሴ 18፣ 2014 ያገረሸውን የፌዴራል መንግሥት እና ሕወሓት ጦርነት ተከትሎ ከደብረ ብርሃን ከተማ ውጪ ሌሌችም የአማራ ክልል ከተሞች አስገዳጅ ውሳኔዎችን ማሳለፋቸው ይታወቃል፡፡

በፀጥታ ስጋት ምክንያት አዳዲስ ውሳኔዎችን ያሳለፈችው የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር፤ ከፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫ አዲስ አበባ ከተማ በ120 ኪሎ ሜትር ርቀት እንደምትገኝ ይታወቃል፡፡