2023-06-04 15:04:55
የአሏህ ሚዛን እንደ ሰዎች ሚዛን አይደለም። ሰዎች ሃይልን ከቁስ ጋር ያገናኛሉ። ድል የሚመጣውም አካላዊ በኾኑ እና ሰዎች አእምሮ ዘንድ በሚመጡ የተለያዩ ሠው ሠራሽ ግብአቶች ነው ብለው በብዛት ያምናሉ። አሏህ ዘንድ ግን ይህ ሚዛን ብቻውን ተቀባይነት የለውም። ሚዛን ደፊ እምነትም አይደለም። ሰዎች ከሚገምቱት ውጭ አሏህ ረቂቅ በሆነ ጥበቡ ድክመት ውስጥ ሃይልን ያደርጋል። ይህንን ሃሣብ የመልእክተኛውን ንግግር ያጤነ ይረዳዋል።
መልእክተኛውﷺ እንዲህ ብለዋል፦
" አሏህ ይህችን ኡመት በደካሞቿ ዱዓ፣ ሶላት እና ኢኽላስ የበላይ ያደርጋል (ይረዳል)።
[ሶሂህ አቲርሚዚይ ]
ቤታችው ቁጭ ባሉ ሴቶች፣ አዛውንቶች፣ ህፃናት ፣ መናገርን ባልቻሉ ደካሞች ፣ ነገሮች በጠበቡባቸው ሰዎች ፣ ምንም ስንቅ የሌላቸው ድሃዎች በሚያደርጉት ዱዓ፣ ሶላት እና ኢኽላስ አሏህ ይህን ኡመት ይረዳል። ድክመት የሚባለው በሐሪዎች ሁሉ ቢገኙባቸውም አሏህ በነዚህ ሰዎች መልካም ስራ ዲኑን ይረዳል። ታላቁ ሃይል እና ትልቁ የበላይነት መጎናፀፊያ መንገድ ለአሏህ ታዛዥ መሆን ነው። መልእክተኛው ﷺ እንዳሉት፦
" ሰዎች ዘንድ ቦታ የሌለው ደካማና ፀጉሩ የተንጨባረረ ሰው አንድን ነገር ለማድረግ በአሏህ ላይ ምሎ ቢናገር አሏህ መሃላውን ተፈፃሚ የሚያደርግለት(ዱዓውን የሚሠማው) ሰው አለ።" [ሶሂህ ሙስሊም]
የብዙ ነገሮች ሃይል እና አቅም ጠላቶቻችን እጅ ስር ቢኾንም አሏህ አይኑን ከአማኝ ባሮቹ ለአፍታ እንደማያዞር እርግጠኞች መሆን አለብን። አሏህ ባሮቹን በበታችነት እና በተገዢነት ስር ዘውታሪ እንዲሆኑ አይወድም። "ሚዛኑ በአር-ራህማን እጅ ነው። ከፊል ሰዎችን የበላይ ያደርጋል፣ ሌሎችን የበታች ያደርጋል።" ብለዋል [ሶሂሁል ጃሚዕ]
እኛ እርሱን ለማስወደድ እውነተኛ ጉዞን ካደረግን፤ ዝቅ ካልን በኻላ እርሱ የበላይ እንደሚያደረግን እውን ነው።
t.me/alhadith_islamic
98 views12:04