Get Mystery Box with random crypto!

የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር በክልሉ መንግስት ተሰጥቶት የነበረው ፈቃድ ተሰረዘ #Ethiopia | Ahmed Habib Alzarkawi

የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር በክልሉ መንግስት ተሰጥቶት የነበረው ፈቃድ ተሰረዘ

#Ethiopia | የሶማሌ ክልል ፍትህ ቢሮ “ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ፈጽሟል” ያለውን የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር ፈቃድ ሰረዘ።

የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር በበኩሉ እርምጃው “የመገናኛ ብዙሃንን ነጻነት ለማፈን የተወሰደ ነው” ሲል ውሳኔውን ነቅፏል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ 24 የጋዜጠኛ ማህበራት ውስጥ አንዱ የሆነው የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር የተመሰረተው ከሶስት ዓመት ገደማ በፊት በህዳር 2012 ዓ.ም ነው።

ማህበሩ የተቋቋመው፤ በክልሉ በጋዜጠኝነት ሙያ ረገድ ያለውን “አነስተኛ ልምድ ለማሳደግ” እና በጋዜጠኞች ላይ ለሚደርሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች “ድምጽ ለመሆን” በሚል ዓላማ እንደነበር መስራቾቹ ይናገራሉ።

በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ 86 ጋዜጠኞችን በአባልነት ያቀፈ እንደሆነ የሚነገርለት ይህ ማህበር፤ ፈቃዱ የተሰረዘው ከሁለት ሳምንት በፊት ነው።

የሶማሌ ክልል ፍትህ ቢሮ ለማህበሩ የሰጠውን ፈቃድ መሰረዙን ያስታወቀው፤ ለክልሉ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ጥር 23፤ 2015 በጻፈው ደብዳቤ ነው።

ማህበሩ ፈቃዱ የተሰረዘበት “ተገቢ ያልሆነ ድርጊት” በመፈጸሙ መሆኑን የክልሉ ፍትህ ቢሮ በደብዳቤው አስፍሯል።

ይህ ደብዳቤ የደረሰው የሶማሌ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ፤ የጋዜጠኞች ማህበሩ በክልልም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ “ፈቃድ የሌለው” መሆኑን በመግለጽ ለክልሉ የጸጥታ ቢሮ እና ፖሊስ ኮሚሽን ደብዳቤ ጽፏል።

የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ በዚሁ ደብዳቤው፤ የጋዜጠኞች ማህበሩ “ህዝብን የሚያሳስት እና የአካባቢውን መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥል የተሳሳተ መልዕክቶችን ለማሰራጨት” በዝግጅት ላይ መሆኑን ጠቅሶ ነበር።

የጋዜጠኞች ማህበሩን “ማህበራዊ ንቅናቄ” (social mobilization) በማደራጀት የሚወቅሰው የኮሚዩኒኬሽን ቢሮው፤ የክልሉ የጸጥታ አካላት “በህጉ መሰረት ተገቢውን እርምጃ” በማህበሩ ላይ እንዲወስዱ አሳስቧል።

ፈቃዱ የተሰረዘበት የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር በክልሉ ፍትህ ቢሮ የተወሰደበትንም እርምጃም ሆነ በኮሚዩኒኬሽን ቢሮው በኩል የቀረበትን ወቀሳ አይቀበልም።

የማህበሩ ፕሬዝዳንት አብዱራዛቅ ሀሰን፤ የማህበሩን ፈቃድ መሰረዝ “የመገናኛ ብዙሃንን ነጻነት ለማፈን የተወሰደ እርምጃ ነው” ሲሉ ተችተውታል።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ በማህበሩ ላይ የወሰደው እርምጃ፤ በሶማሌ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ 15 መገናኛ ብዙሃን እና ወኪሎች “ከስራ እንዲታገዱ ከተላለፈው ውሳኔ ጋር የተያያዘ ነው” የሚል እምነት እንዳላቸውም የማህበሩ ፕሬዝዳንት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

አማኑኤል ይልቃል