Get Mystery Box with random crypto!

ለናይል ወንዝ የተላከ የዑመር ረዲየላሁ ዐንሁ ደብዳቤ ታሪክ (አጭር ምርመራ) ኢስላምን ከሌሎች እ | Al HiDAYA MidiA የተበዳይ ሙስሊሞች ጉዳይ ያሳስበኛል📚ተዉሂድ የሁለት ሀገር የስኬት 🔑ቁልፍ ነዉ📖

ለናይል ወንዝ የተላከ የዑመር ረዲየላሁ ዐንሁ ደብዳቤ ታሪክ
(አጭር ምርመራ)
ኢስላምን ከሌሎች እምነቶች ልዩ የሚያደርገው በእምነቱ ስም የሚወሩ ዘገባዎችን የሚያጣራ የረቀቀ የሐዲሥ ጥናት ማካተቱ ነው፡፡ በዚህ የሐዲሥ ጥናት መሰረት መስፈርት የማያሟሉ ዘገባዎች መልእክታቸው ጣፈም መረረም ይጣላሉ፡፡ መስፈርት የሚያሟሉ ከሆነ ደግሞ መልእክታቸው ጣፈጠንም መረረንም መቀበል ግዴታችን ነው፡፡ ይህንን ሐቅ ጠንቅቆ ማወቅና ማክበር በተለይ በዚህ ያማራቸውን ቂሳ ሁሉ ሳያጣሩ የሚያግበሰብሱ ሰባኪዎች በበዙበት ዘመን እጅግ አንገብጋቢ ይሆናል፡፡ በዚህ ዘመን የሰው መለኪያው ስሜት ሆኗል፡፡ ነፍስያው የወደደችውን “ወሬ” ሳያጣራ “ሶሒሕ” የሚያደርግ፣ ነፍስያው ያልጣማትን ደግሞ በብዙ መረጃ እንኳን ቢደገፍ በሆነ ሰበብ መጣል ብዙዎች የተለከፉበት በሽታ ሆኗል፡፡
ወደ ርእሳችን ስንመለስ ብዙዎቻችን ደጋግመን የሰማነው አንድ ቂሳ አለ፡፡ እሱም እንዲህ የሚል ነው፡-
በቅድመ-ኢስላም ታሪክ ግብፅ ውስጥ አንድ እምነት ነበር፡፡ እሱም የናይል ወንዝ ላይ በያመቱ ቆንጆ ልጃገረድ ካልተጣለበት በስተቀር በቂ ውሃ አይፈሰውም የሚል እምነት ነበር፡፡ ታዲያ ሃገሪቱ በታላቁ ሶሐባ ዐምር ኢብኑል ዓስ ረዲየላሁ ዐንሁ በተከፈተች ጊዜ ይህን የተለመደ ልማድ ኢስላም እንደማይፈቅድ በማሳሰብ ይከለክሏቸዋል፡፡ ግብፃውያኑ እንደፈሩት ውሃው ብዙው ቀርቶ ትንሹም ጠፋ፡፡ ሃገራቸውን ለመልቀቅ መዘጋጀት ያዙ፡፡ ሁኔታውን ያስተዋሉት ዐምር ኢብኑል ዓስ ጉዳዩን ለኸሊፋው ዑመር አሳወቁ፡፡ ከዑመርም እንዲህ የሚል ደብዳቤ መጣ፡ “የአላህ ባሪያ ከሆነው የሙእሚኖች መሪ ዑመር ለናይል ወንዝ!! የምትፈሰው በራስህ ከሆነ አትፍሰስ፡፡ እንዳትፈስ ያደረገህ አንድየውና ሀያሉ አላህ ከሆነ አንደየውንና ሀያሉን አላህ እንዲያፈስህ እንጠይቀዋለን፡፡” ዐምር ኢብኑል ዓስ ስለደብዳቤ አሳወቋቸው፡፡ ከዚያም በናይል ወንዝ ላይ ጣሉት፡፡ ውሃው በጣም በዝቶ መጣ፡፡ ያ ክፉ ልማድ በዚያ ሳቢያ ቆመ፡፡” ልብ በሉ ባጭሩ ነው ያሰፈርኩት፡፡ ብዙዎቹ ተራኪዎች በታሪክ መዛግብት ላይ ከሚገኘውም ባለፈ “ማጣፈጫ ቅመሞችንም” እየጣጣሉ ያደምቁታል፡፡
ቂሳውን የተለያዩ የታሪክ ዘጋቢዎች ዘግበውታል፡፡
ቂሳው ግን ግልፅ ድክመት ያለበት በመሆኑ ለመረጃነት የማይበቃ “ዶዒፍ” ነው፡፡ እንመልከት፡-
1. ከሐዲሡ ሰንሰለት ውስጥ ያለው ኢብኑ ለሂዐህ ደካማ ነው፡፡ ይህንን በርካታ የዘርፉ ምሁራን ገልፀውታል፡፡ ለአብነት ያክል ቡኻሪ [አድዱዓፉ አስሶጊር፡ 190]፣ ኢብኑ ሒባን [አልመጅሩሒን፡ 2/2]፣ ኢብኑ ሐጀር [ጦበቃቱል ሙደሊሲን፡ 54] እና ሌሎችም፡፡ እንዳውም ኢብኑ መህዲ “ከኢብኑ ለሂዐ ጥቂትም ሆነ ብዙ አልወስድም” ብለዋል፡፡ ነሳኢ “ታማኝ አይደለም” ብለዋል፡፡ ኢብኑ መዒን “በሐዲሡ የማይመረኮዙበት ደካማ ነው” ብለዋል፡፡ አልጁዘጃኒ “ሊመረኮዙበት አይገባም” ብለዋል፡፡ ሌሎችም ብዙ የተናገሩ አሉ፡፡ እነዚህ ጥቆማዎች የኢብኑ ሐጀር ተህዚብ ኪታብ ላይ ይገኛሉ፡፡
ማሳሰቢያ፡-
“ኢብኑ ለሂዐህ ከኢብኑ ሙባረክ፣ ከኢብኑ ወህብ እና ከሙቅሪ ካወራ ዘገባው ሶሒሕ ነው” ያሉ አሉ፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግም ከላይ የተዘረዘሩትን ትችቶች ወደ ጎን በመተው ወይም ደግሞ በዚህኛው በመገደብ የኢብኑ ለሂዐን ዘገባዎች ዋጋ የሰጡ አሉ፡፡ ነገር ግን አሁን የምንነጋገርበት የናይል ታሪክ በነዚህ ሶስቱ ሰዎች አማካኝነት ስላልተላለፈ በዚህኛው መስፈርት እንኳን የማለፍ አቅም የለውም፡፡
2. በሰነዱ ውስጥ የማይታወቅ ሰው አለ፡፡ ታሪኩን ኢብኑ ለሂዐህ ከቀይስ ኢብኑል ሐጃጅ የወሰደ ሲሆን እሱ ከማን እንደወሰደው ግን ግልፅ አይደለም፡፡ ሰውየው አይታወቅም፡፡ ከዚህ ካልታወቀ ሰው ያስተላለፈው ቀይስ ብቻ ነው፡፡ ከቀይስ ደግሞ ብዙ ትችቶችን ያስተናገደው ኢብኑ ለሂዐህ፡፡ እንዲህ አይነቱ ታሪክ በሐዲስ ጥናት ሳይንስ “ሙብሀም” ይባላል፡፡ ሙብሃም የሆነ ሐዲሥ በሰንሰለቱ ውስጥ ስሙ በውል ያልተገለፀ ዘጋቢ ያለበት ሐዲሥ ነው፡፡ ሐፊዝ ኢብኑ ሐጀር “ዘጋቢው ያልታወቀን ሐዲሥ በውል እስከሚታወቅ ድረስ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ምክንያቱም አንድን ወሬ ለመቀበል መስፈርቱ አስተላላፊው ብቁ ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡ ስሙን ግልፅ ካላደረገ ማንነቱ አይታወቅም፡፡ ታዲያ እንዴት ብቁነቱ ይታወቃል?!!” ይላሉ፡፡ [ኑኽበቱል ፊክር፡ 511] ሌላው ቀርቶ ብቁነትን በሚጠቁም መልኩ ቢወራ እንኳን ዘጋቢው በውል እስካልተለየ ድረስ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ [ኑኽበቱል ፊክር፡ 19] ስለዚህ ይሄኛውም ምክንያት ቂሳው ተቀባይነት እንዳይኖረው የሚያደርግ ሰበብ ነው፡፡
3. ሌላኛው ታሪኩን ውድቅ የሚያደርገው ምክንያት በሰንሰለቱ ውስጥ የሚገኘው ሌላኛው ዘጋቢ ቀይስ ኢብኑል ሐጃጅ ዐምር ኢብኑል ዓስንም ሆነ ዑመር ኢብኑል ኸጣብን ያላገኘ መሆኑ ነው፡፡ ሁለቱንም አላያቸውም፡፡ ይሄ ከሁለተኛው ነጥብ ጋር ተደምሮ የሚታይ ነው፡፡
ሲጠቃለል ቂሳው ጠንካራ መሰረት የሌለው “ታሪክ” ነው ማለት ነው፡፡ ምናልባት ይሄ ታሪክ ስለሆነ የሐዲሥ መስፈርቶችን ባያሟላም ችግር የለውም የሚሉ ሊኖሩ ስለሚችሉ የአላህ ፈቃዱ ከሆነ በዚህ ረገድ ዑለማዎች ምን እንደሚሉ ለማየት እሞክራለሁ፡፡ የተጠቀምኩት መረጃ በአብዛሀኛው ከሸይኽ ዐሊ ሐሺሽ ጥናት የተወሰደ ነው፡፡ [ተውሒድ መፅሔት፡ ቁ. 442፣ ሸዋል 1429፣ ገፅ፡ 53-55]
ሼር ማድረግ አይርሱ፡፡
=
@AlhidayaMidia