Get Mystery Box with random crypto!

እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና ! በመላው ዓለም ለምትገኙ ክርስቲያኖች በሙሉ እንኳን ለጌታችን ለመድኃ | የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ (pastor Alemayehu Abebe )

እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና !

በመላው ዓለም ለምትገኙ ክርስቲያኖች በሙሉ እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታች ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል መታሰቢያ በሰላም አደረሳችሁ !

" ... እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፤ እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ።"( ማቴዎስ 28:-6)

ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት አስቀድሞ እንደሚነሳ ተናግሮ ነበር ። ደቀ መዛሙርቱ ግን ይህንን እውነት አላስተዋሉትም ። ስለዚህ ተስፋ በመቁረጥ ሲያዝኑ ሲተክዙ አንዳንዶችም ገና ሲጠሩ ወደነበሩበት የኃልዮሽ ሲገሰግሱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተናገረው በሦስተኛ ቀን ተነሳ ።

የኢየሱስ ትንሳኤ ለሁሉ የተገለጠ ነበር ። እንደ ተናገረው የሞትን ጣር አጥፊቶ ተነስቷል። መቃብሩ ባዶ ነው። ስለዚህ ተነስቷል እንጂ በዚህ የለም ኑና አረጋግጡ እዩም ተባሉ። በአንጻሩም ፈሪሳውያን ሱዱቃውያን ተቃዋሚዎች ሁሉ ጠባቂዎችን በማኖር ትንሳኤውን ሊሸፋፍኑ ጥረት ቢያደርጉም ኢየሱስ በብዙ ማስረጃ ለአርባ ቀን ሕያው ሆኖ ታያቸው ።(የሐዋርያት ሥራ 1:2)

እኛ ልንረዳው የሚገባውንን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የሞት እና የትንሳኤ ሚስጥር ምንድነው ?

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት እና ትንሳኤ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ብቻ አይደለም። በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት እና ትንሳኤ ውስጥ አንተም አንቺም ሁላችን አለን ። ምክንያቱም እርሱ የተቀበለው ሞት የሞተው የተነሳውንም ትንሳኤ የተነሳው ለእኔና ለእናንተ ነው ።

ስለዚህ የድነታችን ሚስጥር የተሰወረበት እውነት ነው ። የተከናወነው ልውውጥ ነው ። እርሱ ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ቁስላችንን ወስዶ ፈወሰን ፣ እስራታችንን ወስዶ ፈታን ፣ ስቃያችንን ወስዶ ያሳረፈን፣ ሞታችንንም ወስዶ ህይወት ሰጠን ፣ መቃብራችንን ወስዶ ትንሳኤን ሰጠን በፍጻሜውም የሞትን ጣር አጥፍቶ ተነስቶ አርጎ በአብ ቀኝ ተቀምጦ በአብ ቀኝ ከርሱ ጋር ያስቀመጠን የጌቶች ጌታ የነገስት ንጉስ እርሱ ጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

ስለዚህ ትንሳኤውም የእኔና የናንተ ነው ። ለዚህ ነው በሞቱና እና በትንሳኤው ከርሱ ጋር ለመተባበር የምንጠመቀው ። ይህ የተከናወነው እውነት ምሳሌያዊ መግለጫ አና ከእርሱ ጋር በመተባበራችን በሁሉ ፊት የምንገልጥበት ምስክርነታችን ነው። በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኔና ስለናንተ በመስቀል ላይ ያከናወነውን ሁሉ ስለ እኛ መሆኑን በማመን የእዳ ጽህፈታችን በርሱ እንደ ተደመሰሰልን አምነን ስንቀበል በርሱ በሆነልን ሥራ ድነታችን ይፈጸማል ። በጥምቀትም ሞቱ ሞታችን ፣ ቀብሩም ቀብራችን፣ ትንሳኤውም ትንሳኤአችን እንደሆነ በመቀበል ከዓለም ተሰናብተን ለአዲስ ሕይወት መለየታችንን እናውጃለን።

ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ “ተፈጸመ” አለ (ዮሐ 19፡30) “ተፈጸመ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “tetelestai" ቴቴሌስታይ ሲሆን ይህ ቃል “ሙሉ በሙሉ ተከፈለ” ማለት ነው ።

1ኛ, የሰው ልጅ የኃጢአት ዕዳው ሙሉ በሙሉ መከፈሉን ነው ያወጀው ። ስለዚህ በርሱ የሚያምኑ ሁሉ ከኃጢያት ዕዳ ነጻ ናቸው።ስለዚህ ይህን እውነት ያላመናችሁ ( 2ኛ ቆሮ 6፥2)

2ኛ,የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት እና ትንሳኤ በእውነት ያመኑበት ሁሉ ሞት ትንሳኤ ነው። የሞት መውጊያ ተሰብሯል የሞት መውጊያ ኃጢያት ነው። ( 1ኛ ቆሮ15፥55 )

3ኛ,በአስደናቂ የትንሳኤ እውነት የተረጋገጠ ሞትን የሚሻገር የከበረ ተስፋን የጨበጠ እምነት የክርስትና እምነት እና ሕይወት ብቻ ነው ። እንኳን ክርስቲያን ሆንኩኝ ።

4ኛ,ዛሬም ውድቀታችሁን ለሚጠብቁ መነሳት ይሆናል፣ሞታችሁ ለሚጠብቁ ትንሳኤ ይሆናል ፣ውርደታችሁን ለሚጠብቁ ክብር ይሆናል በሏቸው አውጁ ጠላም ሰዎችም ፍጥረትም ሁሉ ይስማ ።

እግዚአብሔር ትንሳኤያችሁን በግልጽ ያሳያችኃል ! የተመከረባችሁ ምክር አይጸናም ! እንደተደረገባችሁ ክፋት አይከናወንም ! እንደተወራባችሁ ሟርት አይሆንም ! ሰይጣን ያለው ሳይሆን እግዚአብሔር የተናገራችሁ ይፈጸማል። መጪው የአሸናፊነት የድል ጊዜ ፣ የሥኬት እና የመከናወን ጊዜ ይሆናል ።

ፓስተር አለማየሁ አበበ እና ቤተሰቡ
ከረጲ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን