Get Mystery Box with random crypto!

አንዳንድ ነገሮች (በእውቀቱ ስዩም) ፓስተር ዮናታን “ መልካም ወጣት “ የሚል ስልጠና በመስጠቱ | Alex Abreham በነገራችን - ላይ

አንዳንድ ነገሮች
(በእውቀቱ ስዩም)
ፓስተር ዮናታን “ መልካም ወጣት “ የሚል ስልጠና በመስጠቱ የምትናደዱ ሰዎች ፥ ለምን እናንተ “ መልካም ሽማግሌ” የሚል ስልጠና ጀምራችሁ አትሸቅሉም? እኔና ዮናታን የመጀመርያዎቹ ተመዝጋቢዎች እንደምንሆን ተወዲሁ ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ፡ ፡
ዘግይቼም ቢሆን ለኢትዮጵያ ህዝብ እንኩዋን ደስ ያለህ ማለት እፈልጋለሁ፤ አንዳንዴ በደስታ ስትሆኑ ብዙ ነገር አይታችሁ ባላየ ታሳልፋላችሁ፤ አትሌቶቻችን ድል ያደረጉ ቀን እጅግ ከመደሰታችን የተነሳ “ እኛም ኮራን “ እሚለውን ዝማሬ እስከመጨረሻው ታግሰን እንሰማዋለን፤
በቀደም እዚህ በረንዳ ላይ ቁጭ ብለን እንቀመቅማለን፤ ከመካከላችን አንዱ፥
“ ትግሬዎች በስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ያላገኙትን የሩጫ ድል እንዴት ሊያስታቅፉን ቻሉ” የሚል ጥያቄ ጠየቀ፤
የምታስተናግደን ሴት፤ የሰላም ተስፋየን ቅርጽ እና የፍርያት የማነን ፊት አስተባብራ የያዘች ቆንጅየ ልጅ ስለሆነች ፥እስዋን ኢምፕረስ ለማድረግ እየተጭዋጩዋህን እየተሻማን ምላሻችንን አቀረብን፤
አንድ “ መልካም ሽማግሌ” ያቀረቡትን ምላሽ ከታች አስቀምጨዋለሁ::
“ የትግራይ ሰው አትሌቲክስ ከጥንት ጀምሮ መክሊቱ ነው ፤ ደብረዳሞን የመሳሰሉ ተራሮች በሌጣ እግሩ ሲወጣ ሲወርድ ስለኖረ እግሩ ብርቱ ፥ ትንፋሹ የትየለሌ ነው ፤ ግን መንግስትነት ያዘናጋል፤ መንግስት ስትሆን ታሯሩጣለህ እንጂ አትሮጥም፤ ስላዳመጣችሁኝ አመሰግናለሁ”
በነገራችን ላይ ስለምስጋና ያለኝ ፍልስፍና አጭር ነው ፤ የተደረገለት ያመስግን ! የተደረገበት ያማርር!
ለነገሬ ማድመቂያ የሻለቃ ገብረሀናን ተረብ ልንገራችሁ፤( የገብረሀና ማእረግ ዘመኑን እንዲመጥን ሆኖ ተቀይሯል)
ሻለቃ ገብረሀና ደቀመዝሙር አላቸው ፤ ደቀመዝሙሩ ቀኑን ሙሉ ሲዞር ውሎ ከየቤቱ ቁራሽ እና ጥሬ ለምኖ ያቀርብላቸዋል፤ አንድ ምሽት ደቀመዝሙሩ ቀኑን ሙሉ ሲንከራተት ውሎ አልቀናውም፤ ራት ሰአት ላይ ከግብዳ አኮፋዳ ውስጥ ፥ የትራምፕን መዳፍ እምታክል ጢንጥየ ቁራሽ አውጥቶ አቀረበላቸው ፤ ሻለቃ ገብረሀና እያጉረመረሙ መዳፋቸውን ወደ ቁራሺቱ ሰደድ ሲያደርጉ፥ ደቀ መዝሙር እጃቸውን አፈፍ አድርጎ ያዛቸውና፥
“ሻለቃ ከመብላታችን በፊት እናመስግን " አላቸው፤

እሳቸው ፈገግ ብለው፤
“ ተው ልጅየ! አሾፋችሁብኝ ብሎ መብረቅ ይጥልብናል”