Get Mystery Box with random crypto!

ኢያቄምና ሐና በዕለቱ ራእይ አይተው ነገር አግኝተው አደሩ፡፡ ራእዩም ኢያቄም ሰባቱ ሰማያት እንደ | "ኤልሮኢ ዘተዋህዶ"

ኢያቄምና ሐና በዕለቱ ራእይ አይተው ነገር አግኝተው አደሩ፡፡ ራእዩም ኢያቄም ሰባቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ አየ፡፡ ለሐና ነገራት ሐናም እኔም አየሁ አለችው፡፡ ምን አየሽ ቢላት? ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማኅጸኔ ስትተኛ አየሁ አለችው:: ርግብ የተባለች እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት፡፡ ነጭነቷ ንጽህናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ድንግልናዋ ነው፡፡ ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማኅጸኔ ስትተኛ አየሁ ማለቷ ብስራተ ገብርኤልን በጆሮዋ ሰምታ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችንን መፀነሷ ነው፤ ይህንኑም ራእይ ያዩት ሐምሌ 30 ነው::

እንዲህ ያለ ራእይ ካየን ነገር ካገኘን ብለው ዕለቱን በሩካቤ ሥጋ አልተገናኙም፡፡ ፈቃደ እግዚአብሔር ቢሆን ብለው አዳምንና ሔዋንን ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሉዓት ብሎ ያበሰረ አምላክ ለኛስ ይልክልን የለምን? ብለው ዕለቱን አልጋ ምንጣፍ ለይተው እስከ ሰባት ቀን ድረስ ለየብቻቸው ሰነበቱ፡፡ ነሐሴ በባተ በሰባተኛው ቀን መልአኩ ከሰው የላቀች ከመላእክት የከበረች ዓለሙ ሁሉ ተሰብስቦ ቢመዘን አንድ የራሷን ፀጉር የማያህል ደግ ፍጥረት ትወልዳላችሁ አላቸው፡፡ በፈቃደ እግዚአብሔር በብስራተ መልአክ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እሁድ እለት ተፀነሰች፡፡

እመቤታችን በተፀነሰች ዕለት አይሁድ ቀንተው ተነሱባቸው፡፡ ቅናቱ እንዴት ነው? ቢሉ ሳሚናስ የሚባል የጦሊቅ ልጅ ከኤዶቅ ከአጎቱ ቤት ሔዶ ሞተ እነርሱም እንቀብራለን ብለው በአልጋ ይዘው ሲሄዱ ከመንገድ አሳረፉት፡፡ የሐናም የአጎቷ ልጅ ነበርና ለማልቀስ ብትደርስ ዘመዶቿ ሁሉ ተሰብስበው ሲላቀሱ ቆይዋት:፡፡ እርሷ አብራ ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል የሞተው ልጅ ብድግ ብሎ ተነሳ፡፡ ሕዝቡ ሁሉ ተገረሙ ተደሰቱ አይሁድ አብረው ነበሩና ሳሚናስ ምን አየህ? ምን ትላለህ? ቢሉት ከሐና ማኅፀን የምትወለደው ሕፃን ሰማይ ምድርን እመቀ አየርን የፈጠረ አምላክን ትወልዳለች፡፡ እያሉ መላእክት ሁሉ ሲያመሰግኗት ሰማሁ፡፡ እኔንም ያስነሳችኝ ያዳነችኝ እርሷ ናት አላቸው፡፡ ያን ጊዜ አይሁድ እነዳዊት እነሶሎሞን አባቶቻችንን 40፣40 ዓመት እንደ ሰም አቅልጠው፤ እንደ ገል ቀጥቅጠው ገዙ፡፡ ከሐና የሚወለደውም እንዲሁ ሊገዛን ነውን? ብለው ሳይወለድ እንግደለው ብለው ሊገድሉ ያስቡ ነበር ፡፡ መልአኩም አይሁድ እንዳያገኟቸው ወደ ሊባኖስ እንዲሰደዱ ነገራቸው፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም በሊባኖስ ግንቦት 1 ተወለደች::

እመቤታችን በተወለደችበት ዕለት ደስታ ተደረገ፡፡ ቤታቸው በብርሃን ተመላው በስምንተኛውም ቀን ማርያም ብለው ስም አወጡላት:: በዚህ መሰረት የእመቤታችንን የልደት በዓል(ግንቦት ልደታ) በታላቅ ክብር ከሚያከብሩ አብያተ ክርስቲያናት መካካል ዋነኛዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ናት፡፡ የግንቦት ልደታ በዓል አከባበር በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት መሰረት ኢያቄምና ሐና ከአይሁድ ለማምለጥ ተሰደዉ ምግባቸው ንፍሮና ጥራጥሬ ስለነበር ይህንን ትውፊት መሰረት በማድረግ በቤተ ክርስቲያን በማኅሌት፣ በቅዳሴና ታቦታትን በማክበር፣ ከመኖሪያ ቤት ዉጭም ቂጣ ተጋግሮ፤ ንፍሮ ተቀቅሎ እየተበላ ይከበራል፡፡

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ፍቅሯ አማላጅነቷ በሁላችን ይደር፡፡ አሜን፡፡

@aleroe
ለሀሳብ አስተያየት @Aleroebot