Get Mystery Box with random crypto!

በመስጊድ ብቻ በመወሰኑ ከበርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች ወደ ኋላ ተመለሰ። በርግጥ እውነታውን ካ | Ahmedin Jebel - አሕመዲን ጀበል

በመስጊድ ብቻ በመወሰኑ ከበርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች ወደ ኋላ ተመለሰ።

በርግጥ እውነታውን ካየነው የሀገሪቱ አጠቃላይ ችግሮች ሳይቀረፉ የሙስሊሙ ሃይማኖታዊ ጥያቄ ብቻውን ተለይቶ ሊመለስ የሚችልበት ሁኔታ እንደሌለ በመረዳት በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮችም ላይ ከሌሎች ዜጐች ጋር በጋራ መታገል ነበረባቸው። የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንደተጨቆኑ፣ እንደተገፉና በስርዓቱ ውስጥ ተገቢ መብታቸው እንዳልተከበረ በማመናቸው ተደራጅተው ሲታገሉ ለዘመናት ሲጨቆን የነበረው፣ መብቶቹ ያልተከበሩለት እና ከብዙ ሀገራዊ ጉዳዮች ወደ
ኋላ የቀረው ህዝበ ሙስሊሙ መብቱን ለማስከበርና እኩልነቱን በሁሉም ዘርፍ በተግባር ለማረጋገጥ የሚታገልለት አካል መፍጠር አልቻለም።በጣት የሚቆጠሩ ሙስሊሞች በወቅቱ ከተቃዋሚ ጐራ ተሰልፈው የነበሩ ቢሆንም የሙስሊሙን አጀንዳዎች የፖርቲዎቹ አጀንዳ ማድረግ አልቻሉም። ቁጥሩ ከሌሎች አንፃር እጅግ አናሳ ቢሆንም ከተቃዋሚዎቹ ይልቅ በደርግ ውስጥ በመጠኑ የተሻለ ቁጥር ያላቸው ሙስሊሞች ነበሩ። ይህ የሆነው ተቃዋሚነት ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ ዋጋ በመክፈል ለአጀንዳቸው ለመቆም የተዘጋጁ ባለመሆናቸው ሳቢያም ሊሆን ይችላል።

በነኝህና መሰል ሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ያ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረው መነቃቃት እየቀዘቀዘ የሚገባውን ያህል ውጤት ሳያስመዘግብ ቀርቷል። ይህ ሊሆን የቻለው የዓለም ታሪክ እንደሚያስገነዝበው የትኛውም ሕዝብ መብቱንና እኩልነትን በልመናና ተማጽኖ ሊያገኝ የቻለበት ሁኔታ ያልታየ በመሆኑ ነው። ሂደቱን ስንመለከት የ1966ቱ የሙስሊሙ ንቅናቄ መሪዎች የላቀ ባይሆንም በተግባር ግን ካነሷቸው 13 የመብት ጥያቄዎች ምላሽ ሲሹ የነበሩበት
በዋናነት መንግስትን በመማፀን፣ በመለመንና ምላሽ እንደሚያገኙ ተስፋ በማድረግ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሕዝበ ሙስሊሙ ልሂቃንን በማፍራት እና በማብቃት ሥራ ላይ በቀጣይነት ሲንቀሳቀሱ አናይም። እነኝህን በመተግበር እንደሌሎቹ የመብት አስከባሪ ታጋዮች ሁሉ በሀገሪቷ ሁለንተናዊ ጉዳዮች ውስጥ በተለይም በፖለቲካው በመሳተፍ ትግል ቢያካሂዱ ኖሮ የተሻለ ለውጥን ማምጣት በቻሉ ነበር። ምክንያቱም በሀገሩ ፖለቲካ ላይ እኩል ተሳታፊ ያልሆነ አካል ሁሌም በሀገሪቱ እጣፈንታ ላይ እኩል የመወሰን እድል አይኖረውም። ይህ ሲሆን ደግሞ በሀገሩ እጣፈንታ ላይ ሚናው አነሳ ከመሆኑም በተጨማሪ የራሱ እጣፈንታ ጭምር በሌሎች መዳፍ ስር ይወድቃል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ የቱንም ያህል ቅንና ፍትሓዊ ጥያቄዎች ቢኖሩትም እኩል ተጠቃሚ የመሆን ዕድሉ ሩቅ ነው።

በርግጥ የደርግ መንግስት የአፄ ኃይለ ሥላሴን ሥርዓት በማስወገድ ለኢስላም እና ለሙስሊሞች በብሔራዊ ደረጃ እውቅና በመስጠቱ አንፃር ብቻ ስናየው ሥርዓቱ ለሙስሊሞች ባለውለታ ነበር። ይሁን እንጂ በቀድሞ ሥርዓቶች የማግለል ፖሊሲ ምክንያት ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከሀገሪቷ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት በመገለሉ ምክንያት የተፈጠረበትን በደልና በብዙ መልኩ ወደ ኋላ የመቅረቱን እውነታ የሚያካክስ አዎንታዊ እርምጃዎችን (Affirmative Actions) ባለመወሰዱ ልዩነቱ በብዙ መልኩ ቀጥሏል፡፡ በመሆኑም በደርግ ስርአት ውስጥ አብዛኞቹ የመንግስት አስተዳደር፣ የፖለቲካ ተቋማት እና በመንግስታዊ መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሙስሊሞች ቁጥር አናሳ እንደሆነ ዘልቋል። ያም ሆነ ይህ በደርግ የመጀመሪያዎቹ የስልጣን ዘመናት ሕዝበ ሙስሊሙ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በጣት ሊቆጠሩ የሚችሉ አንኳር ጥቅሞችን አግኝቷል። በዝርዝር በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱትና በሕዝበ ሙስሊሙ ላይ ሲደርሱ የነበሩትን ጭቆናዎች አብዛኛዎቹን ያስወገደው የደርግ መንግስት ነበር።

የኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች መሪ ድርጅት የሆነው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጉባኤ (መጅሊስ) ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋመው በዚሁ በደርግ ዘመን በመጋቢት 4 ቀን 1968 ዓ/ል ነበር። ህዝበ ሙስሊሙም በካድሬዎች ሳይሆን እንደነ ሐጅ ሙሐመድ ሳኒ ሐቢብ ባሉና ቁርኣንን ወደ አማርኛ በተረጎሙ ስመጥር ሊቃውንት እንዲመራ የደርግ መንግስት ፈቅዷል። የሃይማኖት እኩልነትን እሳቤ በሕዝቡ ውስጥ ለማስረፅም ጥሯል። ኋላ ላይም ሥርዓቱ ከተከተለው የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ፍልስፍና አንፃር ሁሉንም ሃይማኖት በጥርጣሬና በስጋት ቢያይም እንደ መንግስት ሙስሊሙን ብቻ ነጥሎ የሥርዓቱ እና የሀገሪቷ ስጋት አድርጎ ባለመፈረጁና የማግለል ስልትን ባለመከተሉ ለሙስሊሙ የደርግ ሥርዓት ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት በእጅጉ የተሻለ መሆኑን አሳይቷል። አክሱምን ጨምሮ በአንዳንድ ሰሜናዊው የሀገሪቷ ክፍሎች የሚገኙ ሙስሊሞች ሕጋዊ የሙስሊሞች መካነ መቃብር እንኳን ማግኘት የቻሉት በአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግስት ውድቀት ማግስት ነበር። በነኝህና በሌሎች በርካታ ቆራጥ እርምጃዎቹ የደርግ መንግስት በመጀመሪያዎቹ ጥቂት የአገዛዝ ዘመኑ ለሙስሊሞች ውለታ ቢውልም ኋላ ላይ ግን በሙስሊሙም ሆነ በሌሎች በርካታ ጉዳዮች የሚያስወቅሱ በርካታ ተግባራትን ፈጽሟል።

ይህን ርዕስ ስናጠቃልልም ያኔ አስተዋፅኦ ያደረጉትን ሙስሊሞች የተቻለንን ያህል ስማቸውን መጥቀስ ያሻል ብለን ስላሰብን በዚሁ መሰረት ዝርዝራቸውን እነሆ ብለናል፡- እነ ሐጂ ሙሐመድ ሳኒ ሐቢብ፣ ሐጂ ዩሱፍ ዐብዱረሕማን፣ ዐብዱ በሽር፣ ዐብዱ አደም፣ ሐጂ ሻሚል ኑርሰቦ፣ ጀማል ዐሊ፣ ዐብደላ ሐሰን፣ ዐብደላ ዐብዱልቃዲር፣ አሕመድ ሸኽ አወል፣ ሲራጅ ሱለይማን፣ አሕመዲን ዩሱፍ፣ ዐብዱሶመድ ሰመረዲን፣ ሰዒድ ዩሱፍ፣ አሕመድ ዋሴ፣ ሲቲሚያ ሙሐመድ /ሴት/፣ አቶ ዐሊ አሕመድ፣ አቡበክር ሱለይማን፣ ሙሐመድ ሐጂ ሙሐመድ ሳኒ፣ ዒዘዲን ሙሐመድ /የአል ቁድስ አዘጋጅ የነበረው/፣ በድሩ ሡልጣን /የቃጥባሬ ሸኽ ልጅ/፣ አባቢያ አባጆቢር፣ አቶ አሕመድ ሰዒድ ዐሊ፣ አቶ ሙሐመድ አሕመድ ሸሪፍ እና ሐጂ ነጂብ ሙሐመድ ወዘተ ለሙስሊሙ መብት መከበር ከታገሉት መካከል ይገኙበታል። በሕይወት የሌሉትን አላህ ይማራቸው! ያሉትንም ያቆያቸው! በወቅቱ የታገሉት ከላይ የተጠቀሱት ብቻ ናቸው ማለት አይደለም። ሥማቸው እዚህ ያልተጠቀሱትም በርካቶች አሉ።

*****************************

ደካማ ይልቃል ኃይለኛ ሲዋረድ
ቡቃያ ይበቅላል ያፈራው ሲታጨድ
ሰፊው ይቀንሳል ጠባቡ ሲስፋፋ
ጨረቃ ታምራለች ፀሐይ ስትጠፋ
ከንቅልፉ ሲነቃ ደግሞ የፈዘዘ
የሞቀው ይሄዳል እየቀዘቀዘ
እንደሕልም ታይቶ ያልፋል እንደጥላ
ለዚህ ዓለም ነገር ምንም የለው መላ
መታወቅ መረሳት ማርጀት መታደስ
ይህ ሁሉ ልማድ ነው አይደለም አዲስ፡፡

(ዶ/ር ከበደ ሚካኤል)