Get Mystery Box with random crypto!

ጾምና ሙቀት ሙቀት በበረታበት ጊዜ እየተቸገሩ መጾም ምንዳን ከፍ ያደርጋል። | Ahmedin Jebel - አሕመዲን ጀበል

ጾምና ሙቀት

ሙቀት በበረታበት ጊዜ እየተቸገሩ መጾም ምንዳን ከፍ ያደርጋል። ደጋግ የአላህ ባሮች ዱኒያ ላይ መቆየትን እንዲመኙና እንዲወዱ ከሚያደርጉ ነገሮች መካከልም አንዱ ጾም በሚከብድበት ጊዜና ቦታ ላይ ችግሩን ተቋቁሞ መጾም ነው።

አቡ አድ'ደርዳእ رضي اللہ عنہ
"በሙቀት ጊዜ (በረሃ ውስጥ) ጥምን ተቋቁሜ መጾም፤ የሌሊት ሰላት ላይ የሚደረግ ሱጁድና እውቀትን አዋቂዎች ዘንድ ተንበርክኮ መማር ባይኖር ኖሮ ዱኒያ ላይ መቆየትን አልፈልግም ነበር" ሲሉ፤

ታላቁ ሰሓቢይ ዓሊይ ኢብኑ አቢ ጣሊብ ደግሞ ምን ትመኛለህ ተብለው ሲጠየቁ "በጋ ላይ መጾም፤ በአላህ መንገድ እየታገልኩ ጠላትን በሰይፍ መምታትና እንግዳን በክብር ማስተናገድ " ብለዋል።

ስለዚህ የዘንድሮ ጾም የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ሙቀት በበረታበት ወቅት ላይ መሆኑ ይበልጥ ሊያስደስተን ይገባል።

ከመሆኑም ጋር የሙቀትን ድካም የሚያቀንሱ ነገሮችን ማድረግ ይፈቀዳል። ለምሳሌ፥ በማንኛውም ሰዓት ገላን በቀዝቃዛ ውኃ መታጠብ፣ ፊት እና ጸጉር ላይ ውኃ ማፍሰስ፣ አፍን በውኃ መጉመጥመጥና መልሶ መትፋት፣ ከጸሐይ መሸሽ፣ አናትና ደረት ላይ የረጠበ ፎጣ ማስቀመጥ ወዘተ።

የዱኒያው ቀላል ሙቀት የጀሀነሙን ከባድ ግለት አስታውሷቸው ከርሱ የሚድኑበትን መልካም ስራ ለመስራት ደፋ ቀና ከሚሉ ባሮች አላህ ያድርገን!

ማታ ማታ ተራዊሕ ላይም ሙቀት አልችልም ብሎ ሰላት ትቶ ከመሄድ ይልቅ ታግሶና የጀሀነምን ግለት እያስታወሱ አላህን ከጀሀነም ጠብቀኝ ብሎ መማጸን በላጭና ብልሕነት ነው።

ኡስታዝ አሕመድ ሸይኽ ኣደም
ረመዷን 10/1445 ዓ.ሂ
ዛዱል መዓድ