Get Mystery Box with random crypto!

ኡድሒያን የሚመለከቱ ወሳኝ ነጥቦች ኡድሒያ ማለት በዐረፋ በዓል ቀን እና ቀጥሎ ባሉ ተከታታይ | Ahmedin Jebel - አሕመዲን ጀበል

ኡድሒያን የሚመለከቱ ወሳኝ ነጥቦች

ኡድሒያ ማለት በዐረፋ በዓል ቀን እና ቀጥሎ ባሉ ተከታታይ ሶስት ቀናት ውስጥ ወደ አላህ ለመቃረብ ተብሎ የሚታረድ የቤት እንሥሳ ማለት ነው።
"ኡድሒያ" የተባለው የእርዱ ሰዓት የሚጀምረው የዒድ ቀን ረፋድ (ዱሓ) ላይ ስለሆነ ነው።

ኡድሒያ ማረድ የዲን አካልና ተወዳጅ ተግባር መሆኑ ላይ ሁሉም ሊቃውንት ይስማማሉ፤ ብዙሃኑ ሊቃውንት ዘንድ ሱንናህ እንጂ ስለት (ነዝር) ለሌለበት ሰው ግዴታ አይደለም። አቡ ሐኒፋን ጨምሮ በርካታ ግዴታ ነው የሚል አቋም ያላቸው ሊቃውንት ስላሉና በዒድ ቀን ማረድ ልዩና ከፍ ያለ ምንዳም ስላለው አቅም ያለው ሰው ኡድሒያ ማረድ ባይተው ይመረጣል፤

ከቤት እንስሳት (ከግመል፣ ከከብት ፣ ከበግና ፍየል) ውጪ ሌላን እንስሳ ለኡድሒያ ማረድ እንደማይቻል የፊቅህ ሊቃውንት በሙሉ (ከሐሰን ኢብኑ ሳሊሕ በስተቀር) ይስማማሉ።

ለኡድሑያ የሚታረደው እንስሳ ወንድም ይሁን ሴት ለውጥ የለውም፤ ሁለትም ጾታዎች ለኡድሒያ እንደሚሆኑ (እንደ ሚበቁ) የፊቅህ ሊቃውንት ይስማማሉ።

የዒድ ቀን ከሰላተል-ዒድ በፊትና፣ ከ 14ኛው ቀን የጸሐይ መጥለቅ በኋላ የሚታረድ እርድ ከኡድሒያ አይቆጠርም።

በመሰረቱ የኡድሑያ እንስሳ መግዣ ገንዘቡን ሰደቃ ከመስጠት ይልቅ ኡድሒያ ማረዱ በአጅር ይበልጣል። ይህም የሆነው ኡድሒያ በዕለቱ ተወዳጅና ከዒድ ሰላት ጋር የተያያዘ ዒባዳህ ስለሆነ ነው። (ኢብኑልቀይም)

ነገር ግን ገንዘቡን መስጠቱ ለተቸገረ ሰው ይበልጥ የሚጠቅምበት ሁኔታዎች ላይ በላጩ ገንዘብ መስጠቱ ይሆናል። (ኢብኑ ዑሠይሚን)

ብዙሃኑ የፊቅህ ሊቃውንት ዘንድ ለኡድሒያ እርድ በላጭና ተመራጩ እንስሳ በቅደም ተከተል ግመል፣ ከዛም ከብት፣ ከዛ በግ ወይም ፍየል ነው።
ይህ የሚባለው ግን ግመል ወይም ከብት አንድ አባወራ ለብቻው የሚያርድ ከሆነ ነው። ለጋራ ወይም በቅርጫ ከሆነ ግን የሚያርደው ከግመልና ከከብት ይልቅ በግ ወይም ፍየል ይሻላል።
ኢማሙ ማሊክ በሁሉም ሁኔታ ላይ በላጩ በግና ፍየል፣ ከዛም ከብት፣ ከዛ ግመል ነው የሚል አቋም አላቸው።
ይህ በላጩና ይበልጥ ተወዳጁን ከመግለጽ አንጻር ነው እንጂ ከ4ቱ የቤት እንስሳት ውስጥ ማንኛውንም ቢያርዱ ትክክል ይሆናል።

ለኡድሒያ የሚታረድ ማንኛውም እንስሳ ቁመናና መልኩ የሚያምረው፣ ስጋው ይበልጥ ጣፋጭና ንጹህ ይሆናል የሚባለውና በዋጋም ውድ የሆነው ከዚህ ተቃራኒ ከሁኑ እንስሳት ይልቅ ለኡድሑያ ተወዳጅ እንደሚሆን ሊቃውንት ይስማማሉ። (አን'ነወዊይ)

ይህም ኡድሒያ የሚታረደው ለአላህ ተብሎ ስለሆነና ለርሱ የሚደረግ ነገር በሙሉ ንጹሁ፣ ትልቅና የሚያምር መሆን ስለሚገባው ነው።

ለኡድሒያ የሚታረድ እንስሳ እድሜው በግ ከሆነ 6 ወርና ከዛ በላይ፣ ፍየል ከሆነ 1አመትና ከዛ በላይ፣ ከብት ከሆነ 2 አመትና ከዛ በላይ፣ ግመል ከሆነ 5አመትና ከዛ በላይ መሆን አለበት።
ዕድሜው እዚህ ከተጠቀሰው በታች የሆነ እንስሳ ለኡድሒያ በቂ አይሆንም።

በተፈጥሮ ምንም ቀንድ የሌለው ወይም ቀንዱ በጣም ትንሽ የሆነ፣ ጭራ ወይም ላት የሌለው፣ የተኮላሸ፣ ጆሮው የተሰነጠቀና ከግማሽ በታች የሚሆነው ብቻ የተቆረጠ እንስሳን ለኡድሒያ ማረድ ችግር የለውም።
በላጩ ግን ቀንድ ያለውና አካላቱ ሙሉ የሆኑትን ማረዱ ነው።

ግልጽ የሆነና እንደልቡ ተንቀሳቅሶ እንዳይበላ የሚያደርግ ሸፋፋነት ያለበት፣ አንድ ወይም ሁለቱም አይኑ የማያይ፣ በጣም ከመክሳቱ የተነሳ ቅልጥም፣ ጮማና ሞራው ያለቀ/የሌለው፣ ግልጽ የሆነ በሽታ ወይም የበሽታ ምልክት ያለበት ማንኛውም እንስሳ ለኡድሒያ አይሆንም።

ከላይ ከተጠቀሱት እንከኖች ጋር ተመሳሳይና የባሰ እንከን ያለበትንም ማረድ አይቻልም።
ነገር ግን ከእነዚህ እንከኖች መካከል ቀላልና ግልጽ ያልሆነ ያለበትን ማረድ አማራጭ ካጡ እንደሚቻል ሊቃውንት ይስማማሉ።ጤነኛና ከእንከን ንጹህ ሆኖ የገዙት እንስሳ ያለጥንቃቄ ጉድለት ከላይ የተጠቀሱ እንከኖች ቢገጥሙት ማረድ ይቻላል፤ አቅም ያለው ሰው ሌላ ቢቀይር ግን ይመረጣል።

አንድ በግ ወይም ፍየል ለአንድ አባወራ እስከ ቤተሰቦቹ፣ አንድ ከበት ወይም ግመል ለ7 እና ከዛ በታች ለሆኑ አባወራዎች ( ቤተሰቦች) ይበቃል።
አንድ ሰው ኡድሒያው ላይ ማንኛውንም (በህይወት ያለም ይሁን የሞተን) ሰው በምንዳው ማጋራትና ማካተት ይችላል።

ለአንድ አብሮ ለሚኖር ቤተ ሰብ አንድ ኡድሒያ የሚበቃ ከመሆኑም ጋር አቅም ያለው በሙሉ በስሙ ኡድሒያ ቢያርድ መልካም ይሆናል።

አንድ እንስሳ ቤት ውስጥ ተወልዶ ያደገ (የረባ)ም ይሁን፣ እራሱ ወይም ገንዘቡ በስጦታ መልኩ የተገኘም ይሁን በማንኛውም ህጋዊ በሆነ መንገድ የራስ የተደረገ ከሆነ ለኡድሒያ ነይቶ ካረዱት በቂ ይሆናል። የግድ በጊዜው ለኡድሒያ ተብሎ በራስ ገንዘብ የተገዛ ካልሆነ አይባልም።

አንድን እንስሳ ለኡድሒያ ከወሰኑት በኋላ ሀሳብ ቀይሮ ማረዱን መተው፣ መሸጥ ወይም ለሌላ ሰው ስጦታ መስጠት አይቻልም።ግዴታ ላልሆነ ኡድሒያ የተዘጋጀ እንስሳ ያለጥንቃቄ ጉድለት ቢጠፋ ሌላ መተካት ግዴታ አይሆንም።

ለኡድሑያ የታረደን እንስሳ ቆዳውንም ይሁን ምኑንም መሸጥ፣ ለአራጅ ክፍያ ይሆን ዘንድ ብሎ ምንም ነገር መስጠት አይቻልም።በምንም መልኩ ክፍያው ላይ ተጽዕኖ ሳይኖረው ለአራጅ እንደተጨማሪ ስጦታ ወይም ሰደቃ መስጠት ግን ይቻላል።

ኡስታዝ አሕመድ አደም