Get Mystery Box with random crypto!

ዑዝር ላይ ያሉ ወንድም/እሕቶች የአረፋ ቀንን እንዴት ያሳልፉ? የዐረፋን ቀን ፆም ከልቡ ለመፆም | Ahmedin Jebel - አሕመዲን ጀበል

ዑዝር ላይ ያሉ ወንድም/እሕቶች የአረፋ ቀንን እንዴት ያሳልፉ?

የዐረፋን ቀን ፆም ከልቡ ለመፆም የወሰነ ወንድም/እሕት፣ ነገር ግን በዑዝር ሰበብ (በሽታ፣ ሰፈር፣ ሐይድ፣ የወሊድ ደም፣ ወዘተ) ቀኑን መፆም ባይችልስ? ለሚለው ሸይኽ ስዑድ ከረመዷን ዐሽሩል አዋኺር ጋር ተመሳሳይ ጥያቄ ቀርቦላቸው መልስ ስለሰጡበት: መልሱን እንዲህ አቅርበነዋል:–

ተጠያቂው ሸይኽ ኻሊድ ቢን ሱዑድ

ጥያቄ፡- አሰላሙ ዐለይኩም ወራሕመቱላሂ ወበረካቱሁ ያ ሸይኽ! በሐይድ ላይ ያለች ሴት ወይም የወለደች እንዴት አድርጋ የረመዷንን የመጨረሻ አስር ቀናት መጠቀም ትችላለች? ያ ሸይኽ! እኔ በጣም በመጨናነቄ ሰበብ እርሶ እንዲረዱኝና እንዲሁም ሀሳቡና ጭንቀቱ እንዲቀልልኝ እፈልጋለሁ፡፡ አላህም የለይለቱል-ቀድርን ምንዳ እንዳይከለክለኝ ዱዓእ እንዲያረጉልኝ እማጸንዎታለሁ፡፡

ምላሽ፡- ወዐለይኩሙ-ሰላሙ ወራሕመቱላሂ ወበረካቱሁ የተከበርሽ እህቴ! ከሁሉ በፊት ቀድመሽ ልታውቂው የሚገባ ነገር፡- የወር አበባና የወሊድ ደም አላህ እሱ ብቻ ለሚያውቀውና ለፈለገው ጥበብም በአንቺ ላይ የወሰነው የተፈጥሮ ህግ መሆኑን ነው፡፡ መልካም ነገር ደግሞ አላህ ላንቺ የመረጠልሽ ነገር እንጂ አንቺ ለራስሽ የመረጥሽው አይደለም፡፡ አላህ ለወሰነው (ቀዷ ወል-ቀደር) እጅ ስጪ፡፡ ደግሞም አንቺ ለነፍሲያሽ ከጓጓሽው በላይ አላህ ላንቺ አዛኝ ጌታ መሆኑን እርግጠኛ ሁኚ፡፡

በተጨማሪም ልታውቂው የሚገባ ነገር፡- አንድ ሰው በዑዝር ወቅት በሰላም ጊዜ ይፈጽመው የነበረውን ነገር መቀጠል ቢያቅተው እንኳ አጅሩ ግን እንደማይቋረጥበት ነው፡፡ ተወዳጁ የአላህ ነቢይም (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) እንዲህ ብለዋል፡- "አንድ የአላህ ባሪያ ከታመመ ወይም ከመኖሪያ ክልል ርቆ (ሙሳፊር የሚሰኝበትን ያህል) ከተጓዘ: ጤነኛና የአካባቢው ነዋሪ ሆኖ ይፈጽመው የነበረው (መልካም ስራ) ሳይቋረጥ ይጻፍለታል" (ቡኻሪይ 2996)፡፡

አንቺ ደግሞ በሐይድ ወቅት ያለ ጥርጥር ዑዝር ያለሽ ነሽ፡፡ ምክንያቱም፡- ያለ ምርጫሽና ፍላጎትሽ የመጣ በመሆኑ፡፡ እንዲሁም ልትከላከዪውና ልታስቀሪው የማትችዪው ነገር ስለሆነ፡፡ በድጋሚም ማወቅ ያለብሽ ነገር፡- አንድ የአላህ ባሪያ አንድን ነገር ለመስራት ከልብ የቆረጠ ኒያ ካለው ከዛም ያንን የነየተውን ነገር ለመስራት ድንገተኛ ሁኔታና ክስተት ቢከለክለውና ቢያግደው፤ አላህ ግን እንደሰራው በመቁጠር ሙሉ አጅሩን የሚጽፍለት መሆኑን ነው፡፡ ይህንን አስመልክቶ የአላህ ነቢይም (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) እንዲህ ብለዋል፡-

"በመዲና ውስጥ ሰዎች አሉ፡፡ እናንተ አንድንም ሸለቆ አታቋርጡም መንገድንም አትዘልቁም እነሱ በአጅር ቢጋሯችሁ እንጂ፡፡ ከናንተው ጋር አብረው እንዳይጓዙ ዑዝር ከለከላቸው" (ቡኻሪይ)፡፡

በሌላ ቅዱስ ትምህርታቸው ላይ ደግሞ እንዲህ አሉ፡- "አላህን በፍጹም ልቡ ሸሂድነትን (ለዲን ሰማእት ሆኖ መሞትን) እንዲወፍቀው የለመነ ሰው ቀኑ ደርሶ በፍራሹ ላይ እንኳ ቢሞት(በኒያው ሰበብ) የሸሂዶችን (ሰማእታት) ደረጃ ያጎናጽፈዋል" (ሙስሊም)፡፡

ታዲያ አንቺም እንደ ሌሎቹ ሙስሊም እህቶችሽና ወንድሞችሽ እነዚህን አስር ቀናት በዒባዳ ለማሳለፍ ገና ከመጀመሪያው የነየትሽና የጓጓሽለት ከነበር ጌታሽ ኒያሽን ከንቱ እንደማያረግብሽ ባለሙሉ ተስፋ ሁኚ አብሽሪ፡፡

ሌላው ደግሞ ይህ የወር አበባ ወይም የወሊድ ደም ሶላት ከመስገድ፣ ጾም ከመጾምና መስጂድ ከመግባት ቢያግድሽም ሌሎች ያልተከለከልሻቸው ዒባዳዎች መኖራቸውንም አትዘንጊ፡፡ ከነዚም መካከል፡- (ሱብሐነላህ፣ አልሐምዱ ሊላህ፣ ላኢላሀ ኢለላህ፣ አላሁ አክበር…) አዝካሮችን ማለት፣ ዱዓእ ማድረግ፣ በነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ላይ ሶላዋት ማውረድ፣ ሶደቃ ማውጣት፣ ኢስቲግፋር ማብዛት፣ በአላህ ስሞችና በሱ ስራዎች ማስተንተንን የመሳሰሉት፡፡

በመጨረሻም ማወቅ ያለብሽ ነገር፡- እነዚህ አስር ቀናት በዑዝር ሰበብ ሊያመልጠኝ ነው ብለሽ ማሰብና መጨነቅሽ በራሱ የሚያመላክተው የኢማንሽን ታላቅነት፣ ወደ አላህ ለመቃረብ ያለሽን ጉጉት ነው ኢንሻአላህ፡፡ ስለዚህም የቻልሽውን ያህል ኸይር ስራ ለመስራት ታገዪ፣ ተረጋጊ አትጨናነቂ፣ አይዞሽ፣ አላህ ላይ ያለሽን ተስፋ ከፍ አድርጊ እሱ ኒያሽንም ሆነ መልካም ስራሽን አያባክነውም ምንዳውንም አይከለክልሽም፡፡ የሱ እዝነት አንቺን ብቻ ሳይሆን ዓለሙን ሁሉ የሰፋና ያካለለ ነውና፡፡ ወሰሊላሁመ ወሰለም ዓላ ነቢዪና ሙሐመድ ወዓላ ኣሊሂ ወሰሕቢሂ ወሰለም፡፡

ስለዚህ ነገ ጁምዓ የዐረፋ ቀን ነውና ይህን ቀን እንጹመው እንዳያመልጠን፡፡ አላህ ይወፍቀን አሚን፡፡

ኡስታዝ አቡ ሃይደር