Get Mystery Box with random crypto!

በጦርነቱ ጉዳት ከደረሰባቸው 536 የጤና ተቋማት 463ቱ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፤ =====≡= | Affini Media and Communication

በጦርነቱ ጉዳት ከደረሰባቸው 536 የጤና ተቋማት 463ቱ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፤
=====≡===================
አፊኒ ነሐሴ 16፣2014
ሀዋሳ
በአሸባሪው የሕወሓት ወረራ በአፋርና አማራ ክልሎች ጉዳት ከደረሰባቸው 536 ጤና ተቋማት ውስጥ 463 የሚሆኑት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ከዚህ ውስጥ 319 ጤና ተቋማት በከፊል አገልግሎት የጀመሩና ወደ ተሟላ አገልግሎት ለመመለስ ተጨማሪ ሥራ የሚጠይቁ መሆናቸውንም ጠቁሟል፡፡

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደገለጹት፤ በአሸባሪው የሕወሓት ወረራ በአፋርና አማራ ክልሎች ጉዳት ከደረሰባቸው 536 ጤና ተቋማት ውስጥ 463 የሚሆኑት አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ 319 ጤና ተቋማት በከፊል አገልግሎት የጀመሩና ወደ ተሟላ አገልግሎት ለመመለስ ተጨማሪ ሥራ የሚጠይቁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተከሰተው ጦርነት ጉዳት ከደረሰባቸው ተቋማት ውስጥ የጤና ተቋማት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ ያሉት ሚኒስትሯ፤ ለዚህ ምላሽ ለመስጠት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተለያዩ የድንገተኛ ምላሽ ሥራዎችን ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ሲሠራ ቆይቷል፡፡
ይህን ለማስተግበር እቅድ ተዘጋጅቶ እንደ ሴክተርና ከሌሎችም ሴክተሮች ጋር በገንዘብ ሚኒስቴር በሚመራ የተጀመሩ የመልሶ ግንባታ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአማራ ክልል ከተጎዱት 40 ሆስፒታሎችና 453 ጤና ጣቢያዎች 10 ሆስፒታሎችና 134 ጤና ጣቢያዎች ወደ ሙሉ አገልግሎት መመለሳቸውን ጠቅሰው፤ 25 ሆስፒታሎችና 273 ጤና ጣቢያዎች ደግሞ ከፊል አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በክልሉ በርካታ ጤና ኬላዎች በመልሶ ግንባታ ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውሰው፤ አምስት ሆስፒታሎች እና 46 ጤና ጣቢያዎች አሁንም ድረስ አገልግሎት መስጠት እንዳልቻሉ አክለው ገልጸዋል፡፡

በአፋር ክልል ጉዳት ከደረሰባቸው ሁለት ሆስፒታሎችና 41 ጤና ጣቢያዎችም አንድ ሆስፒታልና 20 ጤና ጣቢያዎች ታድሰው በከፊል አገልግሎት መጀመራቸውን አመልክተው፤ አንድ ሆስፒታልና 21 ጤና ጣቢያዎች እስካሁን ወደ ሥራ መመለስ አልተቻለም፡፡

በሁለቱም ክልሎች ወደ ሥራ ያልገቡ ቀሪዎችን ተቋማት ወደ ሥራ ለመመለስ የጸጥታ ችግር እንቅፋት መሆኑንም መግለጻቸውን የኢፕድ ዘገባ ያመለክታል፡፡

ከክልል ጤና ቢሮዎች፣ ከፌዴራል ሆስፒታሎች፣ ኤምባሲዎች፣ ከልማት አጋር ድርጅቶች፣ ዳያስፖራዎችና የኢትዮጵያ ወዳጆች በመተባበር በተሠራው ሥራ መሠረታዊና ሕይወት አድን የሆኑ ጤና አገልግሎቶች በግጭቱ በተጎዱ ጤና ተቋማት ውስጥ ማስጀመር ተችሏል ያሉት ዶክተር ሊያ፤ እስካሁን ድረስ ከባለድርሻ አካላት በግብአት፣ በመሳሪያ በገንዘብ 600 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሀብት ተሰብስቧል ብለዋል፡፡

እስካሁን ድረስ በግለሰብና ተቋም ደረጃ እገዛ ላደረጉ ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበው፤ በርካታ ጤና ተቋማት ወደ ሥራ መመለሳቸው አበረታች ቢሆንም ሁሉም ተቋማት የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ከፍተኛ ሥራ ስለሚጠይቅ አሁንም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
(ኢዜአ)
አፊኒ_ሚዲያና_ኮሙኒኬሽን
#Affini_Media_Communication
ትኩስ እና እውነተኛ መረጃዎችን ለማግኘት ይከታተላሉ
ዩቲዩብ:https://youtube.com/channel/UCzxVCZUtW-XmosukNkCXZEA
telegram:https://t.me/affinimedia
https://t.me/affinihasaaw