Get Mystery Box with random crypto!

ራጂሽ ኻናን በጨረፍታ ------- አፈንዲ ሙተቂ -------- አሁን በሕይወት የለም። በሕይወት ሳ | AfandishaHarar 🇪🇷🇪🇹🇯🇴🇸🇩🇪🇭🇸🇴

ራጂሽ ኻናን በጨረፍታ
-------
አፈንዲ ሙተቂ
--------
አሁን በሕይወት የለም። በሕይወት ሳለ የህንድ ሲኒማን በዓለም ዙሪያ ካስተዋወቁት ዓለም አቀፍ አክተሮች አንዱ ነበረ። በተለይም በ70ዎቹ እና በ80ዎቹ ኮከብ የህንድ አክተር የነበረው እርሱ ነው። ታዋቂዎቹ አክተሮች አሚታብ ባችቻን እና ሚቱን ቻክራቦርቲ እንደ እርሱ የሚያደንቁት የሲኒማ ጥበበኛ አልነበረም። በመሆኑም ተመልካች ለመሳብ ሲሉ በፊልሞቻቸው ጣልቃ ተጋባዥ ተዋናይ (guest star) አድርገው ያስገቡታል።

ራጂሽ ኻና የታዋቂዋ አክትረስ እና ሞዴሊስት የዲምፕል ካፓዲያ ባለቤት ነበር። ከባለቤቱ ጋር ለአስር ዓመት ከኖረ በኋላ ትዳራቸው በ1984 በፍቺ ተጠናቅቋል። ሁለቱ አክተሮች ሁለት ሴት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን ልጆቹም እንደ ወላጆቻቸው አክተሮች ናቸው።
------
ራጂሽ ኻና በዘመኑ በኢትዮጵያ እና በኤርትራም ዝነኛ ሆኖ ነበር። የኛ ታላላቆች እርሱን የሚያስታውሱት "Haathi Meri Saathi" በተሰኘ ፊልሙ ነው (ብዙዎች ርእሱን በአማርኛ ተርጉመው "ዝሆን ጓደኛዬ" ይሉታል)። የኔ ትውልድ አባላት ራጂሽ ኻናን በደንብ የምናስታውሰው ግን "Disco Dancer" በተሰኘው ፊልም ውስጥ የጂሚ አጎትና አሰልጣኝ ሆኖ በታየባቸው ሁለት ትዕይንቶች ሳቢያ ነው።

ታዲያ በOnline በነበረኝ ቆይታ እንደታዘብኩት ከኤርትራዊያንና ከኢትዮጵያዊያን መካከል ራጂሽ ኻናን በደንብ የሚወዱትና የሚያደንቁት የአስመራ እና የድሬ ዳዋ ልጆች ናቸው። በፌስቡክ ገጼ ላይ ስለሚቱን እና አሚታብ ስጽፍ በውስጥ መስመር እየመጡ "እስቲ ስለ ራጂሽ ኻና አንድ ነገር በል" ይሉኛል።
------
ራጂሽ ኻና እንደ አሚታብ፣ ዳርሜንድራ፣ ጄንተንድራ እና ሚቱን ቻክራቦርቲ የአክሽን ፊልሞችን ብዙም አይነካካም። ፊልሞቹ በአብዛኛው "drama" ናቸው። ደግሞም እስከ መጨረሻው ድረስ ስሜትን የመቆጣጠር ሀይል አላቸው። ይህንን ጽሑፍ የጻፍኩት "Swarg" የሚባል ፊልሙን በማየት ላይ ሳለሁ ስሜቴ ፍንቅል ብሎ በመውጣቱ ነው። ከእርሱ ፊልሞች መካከል ብዙዎቹ በጅምሩ ላይ ትራጀዲ ሆነው ሰውን ካስለቀሱ በኋላ በአፈጻጸም ላይ postive ትዕይንት ያስከትሉና የደስታ ስሜትን በመላው የሰውነት አካል ይረጫሉ።

Anand የተሰኘው ፊልሙ ግን ከጅምሩ እስከ መጨረሻው በትራጄዲ ነው የሚያልቀው። ራጂሽ ኻና በዚያ ፊልም የዓመቱ ኮከብ አክተር ተብሎ ተሸልሞበታል። ፊልሙ የካንሰር በሽተኛ ሆኖ ዕለተ ሞቱን በደስታ ስለሚጠባበቅ ወጣት ነው የሚተርከው። በፊልሙ ውስጥ ሁለት ተጻራሪ ስሜቶች ይንጸባረቃሉ። በአንድ በኩል እርሱን የሚከታተለው ዶክተር፣ መምህሩ፣ ዘመዶቹ፣ ጎረቤቶቹ፣ የስራ ባልደረቦቹ ወዘተ.. ወጣቱ Anand በቅርቡ የሚሞት መሆኑ አሳዝኖአቸው ይተክዛሉ። ያለቅሳሉ። በሌላ በኩል ግን Anand "በቅርቡ መሞቴ የማይቀር እንደሆነ ተረጋግጧል። እርሱን የማስቆምበት ሃይል የለኝም። ቢሆንም እስክሞት ድረስ ለምን በሃሳብና በሰቀቀን ራሴን አሰቃያለሁ? በቀረችኝ ጊዜ በደንብ ተደስቼ መሞት አለብኝ" እያለ ከማንም ጋር ሲቃለድና ሲጫወት ይውላል (BBC የዛሬ አስር ዓመት ገደማ "እስከ ዛሬ የተሰሩት ምርጥ 100 የህንድ ፊልሞች" በማለት ባካሄደው ምርጫ ራጂሽ ኻና የተወነበትን Anand በአምስተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጦታል)።
------
ራጂሽ ኻና በአጭሩ እንዲህ ነበር። እስቲ Wi-Fi ካላችሁ በእረፍት ጊዜያችሁ እነዚህን ፊልሞች በYouTube ተመልከቷቸው። እነዚህን ፊልሞች ካያችኋቸው በኋላ "የህንድ ፊልሞች ዕድገት ወደ ኋላ እየሄደ ነው" የምትሉ ይመስለኛል።

Anand
Avtaar
Amrit
Nazrana
Swarg
------
ሰላም እንሁን!
ሰላም ለሀገራችንና ለህዝባችን!
ሰላም በመላው ዓለም ይስፈን!!
------
አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 24/2014