Get Mystery Box with random crypto!

ባሳለፍነው እሁድ ወደ አንጎለላ ተጉዘን ነበር ነሐሴ 22 ቀን 2014 ዓ.ም አንጎለላ / እንቁላ | Guzo Adwa updates

ባሳለፍነው እሁድ ወደ አንጎለላ ተጉዘን ነበር

ነሐሴ 22 ቀን 2014 ዓ.ም
አንጎለላ / እንቁላል ኮሶ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ
በቀድሞው ሸዋ ክፍለ አገር ተጉለት እና ቡልጋ አውራጃ
አንጎለላ ቀበሌ ልዩ ቦታው እንቁላል ኮሶ በተባለ መንደር  ከእናታቸው ወ/ሮ እጅጋየሁ ለማ እና ከአባታቸው ኃይለ መለኮት ሣህለሥላሴ ነሐሴ 12 በዕለተ ቅዳሜ 1836 ዓ.ም  ተወለዱ።

በዚህችው ቀን ከ4 አመታት ቀድም ብሎ የኋላዋ ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ተወልደውባታለችና፤ ነሐሴ 12 ቀን ታሪካዊ ግጥምጥም አላት።

በተመሳሳይ መልኩ በፈረስ ስማቸው አባ ጎራው በመባል የሚታወቁት በዓድዋ ጦርነት እና ከዛም  ቀደም ብሎ  ከኢጣሊያ ጋር በተደረጉ የአምባላጌ እና የመቀሌ ጦርነቶች ላይ በጀግንነት የተዋጉ እና ድል ያደረጉ የጦሩ መሪ ጀግናው ፊታውራሪ ገበየሁ ገቦም ተወልደውባታል።

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ እና ፊታውራሪ ገበየሁ ገቦ በተመሳሳይ ቀን በተመሳሳይ ዓመት በአንጎለላ ተወልደው በተመሳሳይ ቀን በጥንታዊው የአንጎለላ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ክርስትና ተነስተዋል። (አንጎለላ ኪዳነምህረት የሄደ ሰው በዓድዋ የወደቀው የጀግናው ፊታውራሪ ገበየው ክቡር አስክሬን በመስታወት ሳጥን ውስጥ ኾኖ ማየት ይችላል)

እንዳለፉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት ሁሉ ዘንድሮም ከነሐሴ 12 ጀምሮ በተለያዩ ሁነቶች ጀግኖቻችን በክብር ያስረከቡልንን አገር ለማጽናት አደራቸው ማሰብ ይረዳን ዘንድ ልደታቸውን ምክንያት አድርገን ቀናቱን ስንዘክር ቆይተን ደማቁን መዝጊያ በትውልድ መንደራቸው በማድረግ አጠናቀናል።

በጉዟችን ከ ሶስት ኪሎ ሜትር  ያልበለጠ የእግር ጉዞ በአንጎለላ የገጠር መንደሮች ውስጥ አድርገናል።  በዘመኑ አጠራር በሰሜን ሸዋ አስተዳደር ዞን ውስጥ ከሚገኙ ወረዳዎች አንዱ በሆነው ባሶና ወራና ወረዳ አንጎለላ ቀበሌ ውስጥ ወደ ምትገኘው እና በአጼ ናዖድ ዘመነ መንግስት በ1487 ዓ/ም በተገደመችው ጥንታዊቷ አንጎለላ ጽርሐ አርያም ሰሚነሽ ኪዳነ ምህረት ገዳምን ጎብኝተናል። 

ከገዳሙ  በስተ ምዕራብ ቀረብ ብሎ የሚገኘው ለዘመናት ተቀበሮ የቆየው እና በጉዞ ዓድዋ ግንባር ቀደምነት ከፍተኛ ውትወታ ተደርጎበት ጥበቃ እንዲያገኝና የተቀበረው ቤተመንግስት በቁፋሮ የማውጣት ስራው የተጀመረው በሙያተኞች የመካከለኛው ዘመን ሥነ- ሕንጻ መኾኑ የሚታምነና   የአካባቢው ማሕበረሰብ በተለምዶ የንጉስ ሳህለ ሥላሴ ቤተ መንግስትንም እያለ የሚጠራውን ቦታ ዘንድሮም ጎብኝተናል።

ይህንን ቤተ መንግስት ከተቀበረበት እስከ መጨረሻው የማውጣቱ ስራና ቦታውን ይበልጥ ለሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ቱሪስቶች ለጉብኝትም ይሁን ለጥናት እና ምርምር  ምቹ የማድረግ ስራው ከአመት አመት ከመሻሻል ይልቅ እንደውም በዚያው ተዳፍኖ ስራ መቆሙን ዳግም ታዝበናል።

በዚህ ጉዞ የክብር እንግዳችን የነበሩት የኢትዮጵያ ቅርስ ባላደራ ማኅበር ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መቆያ ማሞ በዕለቱ የነበረንን ትዝብት ተጋርተውናልና፤ በቀጣይ  ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር ለችግሩ  አንድ መፍትሔ ያመጣሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

በመጨረሻም በደማቅ ሀገርኛ  ድግስ ተቀብሎ ፣ ተንከባክቦ እና መርቆ የሸኘንን ወዳጃችንን ወርቅአገኘው  ገ/ማሪያም  እንዲሁም የዚህ ጉዞ ድምቀት ለነበራችሁ የታሪክ እና የጉዞ ወዳጅ ቤተሰቦቻችን ከልብ ለማመስገን እንወዳለን።
__

የጉዞ ዓድዋ ሃይኪንግ የዓመቱ የመጨረሻ ጉዟችን የፊታችን እሁድ (ነሀሴ 29) ወደ ተወዳጁ ''እንሳሮ''
ይካሄዳል።

ውስን ቦታዎች ብቻ ስለሚቀሩን በተከታዮቹ አድራሻዎች ፈጥነው  ይደውሉ
+251942545470 ፣ +251964423971
ወይንም  @guzoadwahiking @guzoad @miki_2012 አጭር የፅሁፍ መልዕክት ይላኩልን ።

#guzoadwahiking #ethiopia #landoforigins #angolela #semienshewa #dagmawimeneliek #guzoadwa