Get Mystery Box with random crypto!

አይዟችሁ!     ' ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፣  እግዚአብሔርም  ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የምስ | Adoni Gospel channel

አይዟችሁ!


    " ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፣  እግዚአብሔርም  ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የምስራቅ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው:: ባሕሩንም አደረቀው፣ ውኃውም ተከፈለ፤ የእሥራኤልም ልጆች በባሕሩ መካከል በየብስ ገቡ፣ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆነላቸው…ንጋትም በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር በእሳትና በደመና ዓምድ የግብጻውያንን ሠራዊት ተመለከተ…አወከ…አሠረ…ወደ ጭንቅም አስገባቸው፣ ግብጻውያንም እግዚአብሔር በግብጻውያን ላይ ይዋጋላቸዋልና ከእሥራኤል ፊት እንሽሽ አሉ” (ዘጸ 14፣21-25)


      እግዚአብሔር አሰራሩ ብዙና ልዩ ልዩ ነው ከሰው አዕምሮም በላይ ነው። በዚህ ስትጠብቁት በዚያ ይመጣል። በዚህ ክፍል ላይ እግዚአብሔር አደግድጎ የሚሰራው ፀሐይ ደምቃ በወጣች ሰዓት ሳይሆን ጨለማው የሚዳሰስ በሆነበት ጊዜ ነው።

     ሌሊት እንቅስቃሴ ሁሉ የሚቆምበት፣ ብዙ ነገሮች ዝግ የሚሆኑበት ነው። ለእስራኤል በሌሊት የሚታያቸው የሚከተላቸው የፈርዖን ጦርና ወታደር ነው። ጠላት ቢገሰግስ ቢመጣ እግዚአብሔር ሳይቸኩልና ሳይጣደፍ ስራውን ይሰራ ነበር። ለእስራኤል ጨለማ ቢሆንም ለእግዚአብሔር ግን የስራ ሰዔት ነበር።

     ለሊቱን ሁሉ ይላል፦ አዎ ለሊት ሁሉ ሲተኛ፣ ድምፅ ሁሉ ሲጠፋ፣ የኛ ነገር ያበቃ ያከተመ በሚመስልበት ሰዓት፣ ተስፋ ያደረግነው ነገር የሞተ በሚመስልበት፣ ምንም የሚታይ ነገር በጠፋበት ወቅት፣ ብንጠራው የሚደርስልን ብንሸሽ የሚከፍትልን ወዳጅ በሌለ ሰዓት እግዚአብሔር ለእኛ እየሰራልን ነው። የእግዚአብሔር የስራ ውጤት ብልሽት የለውም ውብ ያደርገዋል።

    እንደ እስራኤል ሄዳችሁ ብዙ ተጉዛችሁ አላሳልፍ ባለ ችግር ቆማችሁ ይሆናል፤ ብዙ ነገር ጨልሞባችሁ ይሆናል፤ ከፊትም ከኋላም ሞት እየሸተታችሁ፣ በሁሉ ነገር አበቃ ብላችሁ ደምድማችሁ ይሆናል። ነገር ግን የሚወዳችሁ እግዚአብሔር እንዳይረዳችሁ ችግራችሁ አይከለክለውም፣ ጨለማችሁ አያግደውም ያስጨነቃችሁን ያስጨንቀዋል፣ ባህሩን ያደርቀዋል፣ ውሀውን እንደ ግንብ ያቆመዋል፣ ያሳደዳችሁን ጠላት በደመናና በእሳት አምድ ይመክተዋል። ያን ጊዜ በደስታ ትሻገራላችሁ። ለሊት ብቻ ሆኖ አይቀርምና ተሻግራችሁ በንጋት እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም ብላችሁ ትቀኛላችኩ። አይዟችሁ እግዚአብሔር ድንቅን ሊያደርግላችሁ በስራ ላይ ነው።

አዶኒ

በድጋሚ የተለጠፈ August 25/2019 የተፃፈ

Join @adonigospel
@adonigospel