Get Mystery Box with random crypto!

ዐበይት ዜናዎች 1፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ትግራይ ክልልን ለሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ክፍት እንዲ | አድማስ ሬድዮ- Admas Radio

ዐበይት ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ትግራይ ክልልን ለሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ክፍት እንዲያደርግ የሚጠይቅ ዘመቻ እንደጀመረ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ረድዔት ድርጅቶች ዕርዳታ ለማጓጓዝ ያቀረቧቸው በርካታ ጥያቄዎች ፍቃድ እንዳላገኙ የገለጠው ድርጅቱ፣ የረድዔት ሠራተኞችም ለመግባት ፍቃድ እንዳላገኙ አውስቷል፡፡ በክልሉ የሰላማዊ ሰዎች ጭፍጨፋ፣ የዘፈቀደ የከባድ መሳሪያ ድብደባ፣ ከፍርድ ውጭ ግድያ እና ዝርፊያ ስለመበራከቱ በቂ ማስረጃ አለ- ብሏል አምነስቲ፡፡

2፤ በኢትዮጵያው ትግራይ ክልል እስካሁን ትርጉም ያለው ዕርዳታ ለተረጅዎች እንዳልደረሰ የኖርዌይ ስደተኞች ካውንስል ዋና ጸሃፊ ጃን ኢግላንድ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ ማዕከላዊ እና ምዕራባዊ ትግራይ እንዲሁም 2 የኤርትራዊያን ስደተኛ መጠለያዎች ለረድዔት ድርጅቶች እስካሁን ተደራሽ አልሆኑም፡፡ ተደራሽ የሆኑት መቀሌ እና ለአውራ ጎዳናዎች ቅርብ የሆኑ ተረጅዎች ብቻ ናቸው፡፡ ለረድዔት ድርጅቶች ፍቃድ አሰጣጡ ወጥነት የሌለው እና የተንዛዛ እንደሆነ የጠቀሱት ዋና ጸሃፊው፣ እንዲህ ያለ የተጓተተ አሠራር አይቼ አላውቅም ብለዋል፡፡ መንግሥት ሁኔታዎችን ማስተካከል ቢፈልግ ባንድ ቀን ማስተካከል ይችላል በማለትም አክለዋል፡፡ ረድዔት ድርጅቶች የችግሩን ክብደት አጉልተው አለማሳየታቸውም ውድቀት እንደሆነ አውስተዋል፡፡

3፤ በፊንላንድ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር የተመራ የአውሮፓ ኅብረት የሰብዓዊ ሁኔታ አጣሪ ቡድን ወደ ኢትዮጵያው ትግራይ ክልል እንደሚጓዝ ዩሮ ኦብዘርቨር ድረገጽ ተሰምቷል፡፡ የኅብረቱ ልዑክ በቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት ወደ ሥፍራው ይጓዛል ተብሏል፡፡ በክልሉ ግጭት 3 የውጭ መንግሥታት ተሳትፈዋል ያሉት ውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ፣ ዐለማቀፉ ኅብረተሰብ በክልሉ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲያጣራ ጠይቀዋል፡፡

4፤ በአማራ ክልል ከሌሎች ክልሎች የተፈናቀሉ 270 ሺህ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ኢትዮ ኤፍኤም ዘግቧል፡፡ ተፈናቃዮቹ በተለያዩ ማንነትን መሠረት ባዳረጉ ጥቃቶች እና ግጭቶች ምክንያት ከትግራይ፣ ከኦሮሚያ፣ ደቡብ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተፈናቀሉ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ተፈናቃዮች የተጠለሉት፣ በምዕራብ ጎጃም፣ ሰሜን ሸዋ፣ ሰሜን ወሎ እና ራያ ቆቦ ነው፡፡

5፤ ደቡብ ሱዳን ከዐለም ሀገራት በሙስና ከመጨረሻው ሁለተኛውን ደረጃ እንደያዘች የሀገራትን የሙስና ደረጃ የሚያወጣው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ባወጣው አዲስ ሪፖርት አስታውቋል፡፡ ሱማሊያ ደሞ ሦስተኛ ደረጃ ይዛለች፡፡ ደረጃው የወጣው ከ180 ሀገራት ሲሆን፣ መለኪያው በመንግሥት ተቋማት የሚፈጸም ሙስና ነው፡፡

6፤ አልሸባብ በሞቃዲሾ ባለሥልጣናት እና ፖለቲከኞች በሚያዘወትሩት አንድ ትልቅ ሆቴል ላይ በፈጸመው ጥቃት 15 ሰዎች እንደተገደሉ የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል፡፡ በአሸባሪዎቹ ጥቃት ከተገደሉት መካከል የቀድሞ መከላከያ ሚንስትር የነበሩ አንድ ጀኔራል ይገኙበታል፡፡ አሸባሪዎቹ ሆቴሉን ሰብረው የገቡት ትናንት ሌሊት ሲሆን፣ ዛሬ ከ7 ሰዓታት ተኩስ ልውውጥ በኋላ የመንግሥት ወታደሮች ሆቴሉን ተቆጣጥረዋል፡፡ ጥቃቱን ያደረሱት 4ቱ ታጣቂዎች ተገድለዋል ተብሏል፡፡

(ዋዜማ ራዲዮ)
@admasradio