Get Mystery Box with random crypto!

ከአጭበርባሪዎች ይጠንቀቁ! የኤሌክትሪክ ቆጣሪ እናስገባለን በሚል ሰበብ ህገወጥ ድርጊት የሚፈፅሙ | አድማስ ሬድዮ- Admas Radio

ከአጭበርባሪዎች ይጠንቀቁ!

የኤሌክትሪክ ቆጣሪ እናስገባለን በሚል ሰበብ ህገወጥ ድርጊት የሚፈፅሙ ግለሰቦች ስላሉ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሳሰበ።

ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር ተያይዞ ለሚቀርቡ ሌሎች ማንኛውም ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጠውም ይህ ተቋም ሳለ ከህጋዊ አሰራር ውጭ የተቋሙ ሠራተኛ በመምሰል እኩይ ዓላማ ያነገቡ ግለሰቦች የኤሌክትሪክ ቆጣሪ እናስገባለን በሚል በህገ-ወጥ መንገድ ከህብረተሰቡ ገንዘብ የሚቀበሉ ግለሰቦች መኖራቸውን ተቋሙ በደረሰው ጥቆማና ባደረገው ማጣራት ማረጋገጡን ገልጿል።

ለአብነትም ነዋሪነቷ በአዲስ አበባ ከተማ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 የሆነች አንዲት ግለሰብ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የማያውቀው ነገር ግን "ከተቋሙ ነው የመጣነው ቆጣሪ እናስገባልሻለን" ብለው በማታለል ገንዘብ ተቀብለዋት ህጋዊ ያልሆነ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ ገጥመውላታል። ግለሰቧ ለእነዚህ ሰዎች በሐሰተኛ እሴት ታክስ ደረሰኝ 12 ሺህ ብር የከፈለቻቸው ቢሆንም ድርጊቱ ከተቋሙ እውቅና ውጪ እንደነበር ነው የተጠቀሰው።

በመጨረሻም በተደረገው ማጣራት የተገጠመው ቆጣሪ ህገወጥና ትክክለኛውን የአሰራር ስርዓት ተከትሎ የተፈፀመ አለመሆኑን ተደርሶበት የተገጠመላት ቆጣሪ አገልግሎት እንዳይሰጥ መደረጉንም ነው የተገለጸው። ህብረተሰቡ እንደነዚህ አይነት መሰል እኩይ ድርጊቶች ሊያጋጥመው ስለሚችል አስፈላጊ ጥንቃቄ እንዲወስድ ተቋሙ ያሳስባል። ተቋሙ የአዲስ ቆጣሪ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥበት የራሱ የሆነ የአሰራር ስርዓት የዘረጋ መሆኑ ታውቆ፤ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስቧል።

(Ebc)
@admasradio