Get Mystery Box with random crypto!

በሱዳን በተነሳው ግጭት የኢትዮጵያ ጣልቃ ገብነት የለም- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሱዳን የኢትዮጵያ | አዲስ ዘይቤ ~ Addis Zeybe

በሱዳን በተነሳው ግጭት የኢትዮጵያ ጣልቃ ገብነት የለም- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

በሱዳን የኢትዮጵያውያ ዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ግብረ ሀይል ተቋቁሟል

ሚያዝያ 14 ፤ 2015 ዓ.ም.

(አዲስ ዘይቤ፤ አዲስ አበባ) እስካሁን ከ300 በላይ ሱዳናውያን እንዲሁም ከአምስት የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን የሞቱበት ግጭት ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ጣልቃ አልገባሁም አለ።

በሱዳን ግጭት የኢትዮጵያና ኤርትራ እጅ አለበት የሚል መረጃ መሰራጨቱን ተከትሎ በሱዳን የሚኖሩ የሀገራቱ ዜጎች የጥቃት ሥጋት ውስጥ መግባታቸውን ለአዲስ ዘይቤ ገልፀው ነበር።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “በሀገሪቱ ለተፈጠረው ችግር የኢትዮጵያ ጣልቃገብነት እንዳለ የተሠራጨው መረጃ ሀሰተኛ ነው” ብሏል። መረጃውን የሚያሰራጩ አካላትም “በሱዳን የተፈጠረውን ችግር አካባቢያዊ የማድረግ ፍላጎት አላቸው” ሲል የኢትዮጵያ መንግስት ወቅሷል።

ኢትዮጵያና ሱዳን ፅኑ ወዳጅነት አላቸው ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም፣ ችግሩ እንዲፈታ ኢትዮጵያ በየትኛውም ሁኔታ ከሱዳናዊያን ጎን ናት ብለዋል።

በሌላ በኩል የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ከተለያዩ መስሪያ ቤቶችና አጎራባች ክልሎችን በአባልነት ያቀፈ ግብረ ኃይል  መቋቋሙን ቃል አቀባዩ መናገራቸውን ኢዘኤ ዘግቧል። ስለተገደሉትና ስለቆሰሉት ኢትዮጵያውያን ቃል አቀባዩ በዘገባው ያሉት ነገር የለም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሱዳን ተቀናቃኝ ሃይሎች ተኩስ አቁመው ወደ ሰላም ስምምነት እንዲመጡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።

አዲስ ዘይቤ በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በተሰራጨው መረጃ ዙሪያ ያንጋገረችበት ዘገባ - https://am.addiszeybe.com/featured/addis-ababa/current-affairs-am/Ethiopians-are-afraid-of-being-attacked-in-the-Sudanese-conflict