Get Mystery Box with random crypto!

በኮምቦልቻ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ከነበሩ ግለሰቦች 2 ሰዎች ሲሞቱ ከ12 የሚበልጡ ተጎድተዋል ተ | አዲስ ዘይቤ ~ Addis Zeybe

በኮምቦልቻ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ከነበሩ ግለሰቦች 2 ሰዎች ሲሞቱ ከ12 የሚበልጡ ተጎድተዋል ተባለ

ሚያዝያ 3፤ 2015 ዓ.ም.

(አዲስ ዘይቤ፤ ባህር ዳር) ዛሬ ረፋድ ላይ በኮምቦልቻ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ እየተደረገ በነበረበት ወቅት “የልዩ ኃይል አባላት የተያዙ አሉ” የሚል መረጃ በመሰራጨቱ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ግጭት ውስጥ መገባቱን ነዋሪዎች ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል።

በኮምቦልቻ አንድ ጤና ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ የአዲስ ዘይቤ ምንጮች እንደገለፁት አንድ ሰው እዛው ተኩስ የተከፈበት ስፍራ ላይ ህይወቱ ማለፉን እና ሌላ አንድ ሰው በአምቡላንስ ወደጤና ጣቢያ እየተወሰደ ህይወቱ አልፏል ብለዋል።

በተጨማሪም 12 የሚሆኑ ሰዎች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የሚገልፁት ነዋሪዎች፣ አምቡላንስ በተደጋጋሚ ሲመላለስ እንደነበረና የተጎጂዎች ቁጥር ከፍ ሊል ይችላል ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት በኮምቦልቻ ከተማ ከመደበኛ ጊዜው የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ መኖሩን ነዋሪዎች ነግረውናል።