Get Mystery Box with random crypto!

በሆሮ ጉዱሩ ዞን ኡሙሩ ወረዳ በተፈጸመ ጥቃት ከ60 በላይ ሰዎች መገደላቸውንና መቁሰላቸውን ኢሰመኮ | አዲስ ዘይቤ ~ Addis Zeybe

በሆሮ ጉዱሩ ዞን ኡሙሩ ወረዳ በተፈጸመ ጥቃት ከ60 በላይ ሰዎች መገደላቸውንና መቁሰላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ

ጳጉሜ 1፤ 2014 ዓ.ም

(አዲስ ዘይቤ፡ አዲስ አበባ) በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ስር በሚገኘው ኡሙሩ ወረዳ ከነሐሴ 23 እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በታጣቂ ኃይሎች በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ነዋሪዎች የተገደሉ፣ የቆሰሉ እና ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለፀ።

ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ነሐሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ አገምሳ ቀበሌ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ” ተብሎ የሚጠራ) ታጣቂዎች የወረዳው ዋና ከተማ የሆነችውን ኦቦራ ከተማን ለመያዝ ባደረጉት እንቅስቃሴ ሦስት የአማራ ብሔር ተወላጆች መግደላቸውን ተከትሎ ከኡሙሩ ወረዳ፣ ሀሮ አዲስ ዓለም ከተባለ ቀበሌ እና አጎራባች ከሚገኘው የአማራ ክልል፣ ቡሬ ወረዳ የተውጣጡ ታጣቂዎች በኡሙሩ ወረዳ በሚገኙ ቀበሌዎች የሚገኙ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ነዋሪዎች ላይ ነሐሴ 24 እና 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ጥቃት ፈጽመዋል።

በእነዚህ ሁለት ቀናት በተደረጉ ጥቃቶች ከ60 በላይ ሰዎች መገደላቸውን፤ ከ70 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን፣ የነዋሪዎች የቤት ንብረቶች እና የቀንድ ከብቶች መዘረፋቸውን ኮሚሽኑ ካነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እና የመንግሥት ኃላፊዎች ለመረዳት መቻሉን ኢሰመኮ አስታውቋል።

“ጥቃት ከተፈጸመባቸው ቀበሌዎች መካከል አሁንም ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን እና በጥቃቱ ምክንያትም ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች ተፈናቅለው በኦቦራ ከተማ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል” ብሏል ኮሚሽኑ።