Get Mystery Box with random crypto!

“ኢትዮጵያ ከካናዳ ጋር የሥራ ስምሪት ስምምነት የሌላት በመሆኑ ዜጎች በሐሰተኛ የሥራ እና ትምህርት | AMN-Addis Media Network

“ኢትዮጵያ ከካናዳ ጋር የሥራ ስምሪት ስምምነት የሌላት በመሆኑ ዜጎች በሐሰተኛ የሥራ እና ትምህርት ዕድል ማስታወቂያዎች እንዳይታለሉ” - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

AMN - ሰኔ 08/2016 ዓ.ም

“ኢትዮጵያ ከካናዳ ጋር የሥራ ስምሪት ስምምነት የሌላት በመሆኑ ዜጎቻችን በሐሰተኛ የሥራ እና ትምህርት ዕድል ማስታወቂያዎች እንዳይታለሉ” ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳሰበ።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ባወጣው መግለጫ፣ ዜጎችን ወደ ካናዳ እና ሌሎች ሀገሮች ለሥራ እና ትምህርት ዕድሎች መላክ እንደሚፈልግ የሚገልጹ በስሙ የተዘጋጁ የተወሰኑ ሐሰተኛ ማስታወቂያዎች በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች እየተዘዋወሩ እና አጭበርባሪ አካላት ለጉዳይ ማስፈፀሚያ በሚል ገንዘብ እየተቀበሉ መሆኑን መገንዘቡን ገልጿል።

የተወሰኑ ዜጎችም የማጭበርበር ድርጊት እንደደረሰባቸው ለተቋሙ አቤቱታ ማቅረባቸውን እና በተቋሙ ስም የተዘጋጁ ሐሰተኛ ሰነዶች መኖራቸውም እንዳረጋገጠም አስታውቋል።

ስለሆነም ኢትዮጵያ ከካናዳ ጋር የሥራ ስምሪት ስምምነት የሌላት መሆኑን፣ ወደ የትኛውም ሀገር የሚደረግ የሥራ ስምሪት በኢፌዴሪ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ፈቃድ በተሰጣቸው ሕጋዊ የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ኤጀንሲዎች በኩል እንደሚከናወን ገልጾ፣ ዜጎች በሐሰተኛ የሥራ እና ትምህርት ዕድል ማስታወቂያዎች እንዳይታለሉ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ ባወጣው መግለጫው አሳስቧል።