Get Mystery Box with random crypto!

የሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ከንቲባ ባልታወቁ ግለሰቦች በተተኮሰ ጥይት ህይወታቸው አለፈ | Addis Maleda - አዲስ ማለዳ

የሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ከንቲባ ባልታወቁ ግለሰቦች በተተኮሰ ጥይት ህይወታቸው አለፈ

አርብ ነሐሴ 27 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ከንቲባ ውብሸት አያሌው ትላንት ማታ ከሥራ ወጥተው ወደ ቤታቸው በማምራት ከመኪና ላይ ወርደው ሊገቡ ሲሉ ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች በተተኮሰ ጥይት ህይወታቸው ማለፉን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

ውብሸት አያሌው ባለትዳር እና የአንድ ሴትና አንድ ወንድ አባት የነበሩ ሲሆን፤ ወደ ሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር በሥራ ኃላፊነት ከመምጣታቸው በፊት በቀወት ወረዳ አስተዳደር በተለያዩ ተቋማት በባለሙያነትና በሥራ ኃላፊነት ሲያገለግሉ መቆየታቸው ተገልጿል።

ከንቲባው እንደ አንድ የህዝብ አደራ እንደተቀበለ አመራር እና እንደ ተወላጅ ከተማዋ የሚገባትን እድገትና ማዕረግ እንድታገኝ እንዲሁም ነዋሪዎቿ ኹሉን አቀፍ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ በከፍተኛ ቁጭት እየሰሩ የሚገኙ ወጣት አመራር እንደነበሩም የሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር ገልጿል።

"የደረሰብን ሀዘን እጅግ መራርና አስደንጋጭ ነው" ያለው የከተማ አስተዳደሩ "ይህም መስዋእትነት ለህዝብ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና አንድነት የተከፈለ ዋጋ ነው።" ሲል አስታውቋል።

ሥርዓተ ቀብራቸውም በሸዋሮቢት ከተማ ሚካኤል ቤተክርስቲያን በዛሬው ዕለት ከቀኑ 6 ስዓት ላይ ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት እንደሚፈጸም ታውቋል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n