Get Mystery Box with random crypto!

ፍርድ ቤቱ ከኮንዶሚኒየም ዕጣ ማጭበርበር ወንጀል ጋር ተያይዞ የተጠረጠሩ 5 የሶፍትዌር ባለሙያዎች | Addis Maleda - አዲስ ማለዳ

ፍርድ ቤቱ ከኮንዶሚኒየም ዕጣ ማጭበርበር ወንጀል ጋር ተያይዞ የተጠረጠሩ 5 የሶፍትዌር ባለሙያዎች በ60 ሺሕ ብር ዋስ ከእስር እንዲፈቱ ፈቀደ

አርብ ነሐሴ 20 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ከኮንዶሚኒየም ዕጣ ማጭበርበር ወንጀል ጋር ተያይዞ የተጠረጠሩ 5 የሶፍትዌር ባለሙያዎችን በ60 ሺሕ ብር ዋስ ከእስር እንዲፈቱ ፈቅዷል።

ዋስትና የተፈቀደላቸው ተጠርጣሪዎች የቤቶች ልማት ዳታ ቤዝ ቡድን መሪ ስመኘው አባተ እና የሶፍትዌር ባለሙያዎች ሀብታሙ ከበደ፣ ዮሴፍ ሙላት፣ ጌታቸው በሪሁን እንዲሁም ቃሲም ከድር ናቸው።

እነዚህ ተጠርጣሪዎች በዋስ ቢወጡ እንደማይቃወም ፖሊስ ለችሎቱ አስተያየት መስጠቱን ተከትሎ ዋስትና ተፈቅዶላቸዋል።

ቀሪዎቹ ማለትም፤ የአ/አ የቴክኒክ ሙያ ስልጠና አይሲቲ ቢሮ ም/ቢሮ ሀላፊ አብርሐም ሰርሞሌ፣ የቤቶች የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ሚኪያስ ቶሌራ እና የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን አይሲቲ ሀላፊ ኩምሳ ቶላ በሚመለከት ደግሞ በመርማሪ ፖሊስ በተገለጸው ከተለያዩ ተቋማት የሚሰበሰቡ ማስረጃዎች እና የቀሪ ሥራ በመኖሩ ችሎቱ አሳማኝ ምክንያት ነው ሲል የ12 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መፍቀዱን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ከችሎት ዘግባለች።

በአጠቃላይ ተጠርጣሪዎቹ ከ14ኛው ዙር 20/80 እና የ3ኛ ዙር የ40/60 የአ/አ ከተማ ከኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ላይ ያልቆጠቡና በወቅቱ ያልተመዘገቡ ግለሰቦችን ያለአግባብ በዕጣው እንዲያካትቱ አድርገዋል ተብለው በቁጥጥር ሥር ውለው ከአንድ ወር በላይ በእስር ላይ የነበሩ ናቸው።

በሌሎች መዝገቦች በተለያዩ ቀናት ከዚህ በፊት የቀረቡ ዶ/ር ሙሉቀን ሀብቱን ጨምሮ 7 ተጠርጣሪዎች ጉዳይ ግን እንደቀጠለ ነው።

በተለይም ለኮዶሚኒዬም ዕጣ ጉቦ ተቀብለው 5 ሰዎችን በዕጣው እንዲካተቱና ቤት እንዲደርሳቸው አድርገዋል የተባሉ 3 የስፍትዌርና ዳታ ቤዝ ባለሙያዎች ባሳለፍነው ሳምንት በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛሉ።

እነዚህ ተጠርጣሪዎች 1ኛ የአ/አ ቴክኒክና ሙያ ስልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የሶፍትዌር ባለሙያ የነበረ አሚ አምባዬ የሚባል ሲሆን፤ 2ኛ ተጠርጣሪ የዳታ ቤዝ ሰራተኛ የነበረ ዮናስ ወ/ጊዮርጊስ እና 3ኛ የዳታ ቤዝ ሰራተኛ የሆነችው አብረኸት ልዑል ናቸው።

በተለይም 3ኛ ተጠርጣሪ አብረኸት ልዑል በበኩሏ "አንድ ሰው መጥቶ ገንዘብ እየተከፈለ የቤት ዕጣ መካተት ይቻላል ወይ ሲል ጠይቆኝ ነበር እኔ ደግሞ 2ኛ ተጠርጣሪን ዮናስን ስጠይቀው አዎ ገንዘብ ተከፍሎ የሚያካትት አለ አለኝ። ከዛ በኋላ ግለሰቡ የባንክ ሂሳቤ ላይ የሶስት ሰዎችን አጠቃላይ 850 ሺህ ብር ካስገባልኝ በኋላ ኹሉንም ገንዘብ ለ1ኛ ና ለ2ኛ ተጠርጣሪዎች በባንክ ሂሳባቸው አዛውሬላቸዋለው" ስትል ለፍርድ ቤቱ መግለጿን መዘገባችን ይታወሳል።
________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n