Get Mystery Box with random crypto!

ኢሰመኮ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ተጠርጣሪዎች ለአካለ መጠን ከደረሱ ተጠርጣሪዎች ጋር ተ | አዲስ ነገር መረጃ

ኢሰመኮ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ተጠርጣሪዎች ለአካለ መጠን ከደረሱ ተጠርጣሪዎች ጋር ተቀላቅለው እንደሚታሰሩ ገለጸ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኢሰመኮ በአንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎች እድሜያቸው ከ18 በታች የሆኑ ተጠርጣሪዎች ለአካለ መጠን ከደረሱ ተጠርጣሪዎች ጋር ተቀላቅለው የሚታሰሩ መሆናቸውን ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት ገልጿል።

ኢሰመኮ ከሐምሌ ወር 2014 እስከ ሰኔ ወር 2015 ድረስ ያለውን የሴቶችና ሕፃናት ሰብአዊ መብቶች ኹኔታን ያካተተ ዓመታዊ ባለ 46 ገጽ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህም አደረኩት ባለው ክትትል በሶማሌ ክልል ፖሊስ ጣቢያዎች እና ማረሚያ ቤቶች ዉስጥ ያሉ ታራሚ ሕፃናት ለአካለ መጠን ከደረሱ እስረኞች ጋር ተቀላቅለው እንደሚያዙ፤ እንዲሁም በሚቆዩባቸው ጊዜያት የሕፃናቱን ዕድሜ ያላገናዘበ የኃይል እና የእርምት እርምጃዎች እንደሚወሰድባቸው አመላክቷል።

በተመሳሳይም በጉለሌ ክፍለ ከተማ በየካቲት ወር 2015 በእንጦጦ አምባ ትምህርት ቤት በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ምክንያት የክፍለ ከተማው ፖሊስ ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ ተማሪዎችን በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ገልጿል፡፡

ኢሰመኮ ግንቦት 4/2015 ጉለሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ባደረገው ጉብኝት በወቅቱ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ 64 ሕፃናት ታስረው መገኘታቸውንና ሕፃናቱ ለ5 ቀናት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ በእስር እንዲቆዩ መደረጉ አሳሳቢ ሆኖ መገኘቱን አውስቷል፡፡

በወላጅ ወይም አሳዳጊ ጥበቃ ሥር የመቆየት እንዲሁም በዋስ የመለቀቅ መብቶቻቸውም በአብዛኛው የማይከበርላቸው መሆኑ፣ በሚቀርብባቸዉ ክስ ላይ መልስ ለመስጠት ዕድል የማያገኙና በተጨማሪም በቂ የሕግ ባለሙያ ድጋፍ ማግኘት እንደማይችሉም ተገልጿል።

እንዲሁም በወንጀል ተግባር ላይ ለተገኙ ሕፃናት በአገሪቱ ሕግ የተቀመጠው ጥበቃ በአብዛኛው የማይፈጸም መሆኑ ጠቁሟል።

ይህም ያለፍርድ ቤት ፈቃድ ሕፃናት ላይ የወንጀል ምርመራ መደረጉ፣ ተጠርጣሪ ሕፃናት ወዲያውኑ ፍርድ ቤት ቀርበው ቃል እንዲሰጡ የማይደረግ ከመሆኑም ባሻገር ቃል የሚሰጡት ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች በሌሉበት መሆኑን  ገልጿል።

በመጨረሻም በሚሻሻለው የወንጀል ሥነ ስርዓት እና የማስረጃ ሕግ ለሕፃናት ልዩ ጥቅም ቅድሚያ እንዲሰጥ የሚያስገድድ መርሕ እንዲካተትና በወንጀል ለተጠረጠሩ ሕፃናት ከመደበኛ የፍትሕ ሂደት ውጪ ተፈፃሚ የሚሆኑ የሥነ ሥርዓት እርምጃዎችን እንዲካተቱ ኢሰመኮ ጠይቋል።

@Addis_News
@Addis_News