2022-08-23 22:39:45
የብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያና የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፲፯ኛ ዓመት ሢመተ ጵጵስና ተከበረ።
ሐምሌ ፲፯ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም (አቡቀለምሲስ፣ደብረ ብርሃን)
++++++++++++++++++++++++++++++
የብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያና የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፲፯ ዓመት በዓለ ሢመት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ ነቅዐ ጥበብ አባቡ ጨምሮ የሀገረ ስብከቱ የየክፍል ሓላፊዎች እና ሠራተኞች እንድሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተከብሯል።
የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ክቡር መጋቤ ሐዲስ ነቅዐ ጥበብ አባቡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ማርቆስ ጳጳሳትን ሾማ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ከዛሬ 17 ዓመት በፊት ካሰማራቻቸው ብፁዕ አባታችን አንዱ ነበሩ ሲሉ አውስተዋል።
ክቡር ሥራ አስኪያጁ ብፁዕነታቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናን በአስተዳዳሪነት በተለያዩ አድባራትና ገዳማት በአስተዳዳሪነት እና በሊቀ ጵጵስና በሐረርና በደቡብ ሀገረ ስብከቶች ያገለገሉ ሲሆን ልዩ ልዩ የዓለም ፈተና ሳይበግራቸው ፈተናዎቹን አልፈው ዛሬም ለሀገረ ስብከታችን ዕድገትና መልካም የሥራ ፍሬ የብፁዕነታቸው አባታዊ የሥራ መመሪያና ጸሎት አቅምና ኃይል ኾኖናል ብለዋል።
በዚሁ የብፁዕነታቸው የእንኳን አደረሰዎት መርሐ-ግብር ላይ የሀገረ ስብከቱ የየክፍል ሓላፊዎችና የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች ፣ የአድባራት ገዳማት አስተዳዳሪዎች እና የወረዳ ቤተ ክህነት ሠራተኞች ባስተላለፉት መልእክት ብፁዕ አባታችን ለቤተ ክርስቲያን የተፈጠሩና የሚኖሩ ናቸው እኛም ልጆቻቸው የብፁዕነታቸውን ሐዋርያዊ አገልግሎትና አስተዳደራዊ የሥራ መመሪያ በመቀበል ለሀገረ ሰብከቱ ሁለተናዊ ዕድገትና ውጤት እንተጋለን ብለዋል።
ብፁዕነታቸው በዚኽ የእንኳን አደረሰዎት መርሐ-ግብር ላይ ለተገኙት ልዩ ልዩ ሠራተኞችና እንግዶች ባስተላለፉት ቃለ በረከት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ባሰማራቻቸው ገዳማትና አድባራት እንድሁም በጵጵስና በተመደቡባቸው አህጉረ ስብከቶች ልዩ ልዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች እና የልማት ሥራዎችን እንዳከናወኑ ገልጸው ሀገረ ስብከታችንን ከዚኽ በላቀ ለማሳደግ መትጋት አለብን ብለዋል።
ብፁዕነታቸው እያጋጠመን ያለውን ሀገራዊ ፣ ሃይማኖታዊና ዓለም አቀፋዊ ፈተና በመቋቋም የሀገራችንን ፣ የሕዝባችንና የቤተ ክርስቲያናችን ተግዳሮቶች ከምንጩ ለማድረቅ የአንዱን ድካምና ክፍተት ሌላው በመሸፈን በፍጹም ሰላማዊና አንድነት ፣ በፍቅርና በመተሳሰብ ለላቀ የልማትና የዕድገት ሥራ መነሳሳት አለብን ብለዋል።
ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ከልጅነታቸው ጀምሮ በተለያዩ ጉባኤ ቤት ቅኔ ፣ ድጓ ጾመ ድጓ ፣ አቋቋም ፣ ዝማሬ መዋስዕት ፣ ቅዳሴ፣ መጻሕፍተ ሐዲሳትና ብሉያት በመማር የቤተ ክርስቲያኗን ማዕድ በአግባቡ የተመገቡ ትጉህ ደቀ መዝሙር እንደነበሩ በመርሐ-ግብሩ ላይ ተገልጿል።
ዘገባ በዲ/ን አሰፋ ጌትነት
ፎቶ ሚኪያስ አብዩ
479 viewsedited 19:39