Get Mystery Box with random crypto!

የዱራሜው መስጂድ ቢላል ጉዳይ ከምን ደረሰ? በአቡ ሀይደር በአላህ ሥም እጅግ በጣም ሩህሩኅ በ | የኡስታዝ አቡ ሀይደር ትምህርቶች ስብስብ

የዱራሜው መስጂድ ቢላል ጉዳይ ከምን ደረሰ?

በአቡ ሀይደር

በአላህ ሥም እጅግ በጣም ሩህሩኅ በጣም አዛኝ በሆነው

ከሁሉ በፊት አማኝ ባሪያዎቹን በማነሳሳትና በማገዝ: ከፊሉ በገንዘቡ፣ ከፊሉ በዕውቀቱ፣ ከፊሉ በማስተዋወቅና የተቀረው ደግሞ በቦታው ላይ በመሳተፍ ለመስጂዱ ህልውና አስተዋጽኦ እንዲያደርግ: ተውፊቁ (እገዛው) ላልተለየን ጌታ አላህ ምስጋና ይድረሰው። ያለሱ እገዛና ፈቃድ ምንም ነገር ሊከሰት አይችልምና።

በመቀጠልም: የዱራሜው ቢላል መስጂድ ሁኔታ፤ ሙአዚንና ኢማም በሆኑት ሰውዬ ብቻ ሶላት መከናወኑ: እረፍት የነሳው ወንድማችን የ Islam Selam አካውንት እና የዚህ ዩቱብ https://youtube.com/channel/UC1phBbwcq_sXeSKKV_JtUMg ባለቤት ጉዳዩን በፌቡ በመልቀቅ ለሙስሊሞች መነሳሳት ሰበብ ስለሆንከን ጀዛከላሁ ኸይራ።

በመሰለስም: ይህ ጉዳይ ለሁሉም ወንድምና እሕቶች በሰፊው እንዲዳረስና ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በተደጋጋሚ በመፖሰት ሰፊ ተደራሽነት እንዲኖረው ለለፋኸው ወንድም አቡ ዳዉድ ዑሥማን ጀዛከላሁ ኸይራ።

በመረበዕም:– በተለያዩ የሶሻል ሚዲያዊች (በፌቡ፣ በቴሌግራም፣ በዋትስአፕ፣ በቲክቶክና በዩቱብ) ስርጭቱ እንዲስፋፋ ላደረጋችሁ ወንድምና እሕቶች በመላ ጀዛኩሙላሁ ኸይራ።

በመጨረሻም:– በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጭም በመሆን ይህ የዱራሜው ቢላል መስጂድ ጉዳይ የኔ ጉዳይ ነው በማለት በገንዘባቹ የተሳተፋችሁ ወንድምና እሕቶች: ገንዘብና ልጆች በማይጠቅሙበት ቀን አላህ ባወጣችሁት ገንዘብ ተጠቃሚ ያድርጋችሁ።

እንዲሁም ቦታው ድረስ በመገኘት ለተሰበሰበው ሕዝብ ኢስላማዊ ትምሕርት የሰጣችሁ (ኡስታዝ ዐብዲ፣ ኡስታዝ ጁንዱላህ፣ ኡስታዝ መሐመድ ሸምሱ)፣ በቦታው በመገኘት የፕሮግራሙ ድምቀት የሆናችሁ ተሳታፊዎች በሙሉ (በተለይ የሐላባ ጀመዓዎች)፣ ቦታውን በማበጃጀት ላስተካከላችሁ በመላ (በተለይ ወንድም ሱልጣን ናሲር፣ ወንድም መሐመድ ኢብራሂም እና ወንድም ፉአድ) ጀዛኩሙላሁ ኸይራ።

አዲስ ነገር ምን ተሰራ ምንስ ቀረ?

1/ በመስጂዱ ላይ ሙአዚን እና ኢማም ከነበሩት አባት በተጨማሪ: ለመስጂዱ ቋሚ ኢማም (በመግሪብ፣ ዒሻእና ፈጅር ላይ አሰጋጅ) ተመድቧል። ይህ ኢማም ከኢማምነት በተጨማሪ:– የአካባቢውን ህፃናት ቁርኣን ማስቀራት፣ ከመግሪብ እስከ ዒሻእ ለመጣው ሰው ቋሚ የሙሐደራ ፕሮግራም መስጠት፣ በግላቸው የተለያየ ኪታብ መቅራት የሚፈልጉ ወንድሞችን ማቅራት ሥራው ይሆናል።

2/ ቅዳሜና እሕዱ (ከ 14/12/14—15/12/14) ለሁለት ቀናት በመስጂዱ ላይ ለተሰበሰበው ህዝብ ኢስላማዊ ት/ት መስጠት። በዳዕዋው ሰበብም ወደ 9 ሰዎች ሸሀዳ በመስጠት ሰልመዋል። ለተሰበሰበው ሰውም በሁለቱ ቀናት የምሳ ግብዣ ፕሮግራም ተካሂዷል።

3/ የመስጂዱ ውስጣዊ ችግር (ኮርኒስ) እደሳ ተካሂዷል።

በአሁን ሰአት ከአዲሱ ኢማም በደረሰኝ መረጃ መሰረት ከ10 እስከ 15 የሚደርሱ ሰዎች ወደ መስጂዱ በመመላለስ የጀመዓ ሶላት እንደሚሰግዱ ማወቅ ተችሏል። ቁርኣን መማር የጀመሩ ህፃናትም (ወንድና ሴትን ጨምሮ) ወደ 15 ደርሰዋል።
የቀረው ሥራ ደግሞ:– መስጂዱን ዙሪያውን ማጠር: በሶስት ወይም በየ አራት ወራት በመስጂዱ ላይ የዳዕዋ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት።

ምን ያህል ገንዘብ ተሰበሰበ? ምን ያህልስ ወጪ ተደረገ?

የተሰበሰበው ገንዘብ ከገመትነውና ከጠበቅነው በላይ ነው። በአጠቃላይ እስካሁኑ ሰአት ድረስ የተሰበሰበው ገንዘብ 2,585,113·32 ሳ (ሁለት ሚሊየን አምስት መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ፣ አንድ መቶ አሥራ ሶስት ብር ከሰላሳ ሁለት ሳንቲም) ነው።

ወጪ የተደረገው ደግሞ:– 242,997 ብር ነው። ከወጪ ቀሪ የሚሆነው:– 2,342,116·32 ሳ ይሆናል።

በቀጣይ ምን ታሰበ?

ይህ የተሰበሰበው ገንዘብ ለቢላል መስጂድ ሙአዚን እና ኢማም እንዲሁም ኡስታዝ ለሆኑት በተጨማሪም ለአጥር ግንባታው ከሚያስፈልገው በላይ የተረፈ በመሆኑ: ይህ የተረፈ ገንዘብ ለሌላ ኸይር ሥራ እንዲውል:–

1/ በዋንኝት በአካባቢው የሚገኘውን የካምፓሱ ሙስሊም ተማሪዎችን ማገዝ። የዱራሜ ካምፓስ ሙስሊም ተማሪዎች ከካምፓሱ ፊትለፊት ወደ ውስጥ ገባ ብሎ የሰሩትን መስጂድ ጎብኝቼዋለሁ። መስጂዱ ቀሪ ሥራዎች (በተለይ በሴቶች በኩል ምንጣፍ፣ በርና መስኮት እንዲሁም ችፑድና መፀዳጃ ቤት)፣ መድረሳው ሙሉ እድሳት ያስፈልጉታል። እንደተነገረኝ ከሆነ ወደዚህ መስጂድ በመመላለስ የሚሰግዱ ወንድምና እሕቶች ወደ 300 ይጠጋሉ። ስለዚህ እነዚህ ሰጋጆች: ከሶላት በተጨማሪ መንፈሳዊ ማንነታቸውን የሚያጠናክርላቸው ሁለት ኡስታዞችን መቅጠር ያስፈልጋል።

2/ በዛው ዱራሜ ከተማ: ከቢላል መስጂድ ራቅ ብሎ በገጠራማው ክፍል ለሚገኙ ሙስሊም ነዋሪዎች የኡስታዝ እጥረት ያለባቸውን ቦታዎች ጥናት በማድረግ ኡስታዞችን መቅጠር ዋነኛ ስራችን ይሆናል።

3/ ገንዘቡ የሚተርፍ ከሆነ ከሀላባ ከተማ ወደ ከንባታ በሚወስደው መንገድ 12 ኪ ሜ ርቃ የምትገኘውን የአቦኪቾ ከተማ በኡስታዞችና በዳዕዋ መድረስ ሌላው ስራችን ይሆናል። ይህ ከተማ ከ1000–1,500 የሚደርሱ አባወራዎች አሉት። 85 በመቶ የሚሆነው ሙስሊም ነው። ያሉት መስጂዶች ብዛት በጭቃ የተሰሩ 3 ብቻ ናቸው። መደረሳ ማፊ፣ ኡስታዝ ማፊ!! ስለዚህ ቦታው የኡስታዝና የመድረሳ ትኩረት ይሻል።

ወንድምና እሕቶቼ ሆይ!

ይህ የኸይር ሥራ ቀጣይነት እንዲኖረው የናንተን እገዛ ይሻልና: በቻላችሁት መጠን አሁንም ከመተባበር ወደ ኋላ አትበሉ። አላህ ያግዛችሁ ወሰላሙ ዐለይኩም ወራሕመቱላሂ ወበረካቱሁ