Get Mystery Box with random crypto!

የተቀደሠ እርግማን 1 ኣንድ ምርጥ ግጥም ከዚህ ዓለም ሃሣብ ወድያ የሚነጥል አንዲት ሻት የ አል | አብሮነት/Abronet

የተቀደሠ እርግማን 1

ኣንድ ምርጥ ግጥም
ከዚህ ዓለም ሃሣብ ወድያ የሚነጥል
አንዲት ሻት የ አልኮል
ዓይንን የሚያሥጨፍን ጉረሮ ሚያቃጥል ።
ቡና ወፈር ያለ ገጣሚ ሚወደው
ወሬ ደመቅ ያለ የከፋ ጎረቤት ጆሮ የሚሠጠው ።
ሴት ልጅ ሴት የሆነች
ሃሣብ ምታወራ ተሎ የማትሠለች ።
መዝሙር መንፈሳዊ መዝሙር ያሬዳዊ
ደብተራ ሚያዜመው ህይወቱ የሆነ ፍፁም ሰማያዊ ።
የስዕል ትዕይንት
ወሬ ያልበዛበት : የጥበባት ምሽት ።
ቴዓትር የፍቅር
ቴዓትር የ ሃገር
ሙዚቃ ሚያሥለቅስ :ነፍሥ ጥግ የሚደርስ ።
የተማሩ ሰዎች ብዙ ማያወሩ
ግን ጥቂት ሲያወሩ ሥንዴን የሚዘሩ
ሴራን የማይመክሩ ።
ብዙ የሠሩ ሰዎች
በስማቸው በኩል ሃገርን ያሥጠሩ
አውሩልን ሲባሉ እጅጉን የሚያፍሩ ።
በ እርቅ አደባባይ ሢታዩ ሚፈሩ ።
ይህን መሠል ነገር እጅጉን ናፍቆኛል
ምክንያቱም
ያንን መሣይ ህይወት ካጣን አርፍደናል
በንቶፈንቶ ነገር ምንም ምንም በሚል
ዳግመኛ እንዳናየው
እንዳይነሣ አርገን ቆፍረን ቀብረናል ።
ታድያ ...?
በዚህ የማላዝን
ማልከፋ ከሆንኩ
እንደምን አድርጎ እግዜር ሰው ይለኛል ።

ተፃፈ በ ጥር 21 የዓሥተርዮ ማርያም በማህሌት ፈንታ በታለፈ የጥልቅ ሃሣብ ሌሊት ።
ኤፍሬም ሥዩም