Get Mystery Box with random crypto!

عبد الرزاق الحبشي: ዝክረ-ተውሒድ ☞'አል-አሽዐሪያዎችን' በአጭሩ እንተዋወቅ! | 📚ፈዋኢድ እና ፈራኢድ📚

عبد الرزاق الحبشي:
ዝክረ-ተውሒድ

☞"አል-አሽዐሪያዎችን" በአጭሩ እንተዋወቅ!

☞አል-አሻዒራ ማለት ወደ አቡ'ል-ሐሰን ኢብኑ ዐሊይ ኢብኑ ኢስማዒል አል-አሽዐሪይ የሚዛመዱ የፍልስፍና አንጃዎች ናቸው። ይህ ሰው ወደ ታላቁ ሰሐቢይ አቡ ሙሳ አል-አሽዓሪይ የሚዘዝ የዝምድና ትስስር አለው። አቡል ሐሰን አል-አሽዓሪይ ከእድገቱ መባቻ አንስቶ "ሙዕተዚላህ" ተብላ በምትጠራ አንጃ አስትምህሮት ስር ተኮትኩቷል። ይህም የሆነበት ምክንያት የዚህ አንጃ ፊት አውራሪ መምህር የሆነው አቡ ዐሊይ አል-ጁባኢይ የእናቱ ባል በመሆኑ ለእሱም የእንጀራ አባቱ ስለሆነ ነው። በጁባኢይ ስር በመሆን የሙዕተዚላን አስተምህሮት እየቀሰመ እድሜውን አሳልፏል። ይህን ስንል "ሙዕተዚላዎች ማን ናቸው?" ማለታችሁ አይቀርም አንዱ አንዱን ይመዛልና፤ በመሆኑም ሙዕተዚላህ የተባለው ቡድን ከጥመት ቡድኖች መካከል ፊት አውራሪ ሲሆኑ የአሏህን ባህሪያትና መገለጫዎች ሙሉ በሙሉ ውድቅ በማድረግና ባለመቀበል ይታወቃሉ።
ይህንም ጠፍ ተግባራቸውን "አሏህን ከጉደለት ለማጥራት ነው!" በሚል ማምታቻ ይሸፋፍኑታል።
የአሏህን ባህሪያቶች ውድቅ ማረግ ማለት አሏህ ሀይል የለውም፣ መስሚያ የለውም፣ መሻት የለውም፣ አይናገርም .....ሌሎችንም ባህሪያቶች እንዲህ ባለ ሰላማዊ አእምሮንም ሆነ ትክክለኛ አስረጂዎችን በሚቃወም መልኩ በሰቀጠጠ ገለፃ ይገልፃሉ። ይህ አካሄድ የሙዕተዚላዎች አካሄድ አልያም ምልከታ በመባል ይታወቃል። በግልፅ እንደሚታወቀው የአሏህ እጅግ የተዋቡ ስሞቹ እና የላቁ ባህሪያቶቹን አስመልክቶ የቀደምት የኢስላም አበው ማለትም የሰለፎች መንገድ እነዚህን ስሞችና ባህሪያት ከፍጡራን ጋር ሳያመሳስሉ፣ ትርጉማቸውን ሳያራቁቱ (ትርጉም አልባ) ሳያደርጉ፣ ትርጉማቸውን ከትክክለኛው እሳቤያቸው ሳያዛቡ እንዲሁም ያሉበት ሁኔታን ሳይገልፁ መሰረታዊ ትርጉማቸውን በመረዳት የይዘታቸውን ምንነት እውቀት ወደ አሏህ አስጠግተው ያፀድቃሉ። ይህም ትክክለኛው የነብያቶች መንገድ ነው። ከዚህ ትክክለኛ ዐቂዳ በተቃራኒ የሰፈሩት የጥመት አንጃዎቹ ሙዕተዚላዎች የቆጠቆጡበት ዋነኛ ሰበብና ታሪካዊ ዳራ እንደሚጠቁመው የሙዕተዚላህ መነሻ ስብእና የሆነው ዋሲል ኢብን ዐጣእ እና አጃግሬዎቹ የታላቁን ሊቀ ኢስላም ሐሰነል በስሪን ትክክለኛ ምልከታ ገሸሽ በማረግ የራሳቸውን ውግዝ አመለካከት በመያዝ ከሳቸው የትምህርት መአድ እራሳቸው በማሸሻቸው እንዲሁም ሰዎችን በመገንጠላቸው ምክንያት ነው። በዚህ ምክንያት ተገንጣይ ጠርዘኞች የሚል ስም ተሰጣቸው በዐረብኛ "ሙዕተዚላህ" ለሚለው ቃል ተቀራራቢ ፍቺ ይመስላል። ነገር ግን ከሐሰን የእውቀት መቀማመጥ ብቻ ሳይሆን አያሌ ከሆኑ የሙስሊሞች ትክክለኛ እምነት ፅንሰ ሀሳብ በመገንጠላቸውም ምክንያት ነው ይህን ስም የተጎናፀፉት።
"ታዲያ በዚህ ዘመን ሙዕተዚላዎች አሉ!?" ብለህ ከጠየክ መልሱ "በሚገባ!" ይሆናል ። የሺዓ አመለካከት ያለው በአጠቃላይ የሙዕተዚላህ ዐቂዳ አራማጅ ነው። ይህን እንደ መርሆ ያዙ።
ሁሉም ሺዓዎች ትንሽ ወደ ሱና የቀረቡ ናቸው ከሚባሉት ዘይዲያዎች አንስቶ ከሱና እጅግ ከራቁት ጃዕፈሪያዎችና ኢማምያዎች ጭምር እምነታዊ ምልከታቸው (ዐቂዳቸው) ከሙዕተዚላዎች ጋር የገጠመ ነው።
አቡል ሐሰን አል ዐሽዓሪይም በዚህ በሙዕተዚላህ ዐቂዳ ላይ አርባ አመታትን አሳለፈ። ከአጎቶ ቀጥሎም የዚህ አንጃን ታላቅ ስብዕናን ለመላበስ በቃ። ነገር ግን የአሏህ ፍላጎት ሆነና ከአጎቱ ጋር በአንዳንድ መሰረታዊ ነጥቦች ዙሪያ መስማማት ላይ መድረስ ሳይችሉ ቀሩ። ይህም አሏህ ለባሮቹ ይበልጥ የሚበጃቸውን መተግበር ግዴታ አለበት የሚለው አደገኛ ጠንቅ ያለው አመለካከት ነው። እንደሚታወቀው አሏህ በግዴታ ሳይሆን በመፃደቅና፣ በችሮታው እንዲሁም በእሱ መሻት ለባሮቹ መልካም ይመነዳል እንጂ እሱን በተግባሩ ላይ የሚያስገድደው የለም። የአሏህ ችሮታ እና እዝነት ካላገኘው በስተቀር ማንም በስራው ጀነት እንደማይገባ የሚያስረዱ ነብያዊ ፈለጎች እንዳሉ ማንኛውም ሙስሊም የማይክደው እውነታ ነው።
አቡል ሐሰን ይህን "አሏህ ለባሮቹ መልካምን ማረግና ለሰሩት ደግ የመመንዳት ግዴታ አለበትቀ" የሚለውን የሙዕተዚላዎች ምልከታ ንፁህ በሆነ አእምሮው ሊቀበለው አልቻለም።
በዚህም የተነሳ ከሙዕተዚላህ መንገድ በመሸሽ ሀቅን መፈለግ ጀመረ። የአቡ'ል ሐሰን ሀቅን የመፈለግ ውጣ ውረድ ከታላቁ ሰሐቢይ ሰልማን አል-ፋሪሲይ ውጣ ውረድ ጋር ይመሳሰላል ይህ ሰሐቢይ በመጀመሪያ እሳት አምላኪ(መጁስ) እንደነበር ቡኋላም ሀቅን ለመድረስ አንድ ባህታዊ ጋር እንደዘወተረ በመጨረሻም የአሏህ መልእክተኛን በመዲና በማግኘት አላማው መሳካቱን እናውቃለን።
አቡል ሐሰንም ሀቅን ለመፈለግ ባረግው ጥረት የሰለፎች መንሀጅ የመሰለውን የኩላቢያን መንገድ መከተልን መረጠ። በሂደትም ይህ የኩላቢያ አስተሳሰብ ወደ አቡል ሀሰን እንዲጠጋ ሆነ። ሰበቡም አቡል ሀሰን በእውቀቱ እጅግ የገነነ በመሆኑና በዘር ሀረጉም የተሻለ እውቅናና ክብር ስላለው የዚህ ምልከታ አስተሳሰብ ከባለቤቱ ይልቅ ወደ አቡል ሐሰን ተጠጋ። ይህ ዐቂዳም የአቡል ሐሰን ዐቂዳ ተብሎ ተቆጠረ፤ አስተሳሰቡና ምልከታውም የአሽዐሪያ ምልከታ በሚል መጠነ ሰፊ እውቅናን አገኘ።

ይህ የአሽዐሪያ አስተምህሮም ልክ እንደ ሙዕተዚላዎች ሙሉ በሙሉ የአሏህን ባህሪያቶች ውድቅ ከማረግ ይልቅ ባህሪያቶቹን በአእምሮ የምናፀድቃቸው ባህሪያትና በወሬ ብቻ የምንቀበላቸው ባህሪያት ብሎ ይከፋፍላል።
በዚህም ምክንያት አእምሮ ያፀደቃቸውን ባህሪያቶች እንቀበላለን አእምሮ ያላፀደቃቸውን ባህሪያቶች ግን ለአሏህ አናፀድቅም የሚል እርስ በእርሱ የተምታታ ፈሊጥ ነው።
በዚህ ምልከታ ላይ የተወሰኑ ዘመናትን ካሳለፈ ቡኋላ ልክ ሰሐብዩ ሰለማን የአሏህ መልእክተኛን በመጨረሻ እንዳገኘና ሀቀን እንደተቀበለ ብጤ አቡል ሐሰንም ወደ ትክክለኛው የሰለፎች ጎዳና ለመመለስ በቅቷል። መመለሱን የሚያረጋግጡ ድርሰቶችን ፅፏል። ከዚህም መካከል "አል-ኢባናህ" የተሰኘው ድርሰት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። ይህ ድርሰት ታትሞ በየቦታው የሚገኝ ሲሆን በዚህ መፅሀፍ ውስጥ እሱ በታላቁ የአህለ ሱና ሊቅ በሆኑት በአል ኢማም አሕመድ ኢብን ሐንበል መንገድ ላይ እንዳለ ጠቅሷል። የሚገባቸውንም ሙገሳ በመፅሀፉ ውስጥ አስፍሯል። ወደ ሰለፎች ጎዳና መመለሱንም ይፋ አድርጓል።

ይህ የአሽዐሪያ አስተምህሮ ከሳውዲ ዐረቢያ ውጪ ባሉ የተለያዩ ኢስላማዊ ዩኒቨሪስቲዮች
ይሰጣል። ይህች ዐቂዳ የኩላቢዮች ስትሆን አቡል ሐሰን ከነበረበት የሙዕተዚላህ ዐቂዳ የተሻለ መስሎት ለተወሰኑ አመታት ያራመደው ነው። ቡኋላ ይህን ምልከታ ወደ እሱ በጠቀስነው ምክንያት እንዳስጠጉት ተመልክተናል። እነዚህ የአሽዐሪያን ዐቂዳን እንከተላለን የሚሉ ጭፍራዎች በአቡ'ል ሐሰን ላይ መቅጠፋቸውን አላቆሙም። እሱ ከነበረበት ምልከታ እንደተመለሰ የፃፋቸውን አያሌ ድርሰታት የሰለፎችን መንገድ እንከተላለን የሚሉ ሰዎች በሱ ላይ ቀጥፈው የፃፉት እንደሆነ ደጋግመው ይሞገታሉ። ነገር ግን የአሏህ ፍቃድ ሆኖ እሱ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ከእሱ ቡኋላ የመጡ የዚህ የአሽዐሪያ ዐቂዳ ታላላቅ ስብእናዎች የነበሩ የአቡል ሐሰን ተከታዮች የነበሩበትን ዐቂዳ ስህተት በማጋለጥ ወደ ሰለፎች መንገድ ለመመለስ እንደሞከሩና እንደተመለሱ በተለያዩ ድርሰቶቻቸው ላይ አስፍረዋል።