Get Mystery Box with random crypto!

ዛሬም እንደ ትናንቱ፥ ፈተናዎችን በድል ተሻግረን፣ እጃችንን ለምስጋና እንዘረጋለን! - ጠቅላይ | የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ እውነተኛ ደጋፊዎች

ዛሬም እንደ ትናንቱ፥ ፈተናዎችን በድል ተሻግረን፣ እጃችንን ለምስጋና እንዘረጋለን!

- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ዛሬም እንደ ትናንቱ ፈተናዎችን በድል ተሻግረን፣ እጃችንን ለምስጋና እንዘረጋለን!!

የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች፣
ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፣

ኢትዮጵያ የሚለው ስም ለችግሮች ያለመንበርከክ፣ በፈተና ሳይበገሩ የማለፍና እንቅፋቶችን ተሻግሮ ድል የማድረግ የክብር ስም ነው፡፡ ሀገራችን በታሪኳ ያለ ፈተና ያሳለፈቻቸው ዘመናት እጅግ ጥቂቶች ናቸው፡፡ በብርቱ ልጆችዋ ጥረትና በፈጣሪ ቸርነት የሚገጥማትን የችግር ውርጅብኝ እየተቋቋማች እዚህ ደርሳለች፡፡ ዛሬም የሀገራችንን ብርቱ አቅም ሊገዳደር የመከራ ዶፍ በዙሪያችን ቢያስገመግም፤ እንደ ሐምሌ ክረምት በችግር ደመናቸው ሕይወታችንን ሊያጨልሙ የሚቋምጡ ኃይሎች ቢሰበሰቡም መጓዛችንን አናቆምም፡፡ በጽኑ ማንነታችንና በፈጣሪ እገዛ ለምንታመነው እኛ ሁሌም ከክረምቱ ባሻገር የሚመጣው ብሩህ ጸደይ ጎልቶ ይታየናል፤ ከጨለማው ማዶ ደማቅ ብርሃን እንዳለ እናውቃለን፡፡ የትናንቱን ጨለማ እንዳለፍነው ሁሉ÷ የዛሬውን ጽልመት የማንሻገርበት ምክንያት እንደሌለ እያመንን፣ ብርታትና ጥንካሬውን ለሚቸረን ፈጣሪ ዛሬም ምስጋና ከማቅረብ አንቦዝንም፡፡

አመስጋኝነት ያለፈውን ዘመን በአሸናፊነት፣ ያለንበትን ወቅት በዕድለኝነት፣ መጪውን ጊዜ ደግሞ በብሩህ ተስፋ እንድንመለከተው የሚያድርግ ታላቅ ኃይል አለው። በአንጻሩ አማራሪነትና ምስጋና ቢስነት የተሸናፊነትና የዕድለ ቢስነት ሥነ ልቡናን ይፈጥራል፡፡ ራሳችንንና ሌሎችን በአዎንታዊነትና በፍቅር መመልከት እንዳንችልም ያደርገናል። በምሬትና በምስጋና ቢስነት የተጠመደ ግለሰብም ሆነ ሕዝብ የጎደለው እንጂ በእጁ ያለው ጸጋ አይታየውም፡፡ የደረሰበት በደል እንጂ የተሰጠው ዕድል አይጎላለትም፡፡ የሚመጣው መከራ እንጂ ከፊቱ ያለው ደስታ በኅሊናው አይሳልም። አመስጋኝ ሰው በመከራውና በጭንቁ ውስጥ ድሉንና ዕድሉን ማየት የሚችል ነው፡፡ ከወጀቡና ከማዕበሉ ይልቅ የመርከቧን ጥንካሬ ያያል፡፡ ከፈተናና ከችግሩ ግዝፈት ይልቅ፣ ሁሉንም በአንድነትና በፈጣሪ ርዳታ ለማሸነፍ የሚቻል መሆኑን ያስባል፡፡
የአክሱምና ቀደምት ሥልጣኔዎች፣ የላሊበላና በዙሪያው የነበሩ ምሥጢራዊ የኪነ ሕንጻ እምርታዎች፣ በሐረርና በዙሪያው አብቦ የነበረው የከተሜነት መነቃቃትና ዕድገት፣ በጊቤ ዙሪያ የነበሩ ንግድን ከግብርና ያጣመሩ ሥልጣኔዎች፤ በገዳ ሥርዓት ዴሞክራሲን የማስተዋወቅ ጥረቶች፤ በወላይታ፣ በከምባታ፣ በሐላባ፣ በሐድያ፣ በዳውሮና ከፋ ዙሪያ የነበሩ ከመካከለኛው ምሥራቅ እስከ አውሮፓ ድረስ የንግድና የዲፕሎማሲ ግንኙነት የተመሠረተባቸው አስተዳደሮች፤ በጎንደር የተማከለ መንግሥታዊ አስተዳደር የመፍጠር ሙከራ፤ በአፋርና በሶማሊ የነበረው መረጃንና ማዕከላዊነትን መሠረት ያደረገው የአስተዳደር ሥርዓት፣ በጋምቤላ የነበረው ለሴቶች የተለየ የክብር ቦታ የሚሰጠው ሥልጣኔ፣ በቤኒሻንጉል የነበረው የሙዚቃና የሙዚቃ መሣሪያዎች ልህቀት፤ እንዲህም በሌሎቹም አካባቢዎች ታይተው የነበሩትን ሥልጣኔዎች ወደ ኋላ ዞር ብለን በማየት ልንኮራባቸው የሚገቡ ሀብቶቻችን ናቸው። የምንኮራባቸውን ትናንቶች የሰጠንን የኢትዮጵያን አምላክ ማመስገን ያለብንም ለዚህ ነው፡፡

በውስጥ የነበሩ ዘመነ መሳፍንትን የመሰሉ መከፋፈሎችን፤ ከውጭ የመጡ የቅኝ ግዛት ጫናዎችን ሀገራችን በማይታይ ኃይል ተቋቁማቸዋለች፡፡ ታሪኳና ማንነቷ ሳይጠፋ፣ እንደ አድማስ ድንጋይ ጠንክራ ለዘመናት መቆየቷ ተአምር ሊባል የሚችል ነው። ዘመናዊቱ ኢትዮጵያ ከመበታተን ወደ አንድነት በተሰበሰብችበት ሂደት ውስጥም ጦርነቶችና ግጭቶች፣ ወረራዎችና የሥልጣን ሽኩቻዎች እልፍ ሆነው ተከሥተዋል፡፡ የሀገረ መንግሥት ግንባታው መልክ ይዞ ሳይጠናቀቅ፣ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ ፈጣንና ተከታታይ ሥር ነቀል ለውጦች ሀገራችንን ገጥመዋታል፡፡ አብዮቶች፣ የእርስ በርስ ጦርነቶች፣ ወረርሽኞች፣ ከፍተኛ ርሃቦች፣ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ቀውሶች ጎርፍ ሆነው ቢግተለተሉም ኢትዮጵያን ነቀነቋት እንጂ አላፈረሷትም፡፡ በቅርብና በሩቅ ያሉ ታሪካዊ ጠላቶቿ በየጊዜው እየተነሡ ገዝግዘው ሊጥሏት ያላደረጉት ጥረት፣ ያልሸረቡት ደባ አልነበረም። ስሟን ጥላሸት ሊቀቡ ሞክረዋል፤ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ፍትሕን ደጋግመው ነፍገዋታል። ያላትን የባሕር በር አሳጥተው ሊያፍኗት ሞክረዋል። ከሆዷ የሚፈልቁትን ወንዞቿን እንዳትጠቀም ሊያደርጉ በተንኮል የተጠለፉ ውሎችንና በክፋት የተሸመኑ ስምምነቶችን አድርገዋል። በዚህ ሁሉ መሐል፣ ኢትዮጵያችን እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትና፣ በልጆቿ ጥረትና በፈጣሪዋ ፈቃድ ተጠብቃ እንደ ሀገር መቀጠል መቻሏ እጅግ ይደንቃል፡፡ ሀገራችን እነዚህን ሁሉ መከራዎች መሻገራን ስናስብ ለፈጣሪ ምስጋና እንድናቀርብ ምክንያት ይሆነናል፡፡

ያለፉት አራትና አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ተስፋና መከራ፣ አንድነትና ልዩነት፣ ዓለም አቀፋዊ አድናቆትና ውግዘት፣ እመርታና ጉተታ፣ ነጻነትና ግጭት ያስተናገድንበት ጊዜ ነው ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆቿን ያገኘችበት ብቻ ሳይሆን ያጣችበትም ጊዜ ነው። ቀረ፣ ሊያበቃለት ነው የተባለው ታላቁ የሕዳሴ ግድባችን፣ ሙሌቱ ተገባድዶ ኃይልን ማመንጨት ጀምሯል። የድርቅና የጉስቁልና ምድር የተባለች ሀገር ቢልዮን ችግኞችን በመትከልና በየሥፍራው ፓርኮችን በማበጀት የምድረ ገነትነት ግስጋሤዋን ቀጥላለች። የህልውናዋ ዋስትና የምዕራባውያን ስንዴ እንደሆነ ሲያስቡ፣ ኢትዮጵያ ግን በጀመረችው የበጋ ስንዴና ሰፋፊ የእህልና የአትክልት እርሻዎቿ ከራሷ አልፋ ለሌሎች ለመትረፍ ጫፍ ላይ ትገኛለች። በአንድ ወቅት የአፍሪካ የቆሻሻ መጣያ ለመባል የደረሰችው አዲስ አበባ ስሟን የሚመጥን መልክ ልትይዝ ዳር ዳር እያለች ነው፡፡ ያጋጠሙን ፈተናዎች ብዙ ውድ ዋጋዎች አስከፍለውናል፡፡ እነርሱን ባሰብናቸው ቁጥር ያመናል፡፡ ካጣነው በላይ ግን ያገኘነው ይበልጣል፡፡ መከራው አልገታንም፤ ፈተናው አላሸነፈንም፡፡ ለዚህም ለፈጣሪ ብዙ ምስጋና እናቀርባለን።

ውድ የሀገሬ ልጆች፣

ወንድም በወንድሙ ላይ የጨከነበትን፣ አብረን የኖርን ቀርቶ አብረን የዋልን በማይመስል መልኩ የተጋጨንባቸውን፣ በረባው ባልረባው የሰው ሕይወት የተቀጠፈባቸውን፣ ዒላማ እንጂ ዓላማ በሌላቸው ሰዎች የወገኖቻችን ደም በከንቱ የፈሰሰባቸውን ያለፉትን ጥቂት ዓመታት ዞር ብለን ስናይ ልባችን በኀዘን ይሰበራል። እንደ ትውልድም ሐፍረት ይሰማናል፡፡ በሰሜኑና በምዕራቡ የሀገራችን ክፍሎች ጦርነቶችና ግጭቶች ያስከፈሉንን የሰው ሕይወትና የወደመውን የሀገር ሀብት ስናስብ ዓይኖቻችን ብቻ ሳይሆኑ ነፍሶቻችንም ያነባሉ። በአንድ ወቅት በምሥራቁና በደቡቡ የሀገራችን ክፍል ላይ ተከሥቶ የነበረው ጥፋት ያደረሰው ጉዳትና ሰቆቃም የሚረሳ አይደለም። እያነባንም ቢሆን ግን እናመሰግናለን፡፡ ከሆነብን የተደረገልን ይበልጣልና፡፡

አንገቷን ለመስበርና ወገቧን ለማጉበጥ የወረደባትን መዓት ሁሉ ችላ፣ ኀዘኗን በሆዷ፣ ፈተናዋን በክንዷ ተሸክማ አልፋ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ዛሬም በጽናት መቀጠሏና አቅጣጫዋን ሳትስት በመንገዷ ላይ መገሥገሷ በርግጥ አስደናቂ ምሥጢር ነው። በጥፋት ውስጥ ልማትን፣ በኀዘን ውስጥ መጽናናትን፣ በችግር ውስጥ በረከትን፣ በጨለማ መካከል ብርሃንን እያበራ የታደገንና ለሀገራችን ድጋፍና መከታ የሆነን የኢትዮጵያ አምላክ ነው፡፡ ይሄንን ጥላ ከለላ፣ አምባ መከታ፣ ጋሻ መሸሻ የሆነ አምላክ ማመስገን የኢትዮጵያውያን ሁሉ የአንድነት ዜማ