Get Mystery Box with random crypto!

እንኳን ለ1443ኛው ዓመተ ሒጅራ የዒድ አል-አድሐ ዐረፋ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን! የዒ | የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ እውነተኛ ደጋፊዎች

እንኳን ለ1443ኛው ዓመተ ሒጅራ የዒድ አል-አድሐ ዐረፋ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን!
የዒድ አል-አድሐ ዐረፋ በዓልን ስናስብ ቀድሞ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው በመንፈሳዊውም ይሁን በሥጋዊው ዓለም ታላቅነት የሚመጣው በፈተና ውስጥ በጽናት ለማለፍ በመቁረጥ እንደሆነ ነው። ነብዩ ኢብራሒም በአላህ (ሱ.ወ) ታዝዘው ልጃቸው እስማኤልን ለመሰዋት ሲነሱ አጋጣሚው ለአባትም፣ ለልጅም ቀላል አልነበረም። እጅግ ከባድ የሆነ የስሜት ፈተና ሲገጥማቸው ነበር። ከአባትነት ስሜት ከሚመነጨው ፈተና ባለፈ፣ ጠላት ሸይጣንም፣ በእርጅና እድሜያቸው ያገኙትን ልጅ ለመሰዋት መዘጋጀታቸው ጅልነት መሆኑን እየጠቀሰ ከመንገዳቸው ሊያስቀራቸው በተደጋጋሚ ፈትኗቸዋል። ነብዩ ግን አልተረቱለትም። መስዕዋት የሚሆነው ልጃቸው እስማኤልም የገዛ ፍርሃቱን አሸንፎ፣ አባቱ የአላህን ትዛዝ እንዲፈጽሙ ሲያበረታቸው ነበር።

የዘንድሮውን የዐረፋ በዓል የምናከብረው የሥነ ልቦና ጥንካሬአችን በሚፈተኑ አጋጣሚዎች መካከል ሆነን ነው። በአንድ በኩል ሰላማችንን የሚረብሹና ጦራቸውን ሰብቀው ሊወጉን አድብተው የሚጠብቁ ጠላቶች በተራቀቀ ሴራ አቅማችንን ሊያዳክሙ ይተጋሉ። በሌላ በኩል የሕዳሴ ግድብ ግንባታችን ወደ ሦስተኛውና ዋናው ምዕራፍ ለማሸጋገር ከጫፍ ደርሰን ተስፋውንና ጠላቶቻችን የደቀኑብን ስጋት በቅርብ ርቀት እየተመለከትን ነው።

ዐረፋ የመስዕዋት በዓል ነውና ይሄንን በዓል ከሙስሊም ዜጎቻችን ጋር ስናከብር መስዕዋት ለመሆን ፍላጎት ማሳየት ብቻውን እንደ ሀገር የሚገጥሙንን ፈተናና አደጋዎች ሊያስወግድልን እንደማይችል በማሰብ ነው። ያለንበት ወቅት እስከ መጨረሻው ጸንቶ መቀጠልን ይሻል። የእኛ አቋም መወላወል የሚጠቅመው ጠላቶቻችንን ነው። እኛን ለማሸነፍ ሌላ ቦታ መሄድ አይገባቸውም፤ ጦር መስበቅ፣ ነጋሪት መጎሰወም ሳይጠበቅባቸው እኛን ለማሸነፍ የእኛኑ አቋም መዋዠቅ ይጠቀማሉ። በእኛ መካከል የሚፈጠረው አለመግባባት ለእኛ የድክመታችን ምንጭ፣ ለጠላቶቻችን ደሞ አቅማቸውን የሚያሳድግ አጋጣሚን ይፈጥራል።

ለውጥ ስንጀምር አብረውን ሊታገሉ፣ በጉዟችን ጽንተው ሊቆሙ፣ የመስዕዋትነት ጊዜው ሲደርስ አብረውን ሊሰዉ ፍላጎት ያሳዩ ብዙዎች ነበሩ። ሰበብ ፈልገው የተለዩን፣ አኩርፈው የቀሩ፣ የቁርጡ ቀን ሲደርስ ሸርተት ያሉ ሰዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ልክ እንደ እስማኤል በአቋማቸው ጸንተው ዛሬም ለመሰዋት የማያመነቱ፣ በርትተው ሌሎችን የሚያበረቱ እውነተኛ የሀገር ልጆችም አሉ።
ውድ የሀገሬ ልጆች፣
ማንም ሰው በተፈጥሮው ክፉ ሆኖ አይፈጠርም። ከልጅነት እስከ እውቀት ክፋትን እየተማረ፣ ቀስ በቀስ ተንኮልና ጭካኔን እየለመደ ይመጣል እንጂ። በጊዜ ሂደት ከላይ በሚደርባቸው የክፋት ጋቢዎች ምክንያት ቀድመው የነበሩት ደግነትና ጥሩነት በልቡ ጓዳ ውስጥ በጥልቁ ተሰውረው ይቀራሉ። የሐይማኖት አስተምህሮዎች ዓላማም ተዳፍኖ የሚኖረውን ይሄን የሰውን መልካምነትና ደግ ጠባይ ከተደበቀበት ፈልፎሎ ማውጣት ነው።

ለመልካም ተግባር የሚጸኑ ሰዎች በመንፈሳዊውም ሆነ በሥጋዊው ዓለም ትልቅ ሥፍራ ይሰጣቸዋል። ነብዩ ኢብራሒም ለሰው ልጆች ሁሉ አርአያ ከሚሆኑ ጻድቅ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው። በሕይወት ዘመናቸው ከልብ በመነጨ ስሜት ሰዎችን የሚወድዱ፣ ራሳቸውን ለእውነትና ለፈጣሪ የሰጡ፣ በደግነት የሚያስተናግዱና ካላቸው ላይ ከፍለው ለሰዎች የሚያጋሩ ነበሩ። ከነብዩ ኢብራሒም መልካምነትን ተምረን የዐረፋን በዓልና ከዚያ በኋላ ያሉ ቀኖችን በመተጋገዝና መደጋገፍ እንድናሳልፍ ይጠበቃል።

ሕዝበ ሙስሊሙ ብቻ ሳይሆን ሌላውም ሕዝባችን በመረዳዳትና በመተሳሰብ ኢትዮጵያን ከፈተና አውጥተን ወደ ምናስበው ስኬት ልናበቃት ይገባል። በቀና ልቦና አቅማችን የፈቀደውን መልካም ነገር በመፈጸም፣ በየተሰማራንበት ዘርፍ ለኢትዮጵያ የሚመጥነውን በማድረግ፣ ለሰላምና ለብልጽግናዋ በመትጋት፣ ለልጅ ልጅ የሚተርፍ አሻራ በማኖር እውነተኛ ኢትዮጵያዊነታችንን ማስመስከር አለብን።

በድጋሚ መልካም የዐረፋ በዓል እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ፣ ዒድ ሙባረክ!!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ሀምሌ 2 ቀን 2014 ዓ.ም.

የቴሌግራም ቻናል https://t.me/abdisira
የፌስ ቡክ ግሩኘ https://facebook.com/groups/1214264802267291/