Get Mystery Box with random crypto!

✥••••✥••••✥••••●✞ ● ✞ ●✞ ●••••✥••••✥••••✥✞ ●••••✥••••✥••••✥ በአ | የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት

✥••••✥••••✥••••●✞ ● ✞ ●✞ ●••••✥••••✥••••✥✞ ●••••✥••••✥••••✥
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሰ/ት/ቤት 60ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባ እና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ እንዲሁም የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤና የቅድስት ሥላሴ ዩንቨርስቲ የቦርድ ሰብሳቢ ፤ ብጹዕ አቡነ እንጦንስ የምዕራብ ሐረርጌ እና የአፋር አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ ፤ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ክብሩ እንዲሁም የደብሩ ሰ/ት/ቤት አባላትና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በድምቀት ተከበረ።

በምሥረታ በዓሉ ዕለቱን የተመለከተ ያሬዳዊ ወረብ በሰ/ት/ቤቱ አባላት ፤ ቅኔ በደብሩ የቅኔ ሊቅ የቀረበ ሲሆን እንዲሁም ሰፊ ትምህርተ ወንጌልም ተሰጥቷል።

ሰ/ት/ቤቱ ሲመሠረት ጀምሮ ላለፉት 60 ዓመታት ያለመታከት በድካምና በብዙ ውጣ ውረድ ያገለገሉትን  አቶ አሰፋ ተስፋዬን ጨምሮ በልዩ ልዩ ዘርፍ አገልግሎቱን ለደገፉ ድርጅቶችና በርካታ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ለሚኖሩ ግለሰቦች እንዲሁም ለደብሩ ሰ/ጉ/ጽ/ቤት ፣ ደብሩን ከአሁን በፊት ሲያስተዳድሩ ለነበሩ የቀድሞ አስተዳዳሪዎችና በአሁኑ ስዓት በማስተዳደር ላይ ለሚገኙት መልአከ ገነት ክብሩ የምሥጋና የምሥክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

በተቋም ደረጃ ኢትዮ ኤፍ ፣ ፋና ትሬዲንግ ፣ አርኪ እና አኳ አዲስ ውሃ ፣ ማኅበረ ቅዱሳን ፣ ኢ/ር ደረጄና ድርጅቱ እንዲሁም ሚልንየም ማተሚያ ቤት ፣ በመርሐ ግብሩ ላይ ምሥጋና ከተቸራቸው መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ባደረጉት ንግግር "የዛሬ 60 ዓመት ህፃን ዛሬ ደግሞ ለሽምግልና ዕድሜ ለደረሰው የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ክ ሰ/ት/ቤት 60ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል። በሰ/ት/ቤት ደረጃ 60 ዓመታትን በፅናት መቀጠል ቀላል አለመሆኑን ገልጸው ይህንን ዕድሜ ያስቆጠረው ሰ/ት/ቤት አንጋፋዎችን ያፈራ አንጋፋ ፣ በተምሮ ማስተማር ረገድም ከአዲስ አበባ ውጭ ላሉ ወጣቶች ተከታታይ የሆኑ የተልእኮ ትምህርት እየሰጠ የሚገኝ እና ለሌሎች ሰ/ት/ቤቶች ጥሩ ምሳሌና ሞዴል የሆነ አምሳለ ኮሌጅ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ብፁዕነታቸው አክለውም  ሰ/ት/ቤት ለቤተክርስቲያን የችግኝ ጣቢያ ነው፣ ቤተክርስቲያን ልጆቿን ነገ  ለምትሰጣቸው ልዩ ልዩ ኃላፊነቶች እየተንከባከበች የምታቆይበት ሥፍራ በመሆኑ ትልቅ ትኩረት ሰጥተን ልንጠብቀውና ልንከባከበው እንዲሁም አስፈላጊውን ሁሉ ልናደርግ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

የምዕራብ ሀረርጌ እና የአፋር አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብጹዕ አቡነ እንጦንስም "እኔ ሰ/ት/ቤቱን የማውቀው  ከረጅም ዓመት በፊት ነው ፣ ብዙ ሊቃውንትን ያፈራ ሰ/ት/ቤት ነው ሲሉ ምሥክርነታቸውን ሰጥተዋል።

በተያያዘ ዜናም ሰ/ት/ቤቱ የምሥረታ በዓሉን አስመልክቶ ለሕጻናትና አብነት ተማሪዎች መማሪያ የሚሆን እና 60 ሚሊየን ብር ወጪ የሚጠይቅ #G+4 ሕንጻ ለመገንባት ባቀደው ዕቅድ መሠረት በብፁዓን አባቶች የመሠት ድንጋይ ተቀምጧል።

✥••••✥••••✥••••●✞ ● ✞ ●✞ ●••••✥••••✥••••✥✞ ●••••✥••••✥••••✥