Get Mystery Box with random crypto!

አንተ ካልወሰንክ ሌላ ሰው ይወስንልሃል! / የአሜሪካ 40ኛው ፕሬዘዳንት ሆኖ ያገለገለው | ቃልህ እውነት ነው ዘኦርቶዶክስ /Your word is Truth Zorthodox/

አንተ ካልወሰንክ ሌላ ሰው ይወስንልሃል!

/

የአሜሪካ 40ኛው ፕሬዘዳንት ሆኖ ያገለገለው ሮናለድ ሬገን (Ronald Reagan) ውሳኔ የማስተላለፍን አስፈላጊነት ገና በልጅነቱ እንደተማረ ይናገራል ፡፡

ገና በልጅነቱ አንድ ጊዜ አክስቱ አዲስ ጫማ ልታሰራለት ወደ ጫማ ሰሪ ቤት ወሰደችው ፡፡ ጫማ ሰሪው እግሩን ከለካው በኋላ ...

“ እንዲሰራልህ የምትፈልገው ጫማ ቅርጹ ከእግር ጣቶች ጋር ክብ እንዲሆን ነው ወይስ አራት ማዕዘን እንዲሆን ነው የምትወደው?” ብሎ ጠየቀው፡፡

ሮናልድ ሬገን መወሰን አቅቶት ሲወላውል ጫማ ሰሪው “ ችግር የለውም ትንሽ ቀናት አስብበትና ትነግረኛለህ” አለው፡፡

ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ጫማ ሰሪው ሬገንን መንገድ ላይ አገኘውና፣ “የጫማውን ቅርጽ ጉዳይ ወሰንክ?” ብሎ ጠየቀው፡፡

ሬገንን፣ “ገና አልወሰንኩም” ብሎ መለሰለት፡፡

ጫማ ሰሪው “እሺ” ብሎ መንገዱን ከቀጠለ በኋላ በሚቀጥለው ቀን ጫማውን ሰርቶ እቤቱ ድረስ ላከለት፡፡ ሬገን ጫማውን ሲያየው የቀኝ እግር ጫማው ቅርጽ ክብ የግራ እግር ጫማው ቅርጽ ደግሞ አራት ማዕዘን መሆኑን ሲመለከት በጣም ደነገጠ፡፡

“ከዚያን ጊዜ ጀምሮ” ይላል ሬገን፣ “እነዚያን የግራና የቀኝ እግር ጫማዎች ባየኋቸው ቁጥር ስለ ውሳኔ ትልቅ ትምህርትን ያስታውሱኝ ነበር::

“አንተ የራስህን ውሳኔ ካልወሰንክ፣ ሌላ ሰው ለአንተ ይወስንልሃል፡፡ የውሳኔውን ውጤት የምትኖረው ግን አንተው ነህ :: "

በሕይወትህ በፍጹም ለሰው የማትተዋቸው “ወሳኝ ውሳኔዎች” እንዳሉ ታውቃለህ?!

በተለይም የሕይወትህን አቅጣጫ እስከወዲያኛው በሚያስቀይሩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔህን ችላ ባልከውና ሰው እንደፈለገ እንዲያደርገው በፈቀድክ ቁጥር ሌላ ሰው ይወስንልሃል፡፡

በዚህ ምድር ላይ ደግሞ ሌላ ሰው የወሰነልህን ውሳኔ መራራ ፍሬ እየበሉ እንደመኖር አስቀያሚ ነገር የለም፡፡

በሕይወታችን “ሁለት አይነት ጫማ አድርገን” ወዲህና ወዲያ የምንንገላታው የምንፈልገውን ነገር ቁርጥ አድርገን አውቀን ውሳኔያችንን እኛው ስላልወሰንን ነው፡፡

በጥንቃቄ፣ በጥበብና በሚዛናዊነት ከሰው ምክርንና ጥበብን ለመቀበል ክፍት የመሆንህን ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ . . .

// //

• የሕይወትህን ዓላማ አስመልክቶ ውሳኔህን በቁጥጥርህ ስር አድርግ፡፡

• የቀረውን ሕይወትህን ከማን ጋር በፍቅር እንደምትኖር ውሳኔህን በቁጥጥርህ ስር አድርግ፡፡

• የምትማረውን የትምህርት ዘርፍ አስመልክቶ ውሳኔህን በቁጥጥርህ ስር አድርግ፡፡

• ከፈጣሪ የተቀበልከውን ማንነትህን የመኖርና ራስህን የመሆንህን ጉዳይ አስመልክቶ ውሳኔህን በቁጥጥርህ ስር አድርግ፡፡

ሰዎች በአንተ ውስጥ ሆነው የመኖራቸውና የመወሰናቸው ዘመን ያብቃ!

ከbookforall ገጽ የተወሰደ