Get Mystery Box with random crypto!

Take time!! by DEMIS SEIFU  “Give me six hours to chop dow | ህይወት ጥበብ ፍልስፍና

Take time!!

by DEMIS SEIFU 

“Give me six hours to chop down a tree and I will spend the first four sharpening the axe.” ― Abraham Lincoln

እየሄዱ መቆም የመሄድን አቅም መጨመር ነው… መዘግየት አይደለም… እያረፉ መጓዝ የብልህነት ከፍታ ነው … ስንፍና አይደለም… ‘በየመሃሉ’ ማለት መታደስ ነው… ኋላ መቅረት አይደለም… ለረጅም ሰዓት ያሽከረከረ ሹፌር ጥጉን ይዞ ‘እረፍት’ የሚወስደው የበለጠ መጓዝ እንዲችል ነው… የጋለው ሞተር ቀዝቅዞ አቅም መግዛት አለበት… የዛለ ክንዱም በርትቶ መሪ ማዞር አለበት… በየሰከንዱ በምንስበው አየር የመታደስ ያህል ነው – ‘በየመሃሉ’ ማለት… አንዴ በሳቡት አየር ዕድሜ ልክ ልኑር አይባልምና…

ሰውየው በአንድ ድርጅት ውስጥ በእንጨት ቆራጭነት ስራ አምስት ዓመት ያህል ቢያገለግልም ሁሌም የደመወዝ እድገት እንደናፈቀው ነው… ከእርሱ በኋላ የተቀጠሩ ሰራተኞች ዓመት ሳይደፍናቸው የክፍያ መሻሻል አይተዋል… እናም ሰውየው ዘወትር ‘ለምን?’ ይላል… የድርጅቱ ኃላፊ ‘እንደምታውቀው ድርጅታችን ውጤት ተኮር ነው… ብዙ የሰራ ብዙ ያገኛል… አንተን እንደማይህ የዛሬ አምስት ዓመት ትቆርጥ የነበረውን እንጨት ነው ዛሬም የምትቆርጠው… ይሄ ደግሞ ላንተ ለውጥም ሆነ ለድርጅቱ እድገት አንዳች አይፈይድም’ ብሎታል… እናም ይለፋል… ይጥራል… ይግራል… ጠብ የሚል ነገር የለም…

በድጋሚ አለቃውን አግኝቶ ጠየቀ… ‘እስኪ ካንተ በኋላ የተቀጠሩትን ቆራጮች ተመልከታቸው… በየጊዜው መሻሻል እያሳዩ ነው… ለምን እነርሱን አታማክራቸውም… ለምሳሌ እከሌን ማናገር ትችላለህ… ምናልባት እኔና አንተ የማናውቀውን ምስጢር ይጠቁምህ ይሆናል’… ሲል መለሰለት…

ሰውየው የተጠቆመው ሰው ዘንድ ሄዶ ችግሩን አስረዳው… ባለሙያውም ሁኔታውን በደንብ ካጤነ በኋላ ‘ለመሆኑ መጥረቢያህን ከሳልከው ስንት ጊዜ ሆነህ?’ ሲል ጠየቀው… እንጨት ቆራጩ እንደ ማሰላሰል አለ… በጣም ቆይቶ ነበር… በጣም… ባለሙያው አከለለት… ‘ይኸውልህ.. እኔ በየጊዜው የተወሰኑ የእንጨት ክምሮችን ከቆረጥኩ በኋላ መጥረቢያዬን እሞርዳለሁ… በዚህም ምክንያት ብዙ እንጨት መቁረጥ ችያለሁ’ አለው… ሰውየው ለረጅም ጊዜ የተደበቀበት የስኬት ምስጢር ለካ ‘በየመሃሉ’ ማለት ነው…

ብዙዎቹ መጥረቢያዎቻችን ደንዘዋል… ችግሩ ዛሬም በትናንት አቅማቸው እንዲያገለግሉን እየጠበቅን ነው… ነጋ ጠባ በሚቆርጡት እንጨት ጥርሶቻቸው ተሸራርፎ አልቋል… ችርችፍ ብሏል… ዶልዱሟል…

ላሞችህ ወተት እንዲሰጡህ የምትጠብቀው መመገብ እንዳለብህ ዘንግተህ ከሆነ ችግር አለ… የገባው ነው የሚወጣው .. መልኩን ከመቀየሩ ውጪ… የአገልግሎት ማሻሻያ ሳያደርግ ከፍተኛ ገቢ የሚጠብቅ ድርጅት… ሳያነብ ልጨኛ ጽሑፍ መፃፍ የሚፈልግ ‘ደራሲ’… በአግባቡ ሳያስተምር ጎበዝ ተማሪዎችን ማየት የሚናፍቅ መምህር… የድርሻውን ሳይወጣ ያደገች ሃገር ማየት የሚሻ ሕዝብ… የሚጠበቅበትን ሳያደርግ የሚጠበቅብህን የሚጠይቅ መንግስት… ለአርዓያነት ሳይበቃ ‘የተመረቀ ልጅ’ የሚጠብቅ ቤተሰብ… ሁሉም የደነዘ መጥረቢያቸውን አስተውለውት አያውቁም… የአንዳንዶቹ እንዲያውም ዝገት ጀምሮታል…

ከድግሪህ በኋላ ማንበብ ካቆምክ ድግሪህ እርባን የለውም… ዶክትሬትም ቢሆን… ከሽልማት በኋላ መስራት ካቆምክ መሸለምህ ከንቱ ነው… ቅዱስም ብትሆን… ዜኖች እንዲህ ይላሉ… “Before enlightenment, chop wood, carry water. After enlightenment, chop wood, carry water.”

መጥረቢያህን ሳል… በመቁረጥ ላይ ብቻ እንደተመሰጥክ ያስታውቃል… ስትሞርድ ስለት ብቻ አይደለም የምትጨምረው… የሆነ የምታራግፈው ቆሻሻም አለ… ውጋጅ ነገር… አሮጌ አስተሳሰብ… ጠማማ ገጽታ… የተንሸዋረረ እይታ… ግድግዳ ኩራት…

ለመሞረድ የምታጠፋው ጊዜ የባከነ አይደለም… ነዳጅ እንደመጨመር ነው… የሆነ ጊዜ ድንገት ቀጥ ትላለህ… ምናልባት ያኔ ለመሞረድ ሁነኛ ጊዜህ አይሆን ይሆናል… እናም መቆሚያህ እንዳያጥር መቋቋሚያህን አጽና…

A woodsman once asked “what would you do if you had just five minutes to chop down a tree?’… He answered, ‘I would spend the first two & a half minutes sharpening my axe.”…

MORAL OF THE STORY
Let us take a few minutes to sharpen our perspective.

ባላችሁበት ሰላም!!

ምርጫችሁ ስለሆንን ስናመሰግኖት ከልብ ነው !!! @zolaarts