Get Mystery Box with random crypto!

ከጥልቅ እንቅልፍ የማይነቃው ፥ ለህዝቡ ህልውናና ጥቅም መቆም ያቃተው የአማራ ልሂቅ ጉዳይ…..!  | ዘሪሁን ገሠሠ

ከጥልቅ እንቅልፍ የማይነቃው ፥ ለህዝቡ ህልውናና ጥቅም መቆም ያቃተው የአማራ ልሂቅ ጉዳይ…..! 

መንግሥት << የአማራ ህዝብ ተስፋ ቆርጦብናል! >> የሚል ግምገማ አለው፡፡ አሸባሪው ትህነግ ደግሞ << ከአማራ ጋር በ83ቱ መንገድ ካልሆነ በስተቀር አይደለም ጦርነት ማሸነፍ ለህልውናችንም ያሰጋናል! >> የሚል ሰሞንኛ የግምገማ ነጥብ ላይ ደርሷል፡፡ 

ባለፈው በድርድሩ ሂደት ወቅት ደግሞ <<  አማራው በህወሓት ወረራም ሆነ በአገዛዝ ዘመኑ ከደረሰበት ውድመትና በደል ብሎም  በመንግሥት አስተዳደር ላይ ተስፋ እየቆረጠ በመምጣቱ በድርድሩ ስለማይስማማ  ፥ በህወሓት ዙሪያ የማይናወጥና ተመሳሳይ የባላንጣነት ስሜት ካላት ኤርትራ ጋር ሆኖ ሊሠለፍ ይችላል! ይህም ስልጣናችንን ወደሚያሳጣ የሀይል አሰላለፍ ሊያስገባው ይችላል፡፡>> የሚል ግምገማ ይዘው ሲንቀሳቀሱ ነበር፡፡

በነገራችን ላይ እቅዳቸው ባይሳካም ፥ በህዝብ ጥቅምና ፍላጎት እንዲሁም በትህነግ ባላንጣነት ዙሪያ ፅኑ አቋም ያላቸው ብሎም ህዝቡን የማደራጀት ተሰሚነት አላቸው የተባሉ በርካታ የአማራ ፖለቲከኞችንና የጦር መሪዎች ተመርጠው   " ከኤርትራ/ ከውጭ ሀይሎች ጋር በመሆን መፈንቅለ-መንግስት ለማድረግ በማሴር" የሚል ዲሪቶ ክስ በማዘጋጀት ወደወህኒ የማውረድ እንቅስቃሴ  ተጀምሮ የነበረው ብሎም ከአዲስአበባ ኤርትራውያንን እየታደኑ እንዲታሰሩ የማድረጉ ሂደት ፥ ...ወዘተ ከዚህ ግምገማ በኃላ የመጡ ናቸው፡፡ 

በጥራቃው ጠቅላይ ሚኒስቴር " ..ህወሓት ጋር ነገሮችን በድርድር ከፈታን ኤርትራን በጋራ ሆነን እንገጥማለን፡፡  .. አማራውን ነጥለን የአሰብን  ስም እየጠራን አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ባንዲራ እያሳየን ከጎናችን  እናሰልፈዋለን! >> እስከማለት የደረሰ የአፍ ወለምታ ውስጥም ገብቶ ሲዳክር እንደነበር  ፥ ሾካኮቹ ሲያንሿክኩ ጭምጭምታዎችን ሰምተን "ጉድድድ..!" ብለን አልፈናል፡፡ ከሰሞኑ የአሸባሪው ትህነግ አፈቀላጤ ጌታቸው ረዳ ፥ ሰአት ጠብቆና "ከረንትሊ ይጠቅመናል!"  በሚል ስሌት ፥ ይህን ጉዳይ በአደባባይ ሲያነሳው  ፥ ብዙዎቹ "የኤርትራን ከመንግሥት ጋር የመተባበር ሂደት ለማዳከም የታለመ ፖለቲካዊ ቀደዳ ነው " ሲሉ  ፤ እኔ ግን ያረጋገጥኩበት ቀድሜ የነበረኝን መረጃ እውነተኛነትና ጉዳዩ ከሹክሹክታም አልፎ ወደጠረጴዛ የደረሰ አጀንዳ  መሆኑን  ነበር ፡፡ 

በነገሬ ላይ ኤርትራ እስከአለም ፍፃሜ ድረስ ብቻዋን እንኳ ብትቀር ህወሓት የተባለውን አሸባሪ ቡድን ከመፋለምና ከመታገል ወደኃላ የማያስብል ፅኑ አቋም አላት! ህወሓትን መታገል የዘላቂ ሰላምና ህልውና ጉዳይ መሆኑን አምነው የቆሙ ናቸው፡፡

ወደነጥቤ ስገባ በግራም ሆነ በቀኝ የአማራ ህዝብ በድርድሩም ሆነ በጦርነቱ አማራጭ ውስጥ ፥ የትኩረትና የስበት ማዕከል ሆኖ ከጀርባ እየተዶለተበት ያለ ህዝብ ነው፡፡ 

አሁንም ምስጢራዊ ድርድሮች በጓሮ በር እየተደረጉ እንደሆነ ሚስጥራዊ የመረጃ ምንጮች እያንሿከኩ ይገኛሉ፡፡ 

ዳንኤል ክብረትን ጨምሮ የመንግሥት ባለሟሎች ዛሬ ድንገት ተነስተው ፥ "ህወሓት በአማራ ህዝብ ላይ ያደረሰውን በደል የሚያሳይ ጥናት ይፋ አደረግን " ብለው የሚደልቁትም ይቺን ስጋትና የቢሆን ግምገማ ያጣፉ መስሏቸው እንጂ ፥ የአማራ ህዝብ ስራአታዊና መዋቅራዊ መከራ የሚጀምረው "ህገ-መንግስት" ከተሰኘው የሀገር ማፍረሻ ውል መሆኑን አምነውና ደፍረው እንኳ የማይናገሩ መሆናቸው የአደባባይ ሀቅ መሆኑ ሳይታወቅ ቀርቶ አይደለም፡፡ በጥናቱ ከህወሓት ባሻገር ብልፅግና የፈፀመው ግፍስ ተካቶ ይሆንን?

ከዚህ አንፃር የአማራ የፖለቲካ ልሂቅ ፥ በሁለት ጠላቶች የጥቅምና የፍላጎት ማርኪያ የትኩረት ነጥብ ለሆነው ህዝባቸውና ቀጣይ ስለተዶነበት ፈርጀ ብዙ የሆነ አደጋ ፥ የቢሆን ትንተና ሰርተው ህዝባቸውን ከጠላት ከፋፋይ አጀንዳ በመጠበቅ በህብረት ለህልውናው እንዲታገል ያለእረፍት መትጋት አልነበረባቸውምን ?

ምን ይሻላል ግን ?