Get Mystery Box with random crypto!

ፍቅር እና ፊዚክስ-3 ....... ካለፈው የቀጠለ በፍቅር፣ ሰው አእምሮ ውስጥ ግዛት መመስረት | ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

ፍቅር እና ፊዚክስ-3
....... ካለፈው የቀጠለ

በፍቅር፣ ሰው አእምሮ ውስጥ ግዛት መመስረት ወንጀል አይደለም፤ ምክንያቱም ዩኒቨርስ የሚገዛበት ሕግ የተለያየ ነውና፡፡

በፍቅር - በሰውና በእግዚአብሔር ላይ ባለመብት ትሆናላችሁ፡፡ በፍቅር ፣መንገድ ላይ አምስት ሳንቲም የሚለምናችሁ ድሃ ፣እናንተ ላይ ባለ መብት ይሆናል፡፡ ባለመብት ከሆናችሁ ደግሞ አዛዥ ትሆናላችሁ ፤ፍቅረኛችሁን ፣ጓደኞቻችሁን፣ ወላጆቻችሁንና ፈጣሪያችሁን ታዙታላችሁ። እነሱም ቢሆኑ ስለ እናንት ፍቅር የእናንተ አገልጋዮችና ተሸናፊዎች ይሆናሉ፡፡ ዳሩ ግን ፍቅር መልሶ እናንተንም የእነሱ አገልጋዮችና ተሽናፊዎትች ያደርጋችኋል፡፡ የምናፈቅረው አሸናፊና ገዢ ለመሆን ሳይሆን ተሸናፊና አገልጋይ ለመሆን ነው፡፡ በመሆኑም በፍቅር ምን አይነት ዓለም ለመፍጠር አቅሙ እንዳላን አስቡት፤ በፍቅር ዓለም ሁሉ ውብ ሆና አትታያችሁም!? መተዛዘን ሰፍኖ፣ ድህነት ተነቅሎ፣ ሀብት ተከፋፍሎ፣ ቴክኖሎጂ እስከ ጥግ ተዳርሶ፣ እኩልነትና ፍትሃዊነት በዓለም ላይ ሰፍኖ ምድር ልምላሜን ፈጥራ የፍቅር ቡራኬ ሲነግስባት አይታያችሁም!? "በምድር ላይ ..." አለ አንስታይን በአንድ ወቅት ስለ እድገት ተጠይቆ፣ “
"በምድር ላይ አንድ የተራበ ህፃን እስካለ ድረስ
እድገት አለ ማለት አይቻልም።"

ብርሃን በዚያ የፍጥነት የመጨረሻ ሃይሉን ተጠቅሞ እንኳን ብዙ የብርሃን ዓመታትን ወስዶ ማቋረጥ የማይችለውን ዩኒቨርስ እናንተ በፍቅር ከመቅፅበት ከዩኒቨርስ ባሻገር ወደሚገኘው ፈጣሪያችሁ ትደርሳላችሁ፡፡ ፍቅር እንዴት አይነት አስገራሚ መጓጓዣ ነው! ክንፍ የሌላችሁን ክንፍ ሰጣችሁ፣ በመሬት የተወሰናችሁትን ከዩኒቨርስ ባሻገር አገነናችሁ፣ ቁሳዊነታችሁን ሽሮ መንፈሳዊ አደረጋችሁ፤ አውሬነታችሁን አጥፍቶ ደግና ሩህሩህ አደረጋችሁ፡፡

በፍቅር ጊዜን አሳጠራችሁት፤ እድሜያችሁንም አስረዘማችሁት፡፡ አንስታይን ጊዜ የሚያጥረው፣ እድሜም የሚረዝመው ፍጥነት ሲጨምር ነው ቢልም እናንተ ግን በፍቅር የተለየ ሕግጋትን ተጎናፀፋችሁ፤ "አንድ ሺውን አመት እንደ አንድ አመት" አደረጋችሁት። በርግጥ አንስታይንም ቢሆን ጊዜን የሚያሳጥረው ፍጥነት ብቻ ሳይሆን ፍቅርም እንደሆነ በአንድ ወቅት "አንፃራዊነትን" ለሠራተኛው ሲያስረዳት እንዲህ ብሎ ነበር፣

"እጅሽን የጋለ ብረት ምጣድ ላይ ለ5 ሰከንድ ብታስቀምጪው 5 ሰዓታት ያህል የቆየሽ ይመስልሻል፤  ከፍቅረኛሽ ጋር 5 ሰዓታት ብትቆይ ግን 5 ደቂቃ እንኳን የቆየሽ አይመስልሽም፤"

በፍቅር የጊዜን ህልውና ትገዘግዙታላችሁ፣ ህልውናንም ትፈታተኑታላችሁ፡፡ ለነገሩ ጊዜ ምን ህልውና አለው? ከአእምሮአችሁ ውጪ ጊዜ ህልውና የለውም፤ እናንተ መኖር ስታቆሙ ጊዜም አብሮ ይሞታል፡፡

ለመሆኑ ፍቅር፣ ዩኒቨርሰ እየተንቀጠቀጠ የሚገዛለትን የተፈጥሮ ሕግ የሚሽርበት ስልጣንና ሃይል ከየት አገኘ? ፍቅር ይሄንን ባህሪውን ፣ሃይሉንና ረቂቅነቱን ከየት አመጣው? ፕሌቶን ጠይቁት፤ ዓለምን ለሁለት ክፍሎ፣ የ"መሆን" እና የ"መምሰል" ዓለም፣ በቦታ - ጊዜ አውታር የተወሰነና ያልተወሰነ ዓለም፣ "የፍፁማዊና የጉድለት ዓለም" በማለት ለሁለት ከፍሎ ያስረዳችኋል፡፡

የ "መሆን ዓለም (The World of Being)..." ይላል ፕሌቶ፣

"የመሆን ዓለም በቦታ - ጊዜ አውታር የማይወሰንና በዓለም ላይ ያሉ ነገሮች ሁሉ በፍፁማዊነት ደረጃ የሚገኙበት ዓለም ነው፤ ፍቅርንም ጨምሮ።"

በመሆኑም ፍቅር ፍፁማዊነት ደረጃን ተላብሶ ከቦታ - ጊዜ አውታር ውጭ ባለው ዓለም ውስጥ በነባራዊነት ይኖራል፡፡ ፍፁማዊ ፍቅር ስጋችን ሊሸከመው አይችልም ያልነው ለዚህ ነው፡፡ "እኔነት" የተጫነበት ስጋችን ፍፁማዊ ፍቅርን ለመሸከም አቅም የለውም፡፡ ፍፁማዊ ፍቅርን ለመሸከም የተለየ አካል ያስፈልገናል፤ ለቦታ-ጊዜ አውታር ሕግ የማይገዛ የተለየ አካልና ባህሪ፡፡ አለበለዚያ ፍፁማዊ ፍቅር አስለቅሶ ያሳልቀናል፡፡ ፍፁማዊ ፍቅር የደግነትና የርህራሔ ሰለባዎች ያደርገናል፡፡ እናም አቅማችን ታይቶ ከፍፁማዊ ፍቅር ተጨልፎ ተሰጠን፤ ጭላፊዋም ብትሆን ግን ምጡቅና ሃያል፤ ከሕግም በላይ አደረገችን፡፡

"ሰውም ቢሆን የፍፁማዊው ዓለም ፍንጣቂ ነው ፤" ይላል ፕሌቶ፡፡ ጠፈር ከአንድ ማእከላዊ ቁስ እንደተበተነው ሁሉ፣ እኛ ሰዎችም ከአንድ ማእከላዊ (ፍፁም) ፍቅር የተዘረጋን ሳንሆን አንቀርም፡፡ ታዲያ ከፍፁማዊ ፍቅር ተጨልፎ የተጫነበትን ሰው እንዲህ በቀላሉ እንዳትመለከቱት።  በአጭር ቁመት፣ በጠባብ ደረት መወሰኑን አትዩ፡፡ ፍቅር እንደ ሞገድ ሲያከንፈው፣ ስፍራና ጊዜን ደምስሶ ከሕግ በላይ ሲሆን እያያችሁ፤ ሰውን በአጥንት የቆመ፣ በስጋ የለሰለሰ፣ በደም የተሞላ፣ ለከርሱና ለፍትወቱ የሚጋደል ተራ ምድራዊ ፍጡር አድርጋችሁ እንዳትመለከቱት፡፡ የስሜት ሕዋሶቻችሁን የመጨረሻው እውነት አድርጋችሁ እንዳታምኗቸው፡፡ የስሜት ህዋሳቶቻችን ብዙ ነገር ደብቀውናል፤ ከብዙ ነገርም ወስነውናል፡፡ "የሰው ልጆች. . ." አለ ስለ አንስታይን ሥራዎች የፃፈው Lincoln Barnett.

"የሰው ልጆች በሌላ በማንም ሳይሆን በራሳቸው የስሜት ህዋሳት ታስረዋል፤ ሌላው ይቅርና አይናችን የx-ray ን ጨረር ማየት ቢችል እንኳ ኖሮ የሰው ልጅ አጠቃላይ ሕይወት አሁን ከምናውቀው ዘይቤ ፈጽሞ የተለየ ይሆን ነበር፡፡"

እናም "ሰው" በስሜት ሕዋሳታችን የተገለጠውን አይነት አይደለም፤ ከዛ በፍፁም የተለየ ነው፡፡ "ሰው..." ይላል ፕሌቶ፣

"ሰው በሕዋሳት አማካኝነት የምናየውን በቁመት፣ በመልክና በሁኔታ የተለያዩ ግለሰቦችን ብቻ ማለታችን አይደለም፡፡ ሰው አማራ - ትግሬ፣ ክርስቲያን - ሙስሊም፣ ጥቁር - ነጭ፣ ረጅም - አጭር፣ ቀጭን - ወፍራም፣ ወንድ- ሴት አይደለም፡፡ ሰው እከሌ ሳይሆን ሁለንተናዊ የሆነ፣ ሊዳስስ የማይችል፣ ግለሰቦች ከሚያሳዩት ተላዋዋጭና ግላዊ ጠባይ የተላቀቀ፣ የሰውን ዘለዓለማዊ ህልውና በሚገልጽ መለኮታዊ (ፍፁማዊ) አለም ውስጥ የሚመደብ ነባራዊ እውነት ነው፡፡"

ነባራዊ እውነት ደግሞ ምንድ ነው? ነፍስ፣ ህያው ህልውና፡፤

ምንጭ ፦ ፍልስፍና ፩
ፀሀፊ ፦ ብሩህ አለምነህ

@Zephilosophy
@Zephilosophy