Get Mystery Box with random crypto!

'ፍቅር ግንኙነት ሳይሆን የመሆን ሁኔታ ነው' ምንጭ ፦ ህያውነት (ኦሾ) ተርጓሚ ፦ ሀብታሙ ተስፋ | ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

"ፍቅር ግንኙነት ሳይሆን የመሆን
ሁኔታ ነው"

ምንጭ ፦ ህያውነት (ኦሾ)
ተርጓሚ ፦ ሀብታሙ ተስፋዬ

ፍቅር ግንኙነት ሳይሆን የመሆን ሁኔታ ነው፤ ከማነም ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ አንድ ሰው ፍቅር ውስጥ ነው ወይም አፍቅሯል ሳይሆን የሚባለው <እገሌ ፍቅር ነው> ነው የሚባለው፡፡ በእርግጥ አንድ ሰው ፍቅር ሲሆን በፍቅር ውሰጥ ነው ያለው ነገር ግን ይህ ምርጫ ሳይሆን ውጤት ነው፡፡ ምንጩ ፍቅር መሆኑ ነው፡፡

ማን ፍቅር ሊሆን ይችላልን? ማን እንደሆናችሁ የማታውቁ ከሆነማ ፍቅር ልትሆኑ አትችሉም፡፡ ይልቁኑ ፍርሃት ትሆናላችሁ፡፡ ፍርሃት የፍቅር ተቃራኒ ነው፡፡ ሰዎች እንደሚያስቡት የፍቅር ተቃራኒ ጥላቻ አይደለም፡፡ ጥላቻ የፍቅር ተቃራኒ ሳይሆን ፍቅር ተገልብጦ ሲቆም ነው፡፡ እውነተኛ የፍቅር ተቃራኒ ፍርሃት ነው፡፡ ፍቅር ያሰፋል፣ ፍርሃት ያጠብባል፡፡ ፍርሃት ይዘጋል፣ ፍቅር ይከፍታል፡፡ ፍርሃት ያጠራጥራል፣ ፍቅር ያሳምናል፡፡ ፍርሃት ብቸኛ ያደርጋል፡፡ ብቸኛ ከማድረግም አልፎ ያጠፋል፡፡ የሌለ ሰው እንዴት ብቸኛ ይሆናል? እነዚህ ዛፎች፣ አዕዋፋት፣ ደመናዎች፣ ፀሃይ፣ ከዋክብት በሙሉ እናንተ ውሰጥ ናቸው፡፡ ፍቅር ማለት ውስጣዊ ቁልፋችሁን ስታውቁ ነው::

ማንም ህፃን ከፍርሃት ነፃ ነው፤ ህፃናት የሚወለዱት ያለምንም ፍርሃት ነው፡፡ ማህበረሰቡ ፍርሃት አልባ እንዲሆኑ ቢረዳቸውና ቢደግፋቸው ዛፎችና ተራሮች ላይ እንዲንጠለጠሉ፣ ውቅያኖሶችንና ወንዞችን እንዲያቋርጡ በረዳቸው ነበር፡፡ ማህበረሰቡ ጀብደኛ እንዲሆኑ፣ ካረጀ እምነት ይልቅ የማይታወቀውን እንዲመረምሩ ቢያደርጋቸው ኖሮ፤ ታላላቅ የህይወት አፍቃሪዎች ባደረጋቸው ነበር፡፡ ይህ ነው እውነተኛ ሃይማኖት፡፡ ከፍቅር በላይ ሃይማኖት የለም፡፡

ተመሰጡ፣ ደንሱ፣ ዝፈኑ፣ ወደ ውስጣችሁ ጠልቀችሁ ግቡ፡፡ የአዕዋፋቱን ዝማሬ በአንክሮ አድምጡ፡፡ አበቦቹን በአድናቆት ተመልከቱ፡፡ አዋቂ አትሁኑ፤ ነገሮችን አትፈርጁ አዋቂ መሆን ማለት ይህ ነው ለእያንዳንዱ ነገር መደብ፣ ፈርጅ ማውጣት፡፡ ከሰዎች ጋር ተገናኙ፣ ከሰዎች ጋር ተቀላቀሉ፣ በተቻላችሁ መጠን ከብዙ ሰዎች ጋር ተገናኙ፡፡ እያንዳንዱ ሰው በተለያየ ሁኔታ የእግዚአብሄርን መልክ ያሳያል፡፡ ከሰዎች ተማሩ፡፡ አትፍሩ፡፡

ፍቅር እምብዛም የማይገኝ አበባ ነው፡፡ ብቅ የሚለው አንዳንድ ጊዜ ነው፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች አፈቀርን ብለው የውሸት ኑሮ ይኖራሉ፡፡ እንደሚያፈቅሩ ያምናሉ፡፡ ከእምነት የዘለለ ግን አይደለም፡፡

ፍቅር ብርቅዬ አበባ ነው:: ብቅ የሚለው አልፎ አልፎ ነው፡፡ የሚከሰተው ፍርሃት ሳይኖር ሲቀር ነው፡፡ ይህም ማለት ፍቅር የሚከሰተው በጣም መንፈሳዊ ሃይማኖተኛ ለሆነ ሰው ነው፡፡ ሁሉም ወሲብን፣ መላመድን ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ፍቅርን ግን ሁሉም አያገኙትም፡፡

ፍቅር ድፍረት ይሰጣል፤ ፍቅር ፍርሃትን ያጠፋል ጨቋኞች የእናንተ ፍርሃት ጥገኛ ናቸው፡፡ አንድ ሺ አንድ ፍርሃት ይፈጥሩባችኋል፡፡ ስለዚህ በፍርሃት ትከበባላችሁ፤ ሥነ - ልቡናችሁ በፍርሃት ይሞላል፤ በውስጣችሁ ትሸበራላችሁ:: ፊታችሁ አንድ አይነት ገፅታ ብቻ ነው ያለው፣ ውስጣችሁ ግን በፍርሃት ድርብርብ የተሞላ ነው::

በፍርሃት የተሞላ ሰው ምርጫው ጥላቻ ብቻ ነው - ጥላቻ ተፈጥሯዊ የፍርሃት ውጤት ነው፡፡ በፍርሃት የተሞላ ሰው በብስጭት የተሞላ፣ ከህይወት የወጣ ነው፡፡ በፍርሃት የተሞላ ሰው ማረፊያው ሞት ይመስላል፡፡ ፈሪ ሰው ከህይወት በተፃራሪ ራሱን የሚያጠፋ ነው፡፡ ህይወት አደገኛ ትሆንበታለች፡፡ ለመኖር ማፍቀር ያስፈልጋል፡፡ ስጋ ለመኖር መተንፈስ እንደሚያስፈልገው፣ ለነፍስም ፍቅር ያስፈልጋታል፡፡ ፍቅር ደግሞ ክፉኛ ተበክሏል፡፡

የፍቅር ሃይላችሁን በክላችሁ በውስጣችሁ መከፋፈል ፈጥራችኋል፤ ውስጣችሁን ለሁለት ከፍላችሁታል፡፡ የርስ በርስ ግጭት ፈጥራችሁበታል፡፡ ሁልጊዜም በግጭት ላይ ናችሁ:: በዚህ ግጭት ሃይላችሁ ተሟጥጧል፡፡ ስለዚህም ህይወታችሁ ደስታ የራቀው ሆኗል፡፡ በሃይል የተሞላ ሳይሆን የደነዘዘ ጣዕም የሌለው፣ ብልህነት የሌለው ህይወት ሆኗል፡፡

ፍቅር ብልህነትን ይስለዋል፤ ፍርሃት ደገሞ ያዶለዱመዋል፡፡ ብልህ መሆን ማን ይፈልጋል? ስልጣን ላይ ያሉ ይህን አይፈልጉም፡፡ እናንተ ብልህ እንድትሆኑስ እንዴት ሊፈልጉ ይችላሉ? ብልህ ከሆናችሁ እቅዳቸውን ጨዋታቸውን ትነቁባቸዋላችሁ፡፡ ስለዚህ መሃይም እና የማይረባ እንድትሆኑ ይፈልጋል፡፡ ስራን በተመለከተ ውጤታማ እንድትሆኑ ይፈልጋሉ፤ ብልህ እንድትሆኑ ግን አይፈልጉም፡፡ በዝቅተኛ አቅማችሁ እንድትኖሩ ነው የሚፈልጉት፡፡

የሳይንስ ተማራማሪዎች እንደሚናገሩት የሰው ልጅ በመላ የህይወት ዘመኑ የአቅሙን አምስት በመቶ ብቻ ነው የሚጠቀመው፡፡ ተራው ሰው አምስት በመቶውን ከተጠቀመ ልዩ የሆነ ሰውስ? አልበርት አንስታይን፣ ሞዛርት፣ ቤትሆቨን? ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት በጣም ከፍተኛ ተሰጥኦ ያላቸው እንኳን ከአስር በመቶ በላይ አይጠቀሙም፡፡ እና የላቀ ችሎታ አላቸው የምንላቸው እንኳን አስራ አምስት በመቶውን ብቻ ነው የሚጠቀሙት፡፡

ሁሉም ሰው የአቅሙን መቶ በመቶ የሚጠቀም ቢሆን ይህች ዓለም ምን እንደምትመስል አስቡ.... ጣዖታት በምድር ቀንተው ምነው ምድር ላይ በተወለድን ይሉ ነበር፡፡ ምድር ገነት ትሆን ነበር፡፡ አሁን ግን ሱዖል ናት፡፡

የሰው ልጅ ብቻውን ቢተው፣ ሳይበከል ቢቀር .... ፍቅር ቀላል ይሆን ነበር፤ ምንም ችግር አይኖርም፡፡ ቁልቁል እንደሚወርድ ውሃ ወይም ሽቅብ እንደሚወጣ ትነት፣ እንደሚያብቡ ዛፎች፣ እንደ ዘማሪ አዕዋፋት ይሆን ነበር፡፡ ተፈጥሯዊና ህያው ይሆናል!

ነገር ግን የሰው ልጅ ብቻውን አልተተወም፡፡ አንድ ህፃን ሲወለድ ጨቋኞች ዘልለው ሃይሉን ያደቁታል፤ ሃይሉን ያዛቡታል፤ መኖር ያለበትን ያህል ሳይሆን የውሸት ህይወት እየኖረ እንደሆነ እንዳያውቅ፣ እየኖረ ያለው በእውነተኛ ነፍሱ እንደሆነ እንዳይገነዘብ ያደርጉታል፡፡ ለዛም ነው በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች በዚህ ስቃይ ውስጥ የገቡት - እነዚህ ሰዎች እንደተሰናከሉ ራሳቸውን እንዳልሆኑ፣ አንድ የተሳሳተ ነገር እንዳለ.... ይሰማቸዋል ።

@Zephilosophy
@Zephilosophy