Get Mystery Box with random crypto!

መንፈሳዊ ነፃነት ምንጭ ፦ የህይወት ኬሚስትሪ (ሳድጉሩ) ትርጉም ፦ ሀኒም ኤልያስ ነፃነት ወይም | ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

መንፈሳዊ ነፃነት

ምንጭ ፦ የህይወት ኬሚስትሪ (ሳድጉሩ)
ትርጉም ፦ ሀኒም ኤልያስ

ነፃነት ወይም ነፃ መሆን የሚለውን ቃል ስትናገር ሰዎች በአይነ ህሊናቸው የሚያዩት ወፍ ስለመሆንና በሰማይ ላይ ስለመብረር ነው፡፡ የወፍ ተመልካች ከሆንክና ወፎች ሲበሩ ካየህ፣ እንደ ጭልፊት ወይም ንስር ያሉ ድንቅ ወፎችም ሳይቀሩ ሲበሩ ወደ መሬት እየተመለከቱ መሆናቸውን ማወቅ ትችላለህ። ከታች የሚበሉበት  ‌ ነገር እየፈለጉ በመሆኑ ምናልባት እየበረሩ በመሆናቸው እንኳን ደስ አይላቸውም ይሆናል፡፡ መብረር ለእነርሱ፣ ልክ አንተ ወደ ቢሮ እንደምትሄደው ሁሉ የመኖር ሂደት እንጂ ነፃነት አይደለም፡፡

እዚህ ላይ ነፃ ነህ ሲባል ከህልውና ነፃ ነህ ማለት ነው፡፡ ከራስ ህልውና ነፃ ነህ ማለት ነው:: ህልውናህ አልቋል። ህልውና ‌ ከሌለ ከነፃነትም እንኳን ነፃ ነህ፤ ምክንያቱም ነፃነትም የተወሰነ እስራት ነው። በሕይወት እስካለህ ድረስ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የታሰርክ ነህ፡፡ በአካል መኖር ራሱ አንድ ዓይነት እስራት ነው፡፡ ሥጋዊ አካልህን ጥለህ በሌላ መንገድ የምትኖር ከሆነም፣ አሁንም ሌላ ዓይነት እስራት አለ፡፡

በመጨረሻ እያንዳንዱ ፍለጋ ከህልውና ባሻገር መሄድ ይፈልጋል። ይህ ፍለጋ በህልውና ሂደት ውስጥ መሆን አይፈልግም፤ ይህ ማለት መወለድና መሞት ወይም ሌላ ነገር ማለት ሊሆን ይችላል። መኖር ሁልጊዜ ሂደት ነው። ፀሐይ ሂደት ናት፤ አጠቃላይ የፀሐይ ስርአት ሂደት ነው፤ ጋላክሲ ሂደት ነው፤ ሁሉም ጋላክሲዎች አንድ ላይ መጣመራቸው ሂደት ነው፡፡ ከሁሉም ሂደቶች ነፃ ለመሆን ከፈለግክ፣ መኖርህን ማቆም አለብህ ማለት ነው፤ ሌላ መንገድ የለም፡፡

ህልውና ማቆም አለበት፤ ምንም ሂደት የማይኖረው ከዚያ በኋላ ብቻ ነው፡፡ ግን የዚህ ጥቅሙ ምንድነው? አንድ ሰው ሕይወቱን ተመልክቶ “ጥቅሙ ምንድን ነው?” የሚለውን ካየ፣ ያ አንድን ሰው መንፈሳዊ ነፃነት እንዲፈልግ የሚያደርገው ሀሳብ ነው። በአሁኑ ጊዜ ሰዎች ገና ህጻናት ስለሆኑ ጥቅሙ ምንድን ነው? የሚለው ሀሳብ ጥልቀት አሁንም ገና አልተከሰተላቸውም፡፡ ያደገ አካላዊ ሰውነት ሊኖራቸው ይችላል፤ በመረዳት ረገድ ግን ገና ልጆች ስለሆኑ፣ ይህንንም ያንንም ማየት ይፈልጋሉ፡፡ የመቶ አመታት የሕይወት ዘመን ትዝታ ቢከፈትልህ፣ ደግመህ ደጋግመህ በተመሳሳይ ከንቱ ነገር እየሄድክ እንደሆነ ታያለህ፡፡ ከዚያ ጥቅሙ ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ ትጠይቃለህ፡፡ እንደገና በሌላ ሴት ማህፀን ውስጥ ብትገባና እንደገና ብትወለድ ጥቅሙ ምንድነው? ይህንን ጥያቄ በተቻለ መጠን በጥልቀት የምትጠይቅ ከሆነ፣ የመንፈሳዊ ነፃነት ናፍቆትህ ፍጹም ይሆናል፡፡

መንፈሳዊ ነፃነት ማለት ከሕይወትና ከሞት ሂደት ነፃ መሆንን መፈለግ ነው፡፡ እየተሰቃዩ ያሉ ሰዎች መንፈሳዊ ነፃነት ሊያገኙ አይችሉም። ደህና ነህ፣ ደስተኛ ነህ፣ ነገር ግን መዋለ ህፃናት ውስጥ መሆን ይበቃሃል፤ ወደ ፊት መቀጠል ትፈልጋለህ። የትምህርት ቤት ሕይወትህ እጅግ ቆንጆ ቢሆን፣ ኮሌጅ መግባት አትፈልግም? ነፃ መሆን መፈለግ ማለት እንደዚያ ማለት ነው፡፡ ሞት ማለት የአካል ፍጻሜ ማለት ነው፤ በመንፈሳዊ ነፃነት ግን ሁሉም ነገር ያበቃል፡፡ በአንድ በኩል መንፈሳዊ ነፃነት የሞትና የልደት መጨረሻ ነው፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ሞት መጨረሻው አይደለም፤ ምክንያቱም ሞት የሚባል ነገር የለም፡፡ ያለው ሕይወት ነው፣ ሕይወትና ሕይወት ብቻ። ሞት የሚኖረው ስለ ሕይወት ምንም ግንዛቤ ለሌለው ሰው ብቻ ነው።

@Zephilosophy
@Zephilosophy