Get Mystery Box with random crypto!

የፖለቲካ ጠቅላላ ደስታ «ጠላት» ውስጥ የተደበቀ ነው በመሬት ላይ ሳይሆን በካርታ ላይ ብቻ የሚገ | ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

የፖለቲካ ጠቅላላ ደስታ «ጠላት» ውስጥ የተደበቀ ነው

በመሬት ላይ ሳይሆን በካርታ ላይ ብቻ የሚገኙትን የወሰን መስመሮች ካጠፋናቸው ስለ ፖለቲካ የሚጨነቅ ማን ይኖራል? አዎ' አንድ የዓለም መንግስት ይኖራል። ይህ መንግስት ግን አገልጋይ ብቻ ነው የሚሆነው:: ከማንም ጋር ስለማይፎካከር የተለየ ክብር አይሰጠውም፡፡ የዓለም መንግስት ፕሬዝዳንት ሆናችሁ ታዲያ ምን ይጠበስ? መንግስት ብትሆኑም ከማንም አትበልጡም፡፡ . .. .

የሃገራት ኢጎ መጥፋት አለበት፡፡ የሃገራት ኢጎ ሲጠፉ ፖለቲካም ይጠፋል፤ ራስን በራሱ ያጠፋል። እንክብካቤ የሚያደርግ አንድ የስራ (ተግባር) ድርጅት ብቻ ይቀራል። ልክ እንደ ሮታሪ ክለብ ስለሚሆን መሪው አንዳንድ ጊዜ ጥቁር ይሆናል፤ አንዳንድ ጊዜ ሴቶች ይሆናሉ፤ አንዳንድ ጊዜ ቻይናዊ ይሆናል፣ አንዳንድ ጊዜ ሩሲያዊ ይሆናል፤ አንዳንድ ጊዜ አሜሪካዊ ይሆናል - ልክ እንደጕማ ይሽከረከራል።

አንድ ሰው ከአንድ ጊዜ በላይ ባይመራ መልካም ነው፡፡ ከዚያ በላይ ሲሆን አደገኛ ይሆናል፡፡ አንድ ሰው እንደ ፕሪዝዳት ከሆነ በኋላ ተመልሶ አይሾምም፡፡ አንድ ሰው ደጋግሞ ከተመረጠ የብልህነት ድህነት ይመጣል፡፡ ለናንተስ እንደ የብልህነት ድህነት ሆኖ አይታያችሁም?

ሰውን አሁን ባለው ደረጃ ስንመለከተው መንግስት እንደሚያስፈልግ እንገነዘባለን፤ ፖሊስ እንደሚያስፈልግ እንገነዘባለን፡፡ አለበለዚያ ይህን ተከትሎ ነፍስ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ዘረፋ ይስፋፋል. . . ህይወት ሁከት የበዛባት ትሆናለች፡፡ ቁጥጥር ሲጠፋ ሁካታ ይነግሳል፡፡ ሰዎች በቡድን ተደራጅተው ደካሞችን ይበዘብዙና ህይወት የተሻለች በመሆን ፈንታ አስከፊ ትሆናለች::

መለወጥ ከቻልን፣ ብዙ ሰዎችን ወደ ተመስጥኦ ካመጣን፤ ብዙ ሰዎችን እውነተኛ ና ተፈጥሯዊ ኑሮ እንዲኖሩ ፣ ፍቅር እንዲጋሩ፣ ህያው ለሆነ ነገር ሁሉ ትልቅ ርህራሄ እንዲኖራቸው፣ ለህይወት ከበሬታ እንዲኖራቸው ማድረግ ከቻልን. ..

እነዚህ ግለሰብ አብዮተኞች፣ እነዚህ ግለሰብ አማፅያን (የፖለቲካ አማፅያን) ብቻ አይሆኑም ፤ ተቃውሟቸው ባለፈ ልምዳቸው ላይ በሙሉ ይሆናል። የማንነታቸውን ማዕከል የሚያገኙ ይሆናሉ. . . አዎን፣ ደስተኛ የሆኑና ምድርን የማይክዱ ግለሰቦች እየመጡ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በሁሉም ሰዎች ተፈጥሯዊ ያልሆነ ስነልቦና የህይወት መንገድ የማይደግፉ ናቸው። እነዚህ ግለሰቦች በመላው ዓለም እንደ ሰደድ እሳት ቢበተኑ የቁጥጥር አለመኖር ፍልስፍና ግብ መሆኑ ቀርቶ ተረፈ ምርት ይሆናል።

መንግስታት የሰዎችን ግለሰባዊነት ክፉኛ ጎድተውታል። ሁሉንም ህጎች፣ ፍርድ ቤቶችና ዳኞች ይቃወማል - ምክንያቱም እነዚህ ሁሉ ፍትህን የሚያስጠብቁ፣ ለደካሞች የቆሙ፣ ለተበዳዮች የሚከራከሩ አይደሉም - እነሱ የቆሙት ስልጣን ላላቸው፣ ለተቋማትና ለሃብታሞች ነው። ከፍትሃዊነት በስተጀርባ በሰው ልጅ ላይ ታላቅ ደባ ይፈፅማሉ፡፡

መጪው ጊዜ እንደ ባኩኒን፣ ባክሃሪን፣ ቶልስቶይ፣ ለመሳሰሉ ሰዎች ታላቅ ከበሬታ ይሰጣል - ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ሳይንሳዊ አሳቢያን ባይሆኑም ቢያንስ ሃሳቡን ፈጥረዋል፡፡ መሰረቱን ሳይጥሉ ስለ ቤተ - መቅደሱ ማውራት ጀምረዋል፡፡

የእኔ ጥረት በሙሉ በቤተ - መቅደሱ ላይ ሳይሆን መሰረት በመገንባቱ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ከዚያ በኋላ መቅደሱን መስራት አስቸጋሪ አይሆንም:: ቁጥጥር አያስፈልግም የሚለው ፍልስፍና በስነ - ልቦና ረገድ ጤናማ የሆነ፣ ጫና የሌለበት ፣ መንፈሳዊ ጤና ያለው፣ የውጫዊውን ዓለም ውበትም ሆነ ውስጣዊውን የንቃት ሃብት የሚያውቅ ማህበረሰብ ተረፈ - ምርት ይሆናል፡፡ በቅድሚያ እንዲህ አይነት ሰዎች ካልኖሩ በቀር ፍልስፍናው እውን ሊሆን አይችልም! እንደ ተረፈ ምርት ብቻ ነው መምጣት የሚችለው::

አንድ ነገር ልትገነዘቡ ይገባል። ዓለም ነፃነትን እንድታገኝ ከተፈለገ ፖለቲካ ያን ያህል አስፈላጊ አይሆንም፡፡ ከዙፋኑ ሊወርድ፣ ስልጣኑ ሊቀንስ ይገባል - ሰልጣን ሊኖረው የሚገባበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ መንግስት እንደ ፖስታ ቤት ሰራተኛ ሊሆን ይገባዋል። የፖስታ ቤት ሃላፊው ማን እንደሆነ የሚያውቅ ማንም አይኖርም፡፡ ስለፖለቲከኞች ጥሩ እና ትልቅ ስም ሰጧቸው፣ ነገር ግን ያን ያህል ትኩረት ሰጥቶ እነዚህን ለዘመናት የሰውን ልጅ ሲያሰቃዩ የኖሩ ሰዎች በየጋዜጣው የፊት ለፊት ገፅ ላይ ማስፈሩ አላስፈላጊ ነው፡፡

ከፖለቲካ ጋር ምንም የማያገናኛቸውን የተለዩ የገለፃ እና የፈጠራ መንገዶችን ተጠቀሙ:: ከፖለቲካ ግንኙነት የሌላቸውን፣ የስልጣን ፍላጎት የሌላቸውን፣ ህይወትን በምሉዕነት የሚኖሩትን ሰዓሊያን፣ ገጣሚያን፣ ቀራፂያን እና ዳንሰኞች ያቀፉ ትናንሽ ማህበራትንና መንደሮችን መስረቱ፡፡

መላው ህብረተሰብ ቀስ በቀስ የፈጠራ ሰዎች በሚሰባሰቡባቸው መንደሮች ይከፋፈል፡፡ በዓለም ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አያስፈልግም። እያንዳንዱ ፖለሰብ በራሱ መቆም መቻል አለበት፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ የሚኖረው ለምንድነው? ምንም ምክንያት የለም። አንድ የገንዘብ ሚኒስትር ካስፈለጋችሁ ሁሉም የኢኮኖሚ እና የገንዘብ ባለሙያዎች ተወዳድረው አንዱ ሊመረጥ ይችላል፡፡ ሌላ ፓርቲ አያስፈልግም። ከፓርቲ ፖለቲካ ወጥተን ወደ ንፁህ ግለሰባዊነት - ከዲሞክራሲ፣ ከአምባገነናዊነት ወደ ሜሪቶክራሲ መሸጋገር አለብን።

ወሳኙ ነጥብ ችሎታ መሆን አለበት፡፡ ትላልቅ ችሎታ ያላቸው ብዙ ሰዎች አሉን - ነገር ግን የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን የለባቸውም፤ ራሳቸውን ዝቅ ማድረግም የለባቸውም። የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን ለእነሱ ዝቅ ያለ ነገር ነው- ድምፅ እንዲሰጣቸው መለመን፣ ማሟላት የማይችሉትን ሃሰተኛ ነገር ቃል መግባት ዝቅ ያለ ነገር ነው፡፡ ስለዚህም የፖለቲካ ፓርቲ አባል የሚሆኑት በሶስተኛ ደረጃ የሚኖሩ፣ ተራ ሰዎች እንጂ ምርጥ የሚባሉት አይደሉም፡፡

ምርጦቹ ማህበረሰቡን መምራት የሚችሉት መሆን አለባቸው። በየመስኩ ብዙ ተሰጥኦ ያላቸው ሰዎች አሉን፣ ነገር ግን እነዚያን የተሰጥኦ ሰዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም ፕሬዝዳንት ሆነው እናገኛቸው:: የፖለቲካ ፓርቲዎች የማይኖሩ ከሆነ ፕሬዝዳንቶች ና ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሊሆኑ ይችላሉ። ተስጥኦዎቻቸው በቂ ስለሆነ ከእነሱ ጋር የሚወዳደር አይኖርም:: የእናንተን ድምፅ መለመን አይኖርባቸውም፣ በሙሉ ድምፅ ይመረጣሉና::

ጨለምተኛ መሆን፣ ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም፡፡ በታሪክ ያየነውን የማያቋርጥ ውድቀት በመገንዘብ ተፈጥሯዊ ነው ልንል እንችላለን፡፡ ይህን ግን ለማንም አይጠቅምም፡፡ አንድ መንገድ ማግኘት አለብን. .. አሮጌዎቹ ሙከራዎች ለምን እንዳልተሳኩ ማወቅና አዳዲስ ዘዴዎችንና ስትራቴጂዎችን መተለም አለብን፡፡ በመላው ዓለም የሚገኙ ወጣቶች በአንድ አይነት ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ከመሆናቸው በተጨማሪ አሮጌዎቹን መዋቅሮች በሙሉ ለውጠው የሰውን ልጅ ነፃ ለማድረግ ዝግጁ ናቸው፡፡

ነፃነት የሰው ልጅ ሰውነቱን የሚያገኝበት መንፈሳዊ ነገር ነው። ከሞቱ የማይረቡ አስተሳሰቦች፣ ርዕዮተ- ዓለሞች፣ ቀኖናዎች ነፃ መዉጣት አስፈላጊ ነው። ከእነዚህ ነገሮች ነፃ ስትሆኑ ክንፍ አውጥታችሁ በስማይ ላይ የምትበሩ ያህል ይሰማችኋል፡፡

ምንጭ ፦ ህያዉነት፫ (ኦሾ)
ተርጎሚ ፦ ሀብታሙ ተስፉዬ
               ተስፋሁን ምትኩ

@Zephilosophy
@Zephilosophy