Get Mystery Box with random crypto!

አእምሮአችን እየተጠቀመብን ነው ወይስ እየተጠቀምንበት? አእምሮ መሳሪያ ነው። የምትጠቀምበት የሆነ | ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

አእምሮአችን እየተጠቀመብን ነው ወይስ እየተጠቀምንበት?

አእምሮ መሳሪያ ነው። የምትጠቀምበት የሆነ አንድ የተለየ ተግባርን ትከውንበት ዘንድ ለአንተ የተዘጋጀ መሳሪያ፡፡ እናም ተግባሩ ተከውኖ ሲያልቅ የምታሳርፈው ድንቅ መሳሪያ (ማሽን) ነው። ከ80 እስከ 90 በመቶ ያህሉ የአብዛኛዎቹ ሰዎች ሀሳብ ተደጋጋሚ እንዲሁም የማይጠቅም እንቶ ፈንቶ ነው፡፡ ይህም ብቻም አይደለም አዕምሮ በተፈጥሮው ፈሩን የመልቀቅና አሉታዊ ነገሮች ጋር የመጠናወት አባዜ አለበት። እናም አዕምሮ ይህ አይነቱ ባህሪ ስላለበት የጥቅሙን ያህልም ጎጅነቱም የዚያኑ ያህል ነው። አዕምሮህን ልብ ብለህ አስተውለው እናም ይህ እውነት መሆኑን እራስህ ትደርስበታለህ።

እንደ እውነቱ ከሆነ አዕምሮ የዚህ አይነቱ በሀሳብ የመጠመድ አባዜ ሱስ ይሆንበታል፡፡ ልክ እንደማንኛውም ሱስ አስያዥ ነገር አዕምሮም የማሰብና በሀሳብ የመባዘን ሱስ ይይዘዋል። ለመሆኑ የሱስ መገለጫዎች ምንድን ናቸው። እጅ ሰጥተሀል፣ ለመተውም አቅቶሀል፣ ለመተው አማራጭ እንዳለህ እንኳ አልታይህ ብሎሀል። ሱሡ ከአንተ የበለጠ ብርቱ የመሰለብህ ሆኗል። በተጨማሪም ሱሡ የውሽት የሆነ የደስታ ስሜትን ሰጥቶሀል፣ ውሎ አድሮ በስተመጨረሻ ስቃይ የሆነ ደስታ፡፡

ለመሆኑ ማሰብ ምን ሊፈይድልን ነው ከማሰብ ጋር ሱስየሚይዘን?

ምክንያቱም አንተ ከአዕምሮህ ጋር እንዲሁም ከሀሳብ ጋር ተቆራኝተሀልና ነው። ማለትም አንተ ማንነትህን የምትረዳውና የምትመዘዉ ከአእምሮህ ውስጥ ከታጨቀ ፍሬ ሀሳብና ድርጊት ስለሆነ ነው፡፡ ምክንያቱም ማሰብ ካቆምኩ አከተመልኝ ብለህ ስለምታምን ነው፣ አስተዳደግህን ተከትሎ በተገራህበት ግለሰባዊና ባህላዊ አተያይ መሰረት በአዕምሮህ ውስጥ የማንነት ምስል ትፈጥራለህ፡፡ ይህንን ምስልም የእራስ ወዳዱ እኔነት የገዛ ራሱ መንፈስ ብለን ልንጠራው እንችላለን፡፡ ይህ የአዕምሮ ተግባራቱንም ያካትታል፡፡ እናም አዕምሮ ህልውናውን የሚያስቀጥለውም ያለማቋረጥ በማሰብ ነው። እራስ ወዳዱ እኔነት (Ego) የሚለው ቃል ትርጉም ከሰው ሰው ይለያያል፣ እኔ ግን ቃሉን እዚህ ላይ የምጠቀምበት እንዲህ በሚል አንድምታ ነው፤ በንቃተ ህሊና አልባነት ምክንያት ከአዕምሮ ጋር በተደረገ ፅኑ ቁርኝት የተፈጠረ የውሸት ማንነት።

ለእራስ ወዳዱ እኔነት፣ ለእርሡ የአሁን ገዜ የሚባል ነገር የለም፤ ለእራስ ወዳዱ እኔነት አስፈላጊውና እግምት የሚገባው የባለፈውና የወደፊቱ ብቻ ነው። ሀቁ ግን ፈፅሞ የተገላቢጦሽ ሁኖ ሳለ፣ ይህንን የአሁን ግዜ አላስፈላጊ፤ የባለፈውና የወደፊቱ ግን አስፈላጊ እንዲሆን ያደረገው በእራስ ወዳዱ እኔነት ስልተ ዘዬ አዕምሮ ፈፅሞ ፈሩን እንዲስት ስለተደረገ ብቻ ነው። እራስ ወዳዱ እኔነት ሁልግዜም ቢሆን ግድ የሚለው የባለፈው ነው የባለፈውን ነፍስ ይዘራበታል፣ ምክንያቱም የባለፈው ከሌለማ አንተ ማን ቢሉህ ማነኝ ትላለህ? እራስ ወዳዱ እኔነት ህልውናውን ለማስጠቀጠል እራሡን ያለማሰለስ ከወደፊቱ ጋር ይተልማል እራሱንም ከወደፊቱ ትልም ውስጥ ያስገባል። እንዲሁም ደግሞ ስኬትን ወይም እፎይታን ከወደፊቱ ይሻል።

ወይም ደግሞ አዕምሮ፣ እርሡው እራሡ ለወደፊቱ ለተለመው ትልም ውጤት ሲል የአሁን ግዜን ከቁብም የማይቆጠር ያደርገዋል። እስቲ አዕምሮህን ልብ ብለህ አስተውለው፣ እናም ይህ እንዴት እንደሚሠራ እራስህ ታየዋለህ፡፡

የአርነት መውጫን ቁልፍ የያዘው የአሁን ግዜ (የአሁን ቅፅበት) ነው፣ ነገር ግን አንተ አዕምሮህን እስከ ሆንክ ድረስ፣ ማለትም አዕምሮህ ማለት አንተ፣ አንተ ማለት አዕምሮህን እስከሆንክና ከአዕምሮህ ጋር እስካልተፋታህ ድረስ ይህን ቁልፍ አታገኘውም፡፡

እዚህ ላይ አንድ ማስተዋል ያለብን ነገር አለ፤ ይኸውም ማሰብና ንቃተ ህሊና አቻ ትርጉም የላቸውም ፤ አቻም አይደሉም፡፡ ማሰብ የንቃተ ህሊና ቁንፅል መገለጫው ነው፡፡ ማሰብ ያለ ንቃተ ህሊና ህልውና ሊኖረው አይችልም፤ ንቃተ ህሊና ግን ያለ ሀሳብ እራሱን ችሎ መቆም ይችላል።

መገለጥ (የበራ ህይወት) ማለት ከሀሳብ ልቆ መገኘት ማለት ነው። መገለጥ ማለት ወደ ሀሳብ ደረጃ አለመቀልበስ ማለት ነው፡፡ ሁኖም ግን የእንስሳትና የእፅዋት ደረጃ ወደ ሆነው ከማሰብ በታች መውረድ ማለት አይደለም፡፡ የመገለጥ ሁናቴ ውስጥ መሆን ማለት አስፈላጊ በሆነ ጊዜ፣ የሚያስበውን አዕምሮህን መጠቀም ትችላለህ፡፡ እናም ደግሞ ስትጠቀምበትም ከበፊቱ ይልቅ በበለጠ አትኩሮትና ብቃት ትጠቀምበታለህ፡፡ ሁኖም ግን ከአንተ እውቅና ውጭ ለሚደረግ የአዕምሮ በሀሳብ መባዘንና ከአዕምሮ ውስጥ ውስጡን ማብሰልሰል ነፃ ነህ፡፡

እናም ደግሞ አንተ አዕምሮህንም ስትጠቀምም፣ ውስጣዊ መረጋጋትህም እንደተጠበቀ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ የሆነ አይነት የፈጠራ መፍትሔ በሚፈለግበት ወቅት በየጥቂት ደቂቃዎቹ አንድ ግዜ ወደ ማሰብ ሌላ ግዜ ደግሞ አዕምሮን ከሚላጋበትና በሀሳብ ከሚቆዝምበት ሁናቴው አውጥተህ እንዲሰክን እያደረግክ ስራህን ትከውናለህ፡፡ ማለትም አዕምሮ አለ፣ አዕምሮ የለም አይነት በነዚህ በሁለቱ መካከል አዕምሮህን በተገቢው መንገድ ትጠቀምበታለህ። አዕምሮ ሳይኖር ማለት ከሀሳብ ነፃ ሁኖ በንቃተ ህሊና ውስጥ መሆን ማለት ነው።

በተጨማሪም አሪፍ የሆነ የፈጠራ ሀሳብ የሚፈልቅልህ በዚህ ሁናቴ ስታስብ ብቻ ነው፤ ምክንያቱም ሀሳብ የነጠረ አቅም የሚኖረው በዚህ መንገድ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ ሀሳብ ህልቆ መሳፍርት ከሌለው ንቃተ ህሊና ጋር ካልተሳሰረ ግን ብዙም ሳይቆይ ባድማ፣ የተቃወስ እንዲሁም አጥፊ ይሆናል፡፡

የመኖር ዋስትና አቢይ ማሽኑ አዕምሮ ነው። አዕምሮ ከሌሎት አዕምሮዎች ጋር በመፋለም፣ በመከላከል መረጃን ማግኘትና መተንተን የሚችለው አዕምሮ ነው። ሁሉም እውነተኛ አርቲስቶች አውቀውትም ይሁን ሳያውቁት ፈጠራቸው የፈለቀው እንበለ አዕምሮ (አዕምሮ ሳይኖር) ውስጣዊ ርጋታና ስክነት ካለበት ከውስጥ ነው። ታላላቅ ሳይንቲቶች የሚባሉትም እንኳ የፈጠራ ስራቸው ከች ያለላቸው በአርምሞ ውስጥ ሁነው እንደሆነ ተናግረዋል።

ምንጭ ፦ የአሁን ሀያልነት
ደራሲ ፦ ኤክሀርት ቶሌ
ትርጉም ፦ብስራት እውነቱ

@Zephilosophy
@Zephilosophy